ኦሪት ዘፀአት 12:1-34

ኦሪት ዘፀአት 12:1-34 መቅካእኤ

ጌታም በግብጽ ምድር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ “ይህ ወር የወሮች መጀመሪያ ይሁናችሁ፤ ከዓመቱ ወሮችም የመጀመሪያ ይሁናችሁ። ለእስራኤል ልጆች ማህበር ሁሉ እንዲህ ብላችሁ ንገሩ። በዚህ ወር በአሥረኛው ቀን ሰው ሁሉ ለአባቱ ቤት አንድ ጠቦት፥ ለአንድ ቤትም አንድ ጠቦት ይውሰድ። የቤተሰቡ ቍጥር ም ለጠቦቱ የሚያንስ ከሆነ እርሱና ለቤቱ የቀረበው ጎረቤቱ በእያንዳንዱ ሰው ቍጥር አንድ ጠቦት ይውሰድ፤ እያንዳንዱም እንደሚበላው መጠን ከጠቦቱ ይካፈሉ። የእናንተ ጠቦት ነውር የሌለበት፥ ተባዕት፥ የአንድ ዓመት ይሁን፤ ከበጎች ወይም ከፍየሎች ውሰድ። በዚህም ወር እስከ ዐሥራ አራተኛው ቀን ድረስ ጠብቁት፤ የእስራኤልም ማኅበር ጉባኤ ሁሉ ሲመሽ ይረዱት። ከደሙም ጥቂት ወስደው በሚበሉበት ቤት ሁለቱን መቃንና ጉበኑን ይቀቡት። ሥጋውን በዚያች ሌሊት ይብሉ፤ በእሳት የተጠበሰውን ካልቦካ ቂጣና ከመራራ ቅጠል ጋር ይብሉት። ጥሬውን ወይም በውኃ የበሰለውን አትብሉ፥ ነገር ግን ራሱ፥ ከእግሮቹና ከሆድ ዕቃው ጋር በእሳት የተጠበሰውን ብሉት። ከእርሱም እስከ ጥዋት አንዳች አታስቀሩ፤ እስከ ጥዋት የቀረውንም በእሳት አቃጥሉት። እንግዲህ ወገቦቻችሁን ታጥቃችሁ፥ ጫማችሁን በእግራችሁ፥ በትራችሁንም በእጃችሁ አድርጋችሁ ብሉት፥ ፈጥናችሁም ብሉት፤ ለጌታ ፋሲካ ነው። እኔም በዚያች ሌሊት በግብጽ ምድር አልፋለሁ፥ በግብጽም ምድር ከሰው እስከ ከብት ድረስ በኩርን ሁሉ እገድላለሁ፤ በግብጽም አማልክት ሁሉ ላይ እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔ ጌታ ነኝ። ደሙም በምትኖሩባቸው ቤቶች ምልክት ይሆንላችኋል፤ ደሙንም ባየሁ ጊዜ ከእናንተ አልፋለሁ፤ እኔም የግብጽን ምድር በመታሁ ጊዜ መቅሰፍቱ ለጥፋት አይመጣባችሁም። ይህም ቀን መታሰቢያ ይሁናችሁ፥ በዓል አድርጋችሁ ጠብቁት፥ ለጌታ በዓል ነው፤ ለትውልዳችሁ ለዘለዓለም ሥርዓት አድርጋችሁ ትጠብቁታላችሁ። ሰባት ቀን ያልቦካ ቂጣ ትበላላችሁ፤ በመጀመሪያው ቀን ከቤቶቻችሁ እርሾ ታስወግዳላችሁ፤ ከመጀመሪያውም ቀን አንሥቶ እስከ ሰባተኛው ቀን የቦካ የሚበላ ያቺ ነፍስ ከእስራኤል ተለይታ ትጥፋ። በመጀመሪያውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ እንዲሁም በሰባተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሆንላችኋል። ለሁሉም ሰው የሚሆን የሚበላ ካልሆነ በቀር በእነርሱ ቀናት ምንም አትሥሩ፥ ይህንም ብቻ ታደርጋላችሁ። በዚህም ቀን ሠራዊታችሁን ከግብጽ ምድር አውጥቼአለሁና የቂጣውን በዓል ጠብቁት፤ እንግዲህ ይህን ቀን በትውልዳችሁ ለዘለዓለም ሥርዓት ትጠብቃላችሁ። በመጀመሪያው ወር ከወሩም በዓሥራ አራተኛው ቀን ምሽት እስከ ከወሩ ሀያ አንድ ቀን ምሽት ድረስ ያልቦካ ቂጣ ትበላላችሁ። ሰባት ቀን በቤታችሁ እርሾ አይገኝ፤ እርሾ ያለበትንም እንጀራ የሚበላ ነፍስ፥ ከመጻተኛው ጀምሮ እስከ አገሩ ተወላጅ ድረስ፥ ከእስራኤል ማኅበር ተለይቶ ይወገድ። እርሾ ያለበትን ምንም አትብሉ፥ በምትኖሩበትም ቦታ ሁሉ ያልቦካ ቂጣ ብሉ።” ሙሴም የእስራኤልን ሽማግሌዎች ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “ሂዱ ለራሳችሁና ለቤተሰቦቻችሁ በግ ውሰዱ፥ ለፋሲካም እረዱት። ከሂሶጵ ቅጠልም ጭብጥ ውሰዱ፥ በዕቃ ውስጥ ባለው ደም ውስጥ ንከሩት፥ በዕቃውም ውስጥ ካለው ደም ጉበኖችንና ሁለቱን መቃኖች ቀቡ፤ ከእናንተም ማንም ሰው እስኪ ነጋ ድረስ ከቤቱ ደጅ አይውጣ። ጌታ ግብጽን ሊመታ ያልፋል፤ ደሙንም በጉበኖቹና በሁለቱ መቃኖች ላይ ያያል፥ ጌታም በበሩ ያልፋል፥ አጥፊውም ሊመታችሁ ወደ ቤታችሁ እንዲገባ አይፈቅድም። ይህንን ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ለዘለዓለም ሥርዓት አድርጋችሁ ጠብቁት። እንዲህም ይሆናል፥ ጌታ እንደ ተናገረ ወደሚሰጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ ይህንን አገልግሎት ጠብቁት። እንዲህም ይሆናል፤ ልጆቻችሁ፦ ‘ይህ አገልግሎት ለእናንተ ምንድነው?’ ባሉአችሁ ጊዜ፥ እናንተም፦ ‘ለጌታ የፋሲካ መሥዋዕት ነው፥ በግብጽ በእስራኤል ልጆች ቤቶች ላይ አልፎ ግብፃዊያንን በመታ ጊዜ፥ ቤቶቻችንን ያዳነበት ነው’ ትሉአቸዋላችሁ።” ሕዝቡም ተጎነበሱ ሰገዱም። የእስራኤልም ልጆች ሄዱ፥ እንዲሁም አደረጉ፤ ጌታ ሙሴንና አሮንን እንዳዘዘ እንዲሁ አደረጉ። እንዲህም ሆነ እኩለ ሌሊት ላይ ጌታ በግብጽ ምድር ያለውን በኩር ሁሉ፥ በዙፋን ከተቀመጠው ከፈርዖን በኩር ጀምሮ በእስር ቤት እስካሉት እስከ እስረኞች በኩር ድረስ፥ የከብቶችንም በኩር ሁሉ መታ። ፈርዖን፥ አገልጋዮቹ ሁሉና ግብጽ ሁሉ በሌሊት ተነሡ፤ የሞተ የሌለበት ቤት አልነበረምና በግብጽ ምድር ታላቅ ልቅሶ ሆነ። ሙሴንና አሮንን በሌሊት ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የእስራኤልም ልጆች ተነሡ፥ ከሕዝቤ መካከል ውጡ፤ ሂዱም፤ እንዳላችሁትም ጌታን አገልግሉ፤ እንዳላችሁትም መንጎቻችሁንና ከብቶቻችሁን ውሰዱ፥ ሂዱም፥ እኔንም ደግሞ ባርኩኝ።” ግብፃውያንም ፈጥነው ከምድሩ እንዲወጡ ሕዝቡን ያስቸኩሉአቸው ነበር፥ “ሁላችንም ልንሞት ነው” አሉ። ሕዝቡም ሊጡን ሳይቦካ ተሸከሙ፥ ማቡኪያውንም በልብሳቸው ጠቅልለው በትከሻቸው ተሸከሙት።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}