የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ትንቢተ ሕዝቅኤል 47

47
ከመቅደሱ የሚፈልቀው ውሃ
1 # ዘካ. 14፥8፤ ዮሐ. 7፥38፤ ራእ. 22፥1። ወደ ቤቱ መግቢያ መለሰኝ፤ እነሆ ውኃ ከቤቱ መድረክ በታች ወደ ምሥራቅ ይወጣ ነበር፥ የቤቱ ፊት ወደ ምሥራቅ ይመለከት ነበርና፤ ውኃውም ከቤቱ በስተ ቀኝ በኩል በታች በመሠዊያው በደቡብ በኩል ይወርድ ነበር። 2በሰሜኑ በር በኩል አወጣኝ፤ በውጭ ባለው መንገድ፥ ወደ ምሥራቅ ወደሚመለከት በውጭ ወዳለው በር አመጣኝ፤ እነሆ ውኃው በደቡብ በኩል ይፈስስ ነበር።
3ሰውዬው ገመድ በእጁ ይዞ ወደ ምሥራቅ ወጣ፥ አንድ ሺህ ክንድ ለካ፥ በውኃውም ውስጥ አሳለፈኝ፥ ውኃውም እስከ ቁርጫምጭሚት ድረስ ነበር። 4እንደገና አንድ ሺህ ለካ በውኃውም ውስጥ አሳለፈኝ፥ ውኃውም እስከ ጉልበት ድረስ ነበር። ደግሞም አንድ ሺህ ለካ በውኃውም ውስጥ አሳለፈኝ፥ ውኃውም እስከ ወገብ ድረስ ነበር። 5ደግሞም አንድ ሺህ ለካ ልሻገረውም የማልችለው ወንዝ ሆነ፤ ውኃውም ጥልቅ ነበረ፥ የሚዋኝበትም ውኃ ነበረ፤ ሰው ሊሻገረው የማይችለው ወንዝ ነበረ።
6እንዲህም አለኝ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ አይተሃልን? መራኝ፥ ወደ ወንዙም ዳር መለሰኝ። 7በተመለስሁም ጊዜ፥ እነሆ በወንዙ ዳር በዚህና በዚያ እጅግ ብዙ ዛፎች ነበሩ። 8እንዲህም አለኝ፦ ይህ ውኃ ወደ ምሥራቅ አውራጃ ይወጣል ወደ ዓረባም ይወርዳል ወደ ባሕሩም ይገባል፤ ወደ ባሕሩም ወደ ረከሰው ውኃ በገባ ጊዜ ውኃው ይፈወሳል። 9ወንዙ በሚገባበት ስፍራ ያለ ሕያው ነፍስ ያለው ተንቀሳቃሽ ሁሉ በሕይወት ይኖራል፤ ዓሣዎች እጅግ ይበዛሉ፤ ይህ ውኃ በዚያ ስለ ደረሰ የባሕሩ ውኃ ይፈወሳል፥ ወንዙ በሚገባበት ያለው ሁሉ በሕይወት ይኖራል። 10ከዔንጌዲ ጀምሮ እስከ ዔንዔግላይም ድረስ አጥማጆች በዚያ ይቆማሉ፤ የመረቦች መዘርጊያ ይሆናል፤ ዓሣዎችም እንደ ታላቁ ባሕር ዓሣ በየወገናቸው እጅግ ይበዛሉ። 11ረግረጉና እቋሪው ውኃ ግን አይፈወስም፤ ጨው እንደሆነ ይኖራል። 12#ራእ. 22፥2።በወንዙ ዳር በዚህና በዚያ ፍሬው የሚበላ ዛፍ ሁሉ ይበቅላል፥ ቅጠሉ አይረግፍም ፍሬውም አያልቅም፤ ውኃው ከመቅደስ ይወጣልና በየወሩ ሁሉ የፍሬ በኩር ያፈራል፤ ፍሬው ለመብል ቅጠሉም ለፈውስ ይሆናል።
አዳዲስ የምድሪቱ ወሰኖች
13ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ርስት አድርጋችሁ ለዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች ምድሪቱን የምትከፍሉበት ድንበር ይህ ነው። ለዮሴፍ ሁለት ድርሻ ይሆናል። 14እኩል አድርጋችሁ ተካፈሉት፤ ለአባቶቻችሁ ልሰጣቸው ምዬ ነበር፥ ይህች ምድር በርስትነት ለእናንተ ሆናለች።
15የምድሪቱ ድንበር ይህ ነው፤ በሰሜኑ ወገን ከታላቁ ባሕር ጀምሮ በሔትሎን መንገድ ወደ ጼዳድ መግቢያ፥ 16ሐማት፥ ቤሮታ፥ በደማስቆ ድንበርና በሐማት ድንበር መካከል ያለው ሲብራይም፥ በሐውራን ድንበር አጠገብ ያለው ሐጸርሃቲኮን፥ 17ድንበሩ ከባሕሩ ጀምሮ እስከ የደማስቆ ድንበር ሰሜን የሆነው ሐጻርዔኖን ይሆናል፥ በሰሜንም በኩል የሐማት ድንበር አለ። ይህም የሰሜኑ ድንበር ነው። 18የምሥራቁ ድንበር በሐውራንና በደማስቆ፤ በገለዓድና በእስራኤልም ምድር መካከል እስከ ዮርዳኖስ ይሆናል። ከሰሜኑ ድንበር ጀምሮ እስከ ምሥራቁ ባሕር እስከ ታማር ድረስ፤ ይህም የምሥራቁ ድንበር ነው። 19የደቡቡም ድንበር ከታማር ጀምሮ እስከ ሜርባ ቃዴስ ውኃ፥ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ይሆናል። ይህም የደቡቡ ድንበር ነው። 20የምዕራቡ ድንበር ከደቡቡ ድንበር ጀምሮ እስከ ሐማት መግቢያ አንጻር ድረስ ታላቁ ባሕር ይሆናል። ይህም የምዕራቡ ድንበር ነው።
21ይህችን ምድር እንደ እስራኤል ነገዶች መጠን ትከፋፈላላችሁ። 22ለእናንተና በእናንተ መካከል ለሚቀመጡ በእናንተም መካከል ልጆች ለወለዱ ስደተኞች ርስት አድርጋችሁ በዕጣ ትካፈሉአታላችሁ፤ እነርሱም በእስራኤል ልጆች መካከል እንዳሉ የአገር ልጆች ይሆኑላችኋል፥ በእስራኤልም ነገዶች መካከል ከእናንተ ጋር ርስትን ይወርሳሉ። 23ስደተኛው በተቀመጠበት ነገድ በዚያ ርስቱን ስጡት፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ