የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፀአት 9

9
5. የከብቶች ዕልቂት
1ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ወደ ፈርዖን ግባ እንዲህም በለው የዕብራውያን አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ። 2ልትለቅቃቸውም እንቢ ብትል፥ ብትይዛቸውም፥ 3እነሆ የጌታ እጅ በሜዳ ውስጥ ባሉት በከብቶችህ፥ በፈረሶች፥ በአህዮች፥ በግመሎች፥ በበሬዎችና በበጎች ላይ ትሆናለች፤ ብርቱ ተላላፊ በሽታ ይወርዳል። 4ጌታም በእስራኤልና በግብጽ ከብቶች መካከል ይለያል፤ ከእስራኤልም ልጆች ከብት አንድ ስንኳ አይሞትም።’” 5ጌታም፦ “ነገ ጌታ ይህን ነገር በምድር ላይ ያደርጋል” ብሎ ጊዜን ወሰነ። 6ጌታም ያንን ነገር በማግስቱ አደረገ፥ የግብጽም ከብት ሁሉ ሞተ፤ ከእስራኤል ልጆች ከብት ግን አንድ ስንኳ አልሞተም። 7ፈርዖንም ላከ፥ እነሆም ከእስራኤል ልጆች ከብት አንድ ስንኳ አልሞተም። የፈርዖን ልብ ግን ደነደነ፥ ሕዝቡንም አልለቀቀም።
6. ብጉንጅ
8ጌታም ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ “እጃችሁን ሞልታችሁ ከምድጃ አመድ ውሰዱ፥ ሙሴም በፈርዖን ፊት ወደ ሰማያት ይበትነዋል። 9እርሱም በግብጽ ምድር ሁሉ ትቢያ ይሆናል፥ በግብጽም ምድር ሁሉ በሰውና በእንስሳ ላይ ፈሳሽ የሚያወጣ ብጉንጅ ይሆናል።” 10#ራእ. 16፥2።ከምድጃውም አመድ ወስደው በፈርዖን ፊት ቆሙ፤ ሙሴም ወደ ሰማያት በተነው፥ በሰውና በእንስሳ ላይም ፈሳሽ የሚያወጣ ብጉንጅ ሆነ። 11ብጉንጅ በጠንቋዮቹና በግብጻውያን ሁሉ ላይ ነበር፤ ጠንቋዮቹም ብጉንጅ ስለ ነበረባቸው በሙሴ ፊት መቆም አልቻሉም፤ 12ጌታም የፈርዖንን ልብ አጸና፤ ጌታ ሙሴን እንደ ተናገረው ፈርዖን አልሰማቸውም።
7. በረዶ
13ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ማልደህ ተነሣ፥ በፈርዖንም ፊት ቁም እንዲህም በለው፦ የዕብራውያን አምላክ ጌታ እንዲህ ይላል፦ ‘እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ። 14በዚህ ጊዜ መቅሠፍቴን ለልብህ በአገልጋዮችህ በሕዝብህም በምድር ሁሉ ላይ እልካለሁ ይህም እንደ እኔ ያለ እንደሌለ እንድታውቅ ነው። 15አሁን እጄን ዘርግቼ አንተንና ሕዝብህን በተላላፊ በሽታ በመታሁህ ነበር፥ አንተም ከምድር በጠፋህ ነበር፤ 16#ሮሜ 9፥17።ነገር ግን እንድትቆም ያደረግኩት ኃይሌን እንድገልጥብህና ስሜም በምድር ሁሉ ላይ እንዲታወጅ ነው። 17እንዳትለቅቃቸው አሁንም በሕዝቤ ላይ ትታበያለህ፤ 18እነሆ እኔ ነገ በዚህ ጊዜ በግብጽ፥ ከተመሠረተች ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እንደ እርሱ ያለ ሆኖ የማያውቅ፥ እጅግ ከባድ በረዶ አዘንባለሁ። 19ስለዚህም ልከህ ከብቶችህንና በሜዳ ያለ የአንተ የሆነውን ሁሉ አምጣ፤ በሜዳ የተገኘ ወደ ቤት ያልገባ ሰውና እንሰሳ ሁሉ ላይ በረዶ ይወርዳል እነርሱም ይሞታሉ።’” 20ከፈርዖን አገልጋዮች የጌታን ቃል የፈራ አገልጋዮቹንና ከብቶቹን ወደ ቤቶቹ አሸሸ፤ 21የጌታንም ቃል በልቡ ያላስቀመጠ አገልጋዮቹንና ከብቶቹን በሜዳ ተወ።
22ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በግብጽ ምድር ሁሉ ላይ በሰው፥ በከብት፥ በእርሻ ቡቃያ ሁሉ ላይ፥ በግብጽ ምድር ሁሉ በረዶ እንዲሆን እጅህን ወደ ሰማያት ዘርጋ።” 23ሙሴም በትሩን ወደ ሰማያት ዘረጋ፤ ጌታም ነጎድጓድና በረዶ ላከ፥ እሳትም ወደ ምድር ወረደ፤ ጌታም በግብጽ ምድር ላይ በረዶ አዘነበ። 24#ራእ. 8፥7፤ 16፥21።በረዶና እሳት ነበረ፥ በበረዶውም መካከል እጅግ ከባድ የሚበርቅ እሳት ነበር፥ በግብጽ ምድር ሁሉ አገር ከሆነ ጀምሮ እንደ እርሱ ሆኖ አያውቅም። 25በረዶውም በግብጽ ምድር ሁሉ በሜዳ ያለውን ሁሉ ከሰው እስከ እንስሳ መታ፤ የእርሻን ቡቃያ መታ፥ በረዶውም የአገሩን ዛፍ ሁሉ ሰበረ። 26የእስራኤል ልጆች በነበሩባት በጎሼን ምድር ብቻ በረዶ አልነበረም።
27ፈርዖንም ልኮ ሙሴንና አሮንን አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “በዚህ ጊዜ ኃጢአትን ሰርቻለሁ፤ ጌታ ጻድቅ ነው፥ እኔና ሕዝቤም በደለኞች ነን። 28የአምላክ ነጎድጓድ በረዶውም በዝቶአልና ወደ ጌታ ጸልዩ፤ እለቅቃችኋለሁ፥ ከዚህ በኋላ እዚህ አትቀመጡም።” 29ሙሴም እንዲህ አለው፦ “ከከተማ እንደ ወጣሁ እጄን ወደ ጌታ እዘረጋለሁ፤ ምድሪቱ የጌታ እንደ ሆነች እንድታውቅ፥ ነጎድጓዱ ይቆማል፥ በረዶውም ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። 30አንተና አገልጋዮችህ ጌታ አምላክን ገና እንደማትፈሩ አውቃለሁና።” 31ገብሱና ተልባው ተመታ፤ ገብሱ ገና እሸት ተልባውም እንቡጥ ስለ ነበረ ነው። 32ስንዴውና አጃው ግን ጊዜው ገና ነበርና አልተመታም። 33ሙሴም ከፈርዖን ዘንድ ከከተማ ወጣ፥ እጁንም ወደ ጌታ ዘረጋ፤ ነጎድጓዱም በረዶውም ቆመ፥ ዝናቡም ወደ ምድር አልዘነበም። 34ፈርዖንም ዝናቡ፥ በረዶውና ነጎድጓዱ እንደ ቆመ ባየ ጊዜ ኃጢአትን ጨመረ፥ እርሱና አገልጋዮቹም ልባቸውን አደነደኑ። 35የፈርዖንም ልብ ጸና፤ ጌታም በሙሴ አፍ እንደ ተናገረ የእስራኤልን ልጆች አልለቀቀም።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ