የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፀአት 36

36
1ባስልኤል፥ ኤልያብና ጥበበኞች ሁሉ፥ የመቅደሱን አገልግሎት ሥራ ሁሉ እንዲያደርጉና እንዲያውቁ ጌታ ጥበብንና ማስተዋልን የሰጣቸው ጌታ ያዘዘውን ነገር ሁሉ አደረጉ።
2ሙሴም ባስልኤልን፥ ኤልያብንና ጌታ በልቡ ጥበብን ያሳደረበትን ጥበበኛ ሰው ሁሉ፥ ሥራውን ለመሥራት ልቡ ያነሣሣውን ሁሉ ጠራቸው። 3የመቅደሱን ሥራ ለመሥራት የእስራኤል ልጆች ያመጡትን ስጦታ ሁሉ ከሙሴ ወሰዱ። እነዚያም በፈቃዳቸው የሚያቀርቡትን ስጦታ አሁንም ማለዳ ማለዳ ወደ እርሱ ያመጡ ነበር። 4የመቅደሱን ሥራ የሚሠሩ ጠቢባን ሁሉ ሥራቸውን ትተው መጡ፥ 5ሙሴንም፦ “ሕዝቡ ጌታ እንዲሠራ ላዘዘው ሥራ ከበቂ በላይ አመጡ” አሉት። 6ሙሴም በሰፈሩ ውስጥ አዋጅ እንዲተላለፍ አዘዘ፦ “ወንድ ወይም ሴት ለመቅደሱ ስጦታ ከእንግዲህ ወዲህ አያምጣ”፤ ሕዝቡም እንዳያመጡ ተከለከሉ። 7ያመጡት ነገር ሥራውን ሁሉ ለመፈጸም በቅቶ ይተርፍ ነበር።
የድንኳኑ አሠራር
8ሥራ ሲሠሩ ከነበሩት ጥበበኞች የሆኑት ሁሉ ማደሪያውን ሠሩ፤ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ፥ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ግምጃ፥ ኪሩቤልም የተጠለፈባቸው ዐሥር መጋረጃዎች ሠሩ። 9የእያንዳንዱ መጋረጃ ርዝመቱ ሀያ ስምንት ክንድ፥ ወርዱ አራት ክንድ ነበረ፤ የሁሉም መጋረጃዎች መጠን እኩል ነበር። 10አምስቱን መጋረጃዎች እርስ በርሳቸው አጋጠመ፥ ሌሎቹንም አምስት መጋረጃዎች እንዲሁ እርስ በርሳቸው አጋጠመ። 11በአንደኛው መጋረጃ ጠርዝ በመጋጠሚያው ላይ የሰማያዊው ግምጃ ቀለበቶች አደረገ፤ ደግሞ በሁለተኛው መጋረጃ ጠርዝ በመጋጠሚያው ላይ እንዲሁ አደረገ። 12አምሳ ቀለበቶችን በአንደኛው መጋረጃ አደረገ፥ አምሳ ቀለበቶች በሁለተኛው መጋረጃ ጠርዝ መጋጠሚያ አደረገ፤ ቀለበቶቹ እርስ በርሳቸው ፊት ለፊት የሚተያዩ ነበሩ። 13አምሳ የወርቅ መያዣዎች ሠራ፤ መጋረጆችንም እርስ በርሳቸው በመያዣዎች አጋጠማቸው፤ ማደሪያውም አንድ ወጥ ሆነ።
14ከማደሪያው በላይ ለሚሆነው ድንኳን መጋረጃዎችን ከፍየል ጠጉር ሠራ፤ ዐሥራ አንድ መጋረጃዎችን ሠራ። 15የእያንዳንዱ መጋረጃ ርዝመት ሠላሳ ክንድ፥ የእያንዳንዱም መጋረጃ ወርድ አራት ክንድ ነበረ፤ የዐሥራ አንዱም መጋረጃዎች መጠን እኩል ነበረ። 16አምስቱን መጋረጃዎች አንድ ላይ ለብቻ፥ ስድስቱንም መጋረጃዎች አንድ ላይ ለብቻ አድርጎ አጋጠማቸው። 17ከተጋጠሙት መጋረጃዎች በአንደኛው መጋረጃ ጠርዝ ላይ አምሳ ቀለበቶች አደረገ፤ እንዲሁም በሁለተኛው መጋረጃ ጠርዝ በሚጋጠሙበት በኩል አምሳ ቀለበቶች አደረገ። 18ድንኳኑ አንድ ወጥ እንዲሆን የሚያጋጥሙበት አምሳ የነሐስ መያዣዎችን ሠራ። 19ለድንኳኑ መሸፈኛ ከቀይ አውራ በግ ቁርበት፥ በላዩ ላይ የሚሆን መሸፈኛ ከአቆስጣ ቁርበት ሠራስስ።
20ለማደሪያው የሚቆሙ ሳንቃዎችን ከግራር እንጨት ሠራ። 21የእያንዳንዱ ሳንቃ ርዝመት ዐሥር ክንድ፥ ወርድ አንድ ክንድ ተኩል ነበረ። 22እያንዳንዱ ሳንቃ አንዱ በአንዱ ላይ የሚያያዝበት ሁለት ማጋጠሚያዎች ነበሩት፤ ለማደሪያው ሳንቃዎች በሙሉ እንዲሁ አደረገ። 23ለማደሪያው ሳንቃዎችን አደረገ፤ በደቡብ በኩል ሃያ ሳንቃዎችን አደረገ፤ 24ከሃያው ሳንቃዎች በታች አርባ የብር እግሮችን አደረገ፤ በአንደኛው ሳንቃ ለሁለቱ ማጋጠሚያዎች ሁለት እግሮች፥ በሁለተኛው ሳንቃ ለሁለቱ ማጋጠሚያዎች ሁለት እግሮች አደረገ። 25ለማደሪያው ለሁለተኛው ወገን በሰሜን በኩል ሃያ ሳንቃዎችን አደረገ፤ 26አርባ የብር እግሮች፥ ከአንዱ ሳንቃ በታች ሁለት እግሮች፥ ከአንዱም ሳንቃ በታች ሁለት እግሮች አደረገ። 27በማደሪያው በስተ ኋላ በምዕራብ በኩል ስድስት ሳንቃዎችን አደረገ። 28በማደሪያው በሁለቱ ማዕዘን በስተ ኋላ ሁለት ሳንቃዎችን አደረገ። 29ከታችም እስከ ላይ እስከ አንደኛው ቀለበት ድረስ አንድ ሳንቃ ድርብ ነበረ፤ ለሁለቱም ማዕዘን እንዲሁ ሁለት ነበሩ። 30ስምንት ሳንቃዎች ነበሩ፥ የብር እግሮቻቸውም ዐሥራ ስድስት እግሮች ነበሩ፥ ከእያንዳንዱ ሳንቃ በታች ሁለት እግሮች ነበሩ።
31ከግራር እንጨት መወርወሪያዎችን ሠራ፥ በማደሪያው በአንደኛው በኩል ላሉት ሳንቃዎች አምስት፥ 32በማደሪያው በሁለተኛው በኩል ላሉት ሳንቃዎች አምስት መወርወሪያዎች፥ ከማደሪያው በስተ ኋላ በምዕራቡ በኩል ላሉት ሳንቃዎች አምስት መወርወሪያዎችን ሠራ። 33በመካከል ያለውን መወርወሪያ በሳንቆቹ መካከል ከዳር እስከ ዳር እንዲያልፍ አደረገ። 34ሳንቃዎቹን በወርቅ ለበጣቸው፥ ቀለበቶቻቸውንም የመወርወሪያው ማስገቢያ እንዲሆኑ ከወርቅ ሠራ፥ መወርወሪያዎቹንም በወርቅ ለበጣቸው።
35መጋረጃውንም ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይም ግምጃና ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ ሠራ፤ ብልህ ሠራተኛ እንደሠራው ኪሩቤልን በእርሱ ላይ አደረገ። 36አራት ምሰሶዎችን ከግራር እንጨት ሠርቶ በወርቅም ለበጣቸው፤ ኩላቦቻቸው የወርቅ ነበሩ፤ ለእነርሱም አራት የብር እግሮች ሠራላቸው። 37ለድንኳኑም ደጃፍ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይ ግምጃና ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ የተጠለፈ መጋረጃ አደረገ፤ 38አምስቱን ምሰሶዎችንና ኩላቦቻቸውን አደረገ፤ ጉልላቶቻቸውንና ዘንጎቻቸውን በወርቅ ለበጣቸው፥ አምስቱ እግሮቻቸው የነሐስ ነበሩ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ