የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፀአት 6

6
የእስራኤል ከግብፃውያን አርነት መውጣት እንደ ተረጋገጠ
1ጌታም ሙሴን አለው፦ “አሁን ፈርዖንን ምን እንደማደርገው ታያለህ በጸናች እጅ ይለቅቃቸዋል፥ በጸናችም እጅ ከምድሩ አስወጥቶ ይሰድዳቸዋል።”
2 # ዘፍ. 17፥1፤ 28፥3፤ 35፥11፤ ዘፀ. 3፥13-15። እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው አለውም፦ “እኔ ጌታ ነኝ፤ 3ለአብርሃም ለይስሐቅ ለያዕቆብም ሁሉን የሚችል አምላክ ሆኜ ተገለጥኩላቸው፤ ጌታ የሚለውን ስሜን ግን አላስታወቅኳቸውም። 4ደግሞም የከነዓንን ምድር፥ በእንግድነት ተቀምጠውበት የነበረውን የእንግድነታቸው ምድር እሰጣቸው ዘንድ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳኔን መሰረትኩ። 5ደግሞም እኔ ግብፃውያን እንዲሰሩ የሚያስገድዷቸውን የእስራኤልን ልጆች ጩኸት ሰማሁ፤ ቃል ኪዳኔንም አሰብሁ። 6ስለዚህም ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው፦ ‘እኔ ጌታ ነኝ፥ ከግብፃውያን ጭቆና አወጣችኋለሁ፥ ከተገዥነታችሁም አላቅቃችኋለሁ፤ በተዘረጋች ክንድ በታላቅ የፍርድ ሥራም አድናችኋለሁ፤ 7ለእኔ ሕዝብ አድርጌ እቀበላችኋለሁ፥ አምላክም እሆናችኋለሁ፤ እኔም ከግብጽ ጭቆና ያወጣኋችሁ ጌታ አምላካችሁ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ። 8ለአብርሃም ለይስሐቅና ለያዕቆብ እሰጣታለሁ ብዬ እጄን ወደ አነሳሁባት ምድር አመጣችኋለሁ፤ እርሷንም ርስት አድርጌ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ ጌታ ነኝ።’” 9ሙሴም ይህን ለእስራኤል ልጆች ተናገረ፤ እነርሱ ግን ከመንፈሳቸው መሰበር ከከባዱም ሥራ የተነሣ ሙሴን አልሰሙትም።
10ጌታም ሙሴን አለው፦ 11“ግባ፥ የግብጽን ንጉሥ ፈርዖንን የእስራኤልን ልጆች ከምድሩ እንዲለቅ ንገረው።” 12ሙሴም በጌታ ፊት፦ “እነሆ የእስራኤል ልጆች አልሰሙኝም፤ ታድያ እንዴት ፈርዖን ይሰማኛል? እኔ ደግሞ ከንፈሬ ያልተገረዘ ሰው ነኝ” ብሎ ተናገረ። 13ጌታም ሙሴንና አሮንን ተናገራቸው፥ የእስራኤልን ልጆችንና የግብጽ ንጉሥ ፈርዖንን የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ እንዲያወጣቸው እንዲነግሩት አዘዛቸው።
የሙሴና የአሮን ትውልድ
14የአባቶቻቸው ቤት አለቆች እነዚህ ናቸው። የእስራኤል የበኩር ልጅ የሮቤል ልጆች ሐኖክ፥ ፋሉ፥ ሔፅሮንና ካርሚ፤ እነዚህ የሮቤል ወገኖች ናቸው። 15የስምዖንም ልጆች ይሙኤል፥ ያሚን፥ ኦሃድ፥ ያኪን፥ ጾሐር፥ የከነዓናዊቱም ልጅ ሻኡል፤ እነዚህ የስምዖን ወገኖች ናቸው። 16#ዘኍ. 3፥17-20፤ 26፥57፤58፤ 1ዜ.መ. 6፥16-19።እነዚህ የሌዊ ልጆች ስሞች እንደ ትውልዳቸው ጌርሾን፥ ቀሃት፥ ሜራሪ ናቸው። የሌዊም የሕይወቱ ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው። 17የጌርሾንም ልጆች እንደ ወገኖቻቸው ሊብኒና፥ ሽምኢ ናቸው። 18የቀሃትም ልጆች ዓምራም፥ ይፅሃር፥ ሔብሮን፥ ዑዚኤል ናቸው፤ የቀሃትም የሕይወቱ ዘመን መቶ ሠላሳ ሦስት ዓመት ነው። 19የሜራሪ ልጆች ማሕሊ፥ ሙሺ ናቸው። እነዚህ እንደ ትውልዳቸው የሌዊ ወገኖች ናቸው። 20ዓምራምም የአባቱን እኅት ዮካቤድን አገባ፥ አሮንንና ሙሴንም ወለደችለት፤ የዓምራምም የሕይወቱ ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው። 21የይፅሃር ልጆች ቆራሕ፥ ኔፌግ፥ ዚክሪ ናቸው። 22የዑዚኤል ልጆች ሚሻኤል፥ ኤልጻፋን፥ ሢትሪ ናቸው። 23አሮንም የዓሚናዳብን ልጅ የናሕሾንን እኅት ኤሊሼባን አገባ፥ እርሷም ናዳብ፥ አቢሁ፥ ኤልዓዛርንና ኢታማርን ወለደችለት። 24የቆራሕ ልጆች አሲር፥ ኤልቃናና፥ አቢያሳፍ ናቸው፤ እነዚህ የቆራሓውያን ወገኖች ናቸው። 25የአሮንም ልጅ ኤልዓዛር ከፑቲኤል ልጆች አንዷን ሚስት አገባ፥ እርሷም ፒንሐስን ወለደችለት። እነዚህ እንደ ወገኖቻቸው የሌዋውያን አባቶች አለቆች ናቸው። 26እነዚህ አሮንና ሙሴ ጌታ፦ “የእስራኤልን ልጆች በየነገዳቸው ከግብጽ ምድር አውጡ” ያላቸው ናቸው። 27እነዚህ ከግብጽ ንጉሥ ከፈርዖን ጋር የእስራኤልን ልጆች ከግብጽ ስለማውጣት የተነጋገሩ ናቸው፤ እነዚህም ሙሴና አሮን ናቸው።
እግዚአብሔር ለሙሴና ለአሮን የሰጠው ትእዛዝ
28ጌታ በግብጽ አገር ሙሴን በተናገረው ቀን፥ 29እርሱም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እኔ ጌታ ነኝ፤ ለግብጽ ንጉሥ ለፈርዖን እኔ የምነግርህን ሁሉ ንገረው።” 30ሙሴም በጌታ ፊት፦ “እነሆ እኔ ከንፈሬ ያልተገረዘ ነኝ፤ እንዴትስ ፈርዖን ይሰማኛል?” አለ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ