ትንቢተ ሕዝቅኤል 14:1-8

ትንቢተ ሕዝቅኤል 14:1-8 መቅካእኤ

ከእስራኤልም ሽማግሌዎች አንዳንዶች ወደ እኔ መጥተው በፊቴ ተቀመጡ። የጌታም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፦ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነዚህ ሰዎች ጣዖቶቻቸውን በልባቸው አኑረዋል። የበደላቸውንም የማሰናከያ ድንጋይ በፊታቸው አስቀምጠዋል፥ ታዲያ እንዲጠይቁኝ ልፍቀድላቸው? ስለዚህ ተናገራቸው፥ እንዲህም በላቸው፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ማንም ሰው ከእስራኤል ቤት ጣዖቶቹን በልቡ የሚያኖር፥ የበደሉንም የማሰናከያ ድንጋይ በፊቱ የሚያቆም፥ ወደ ነቢዩም የሚመጣ፥ እኔ ጌታ እንደ ጣዖታቱ ብዛት እመልስለታለሁ። ይህም የእስራኤልን ቤት ለመያዝ ነው፤ ሁሉም በጣዖቶቻቸው ምክንያት በልባቸው ከእኔ ተለይተዋልና፤ ስለዚህ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፦ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ተመለሱ፥ ከጣዖቶቻችሁም ተመለሱ፥ ከርኩሰቶቻችሁ ሁሉ ፊታችሁን መልሱ። ማንም ከእስራኤልም ቤት፥ በእስራኤልም የሚቀመጥ መጻተኛ፥ ራሱን ከእኔ የሚለይ፥ ጣዖቶቹን በልቡ የሚያኖር፥ የበደሉንም የማሰናከያ ድንጋይ በፊቱ የሚያቆም፥ ስለ እኔም ለመጠየቅ ወደ ነቢዩ የሚመጣ፥ እኔ ጌታ ራሴ እመልስለታለሁ፥ ፊቴን በዚያ ሰው ላይ አደርጋለሁ ምልክትና ምሳሌም አደርገዋለሁ፥ ከሕዝቤም መካከል አስወግደዋለሁ፥ በዚያን ጊዜ እኔ ጌታ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።