በነዚያም ቀኖች፥ ሙሴ ባደገ ጊዜ ወደ ወንድሞቹ ወጣ፥ የሥራቸውንም መከራ ተመለከተ፤ የግብጽም ሰው ከወንድሞቹ አንድ የሆነውን ዕብራዊ ሰው ሲመታ አየ። ወዲህና ወዲያም ተመለከተ፥ ማንንም አላየም፥ ግብፃዊውንም ገደለው፥ በአሸዋም ውስጥ ደበቀው። በሁለተኛውም ቀን ወጣ፥ ሁለት ዕብራውያን ሰዎች ሲጣሉ አየ፥ በዳዩንም፦ “ለምን ባልንጀራህን ትመታዋለህ?” አለው። እሱም፦ “አንተን በእኛ ላይ አለቃና ዳኛ አድርጎ የሾመህ ማን ነው? ግብፃዊውን እንደ ገደልኸው ልትገድለኝ ትፈልጋለህን?” አለው። ሙሴም፦ “በእውነት ይህ ነገር ታውቆአል” ብሎ ፈራ። ፈርዖንም ይህን ነገር በሰማ ጊዜ ሙሴን ሊገድለው ፈለገ። ሙሴ ግን ከፈርዖን ፊት ኮበለለ፥ በምድያምም ምድር ተቀመጠ፥ በውኃም ጉድጓድ አጠገብ ተቀመጠ። የምድያምም ካህን ሰባት ሴቶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም መጥተው ውኃ ቀዱ፥ የአባታቸውንም በጎች ሊያጠጡ የውሀውን ገንዳ ሞሉ። እረኞችም መጥተው ገፉአቸው፤ ሙሴ ግን ተነሥቶ ረዳቸው፥ በጎቻቸውንም አጠጣላቸው። ወደ አባታቸው ወደ ሩኤልም ሄዱ እርሱም፦ “ለምን ዛሬ ፈጥናችሁ መጣችሁ?” አላቸው። እነርሱም፦ “አንድ ግብፃዊ ሰው ከእረኞች እጅ አዳነን፥ ደግሞም ቀዳልን፥ በጎቻችንንም አጠጣ” አሉት። ልጆቹንም፦ “ሰውዬው የት ነው? ለምንስ ይህንን ሰው ተዋችሁት? ጥሩት ምግብም ይብላ” አላቸው። ሙሴም ከዚያ ሰው ጋር ሊቀመጥ ፈቀደ፤ ልጁንም ጺጶራን ለሙሴ ሰጠው። ወንድ ልጅም ወለደች፦ “በሌላ ምድር መጻተኛ ነኝ” ሲል ስሙን “ጌርሾም” ብሎ ጠራው። ከብዙ ቀኖች በኋላ የግብጽ ንጉሥ ሞተ፤ የእስራኤልም ሕዝቦች ከባርነት የተነሣ አለቀሱ፥ ጮኹም፥ ስለባርነታቸውም የልመና ጩኸታቸው ወደ እግዚአብሔር ወጣ። እግዚአብሔርም የለቅሶአቸውን ድምፅ ሰማ፥ እግዚአብሔርም ከአብርሃምና ከይስሐቅ ከያዕቆብም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን አስታወሰ። እግዚአብሔርም የእስራኤልን ሕዝቦች አየ፥ እግዚአብሔርም የደረሰባቸውን ነገር አወቀ።
ኦሪት ዘፀአት 2 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ኦሪት ዘፀአት 2:11-25
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች