የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፀአት 7

7
1ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እይ፥ እኔ ለፈርዖን አምላክ አድርጌሃለሁ፤ ወንድምህም አሮን ነቢይህ ይሆናል። 2አንተ ያዘዝሁህን ሁሉ ትነግረዋለህ፤ ወንድምህም አሮን የእስራኤልን ልጆች ከአገሩ እንዲለቅ ፈርዖንን ይነግረዋል። 3#የሐዋ. 7፥36።እኔም የፈርዖንን ልብ አደነድናለሁ፥ ምልክቶቼንና ድንቆቼን በግብጽ ምድር ላይ አበዛለሁ። 4ፈርዖንም እናንተን አይሰማችሁም፥ እጄንም በግብጽ ላይ አደርጋለሁ፥ ሠራዊቴን፥ ሕዝቤን የእስራኤልን ልጆች፥ በታላቅ የፍርድ ሥራ ከግብጽ ምድር አወጣለሁ። 5ግብፃውያንም፥ እጄን በግብጽ ላይ ዘርግቼ የእስራኤልን ልጆች ከመካከላቸው ሳወጣ፥ እኔ ጌታ እንደሆንኩ ያውቃሉ።” 6ሙሴና አሮንም እንዲሁ አደረጉ፤ ጌታ እንዳዘዛቸው አደረጉ። 7ፈርዖንን ባናገሩት ጊዜ ሙሴ የሰማንያ ዓመት ሰው ነበር፥ አሮንም የሰማንያ ሦስት ዓመት ሰው ነበር።
የአሮን ተአምራዊ በትር
8ጌታም ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ 9“ፈርዖን ‘ተአምራትን በማድረግ ማንነታችሁን አሳዩኝ’ ሲላችሁ፥ አሮንን ‘በትርህን ወስደህ እባብ እንዲሆን በፈርዖን ፊት ጣለው’ በለው፥ በትሩም እባብ ይሆናል።” 10ሙሴና አሮንም ወደ ፈርዖን ሄዱ፥ ጌታም እንዳዘዛቸው እንዲሁ አደረጉ፤ አሮንም በትሩን በፈርዖንና በአገልጋዮቹ ፊት ጣለ፥ እባብም ሆነ። 11ፈርዖንም ጠቢባንንና አስማተኞችን ጠራ፤ የግብጽም አስማተኞች ደግሞ በአስማታቸው እንዲሁ አደረጉ። 12እያንዳንዳቸውም በትራቸውን ጣሉ፥ እባቦችም ሆኑ፤ የአሮን በትር ግን በትራቸውን ዋጠ። 13ልክ ጌታ እንደ ተናገረው የፈርዖን ልብ ጸና፥ አልሰማቸውምም።
ዐሥሩ መቅሠፍታት
1. የውኃ ወደ ደም መለወጥ
14 # ጥበ. 11፥6-8። ጌታም ሙሴን አለው፦ “የፈርዖን ልብ ደነደነ፥ ሕዝቡንም አልለቅም አለ። 15ወደ ፈርዖን በጠዋት ሂድ፤ እነሆ ወደ ውኃ ይወጣል፥ አንተም እንድትገናኘው በወንዝ ዳር ትቆማለህ፤ ወደ እባብም የተለወጠውን በትር በእጅህ ትወስዳለህ። 16እንዲህም ትለዋለህ፦ ‘ጌታ የዕብራውያን አምላክ፦ በምድረ በዳ እንዲያገለግሉኝ ሕዝቤን ልቀቅ፥ ብሎ ወደ አንተ ላከኝ፤ እነሆ አንተ እስከ ዛሬ አልሰማህም። 17#ራእ. 16፥4።ጌታ እንዲህ ይላል፦ እኔ ጌታ እንደሆንሁ በዚህ ታውቃለህ፤ እነሆ እኔ በዓባይ ወንዝ ያለውን ውኃ በእጄ ባለው በትር እመታለሁ፥ ወደ ደምም ይለወጣል። 18በዓባይ ወንዝ ያሉትም ዓሦች ይሞታሉ፥ የዓባይ ወንዝም ይገማል፤ ግብፃውያንም የዓባይን ወንዝ ውኃ ለመጠጣት ይጠላሉ።’” 19ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “አሮንን እንዲህ በለው፦ ‘በትርህን ውሰድ፥ በግብጽ ውኆች፥ በፈሳሾቻቸው፥ በወንዞቻቸው፥ በኩሬዎቻቸው፥ በውኃ ማጠራቀሚያዎቻቸውም ላይ ደም እንዲሆኑ እጅህን ዘርጋ፤ በግብጽም ምድር ሁሉ በእንጨት ዕቃና በድንጋይ ዕቃ ሁሉ ደም ይሆናል።’”
20ሙሴና አሮንም ልክ ጌታ እንዳዘዛቸው እንዲሁ አደረጉ፤ በትሩንም አነሣ፥ በፈርዖንና በአገልጋዮቹም ፊት በዓባይ ወንዝ የነበረውን ውኃ መታ፤ በዓባይ ወንዝ ላይ የነበረው ውኃ ሁሉ ወደ ደም ተቀየረ። 21በዓባይ ወንዝ የነበሩ ዓሦችም ሞቱ፤ የዓባይም ወንዝ ገማ፥ ግብጻውያንም ከዓባይ ወንዝ ውኃ መጠጣት አልቻሉም፤ ደሙም በግብጽ ምድር ሁሉ ላይ ነበረ። 22የግብጽም አስማተኞች በአስማታቸው እንዲሁ አደረጉ፤ የፈርዖንም ልብ ጸና፥ ጌታም እንደ ተናገረ አልሰማቸውም። 23ፈርዖንም ተመልሶ ወደ ቤቱ ገባ፥ ይህንም ደግሞ በልቡ አላኖረውም። 24ግብጽም ሁሉ የዓባይ ወንዝ አካባቢውን ቆፈሩ የዓባይን ወንዝ ውኃ መጠጣት አልቻሉምና። 25ጌታ ወንዙን ከመታ በኋላ ሰባት ቀን ተፈጸመ። 26ጌታም ሙሴን ተናገረው፦ “ወደ ፈርዖን ግባ እንዲህም በለው፦ ‘ጌታ እንዲህ ይላል፦ እንዲያገለግለኝ ሕዝቤን ልቀቅ። 27ለመልቀቅ እንቢ ብትል ግን እነሆ እኔ አገርህን ሁሉ በእንቁራሪቶች እመታለሁ። 28የዓባይ ወንዝም በእንቁራሪቶች ይሞላል፥ ወጥተውም ወደ ቤትህ፥ ወደ መኝታ ቤትህ፥ ወደ አልጋህም፥ ወደ አገልጋዮችህና ሕዝብህም ቤት፥ ወደ ምድጆችህ፥ ወደ ማቡኪያ ዕቃህም ይገባሉ፤ 29እንቁራሪቶቹም በአንተ፥ በሕዝብህና በሁሉም አገልጋዮችህ ላይ ይወጣሉ።’”

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ