የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ዘፀአት 12:1-34

ዘፀአት 12:1-34 NASV

እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን በግብጽ እንዲህ አላቸው፤ “ይህ ወር ለእናንተ የወር መጀመሪያ፣ የዓመቱም መጀመሪያ ይሁንላችሁ። ለመላው የእስራኤል ሕዝብ ይህን ንገሩ፤ ይህ ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን እያንዳንዱ ሰው አንዳንድ ጠቦት ለቤተ ሰቡ፣ አንዳንድ ጠቦት ለአባቱ ቤት ያዘጋጅ። ማንኛውም ቤተ ሰብ ለአንድ ሙሉ ጠቦት ቍጥሩ አነስተኛ ከሆነ፣ በጎረቤት ያሉትን ሰዎች ቍጥር እስከ ቅርብ ከሆነው ጋራ መካፈል ይኖርበታል፤ እያንዳንዱ ሰው በሚበላው መጠንም ምን ያህል ጠቦት እንደሚያስፈልግ መወሰን ይኖርባችኋል። የምትመርጡት ጠቦት በግ ወይም ፍየል ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ምንም ነቀፋ የሌለበትና አንድ ዓመት የሞላው ተባዕት መሆን አለበት። ወሩ በገባ እስከ ዐሥራ አራተኛው ቀን ድረስ ጠብቋቸው። በዚያ ምሽት ጀምበር ስትጠልቅ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ይረዷቸው። ከዚያም ከደሙ ወስደው የጠቦቶቹ ሥጋ የሚበላበትን የእያንዳንዱን ቤት ደጃፍ መቃንና ጕበን ይቀቡ። ሥጋውንም በዚያችው ሌሊት በእሳት ላይ ጠብሰው ከመራራ ቅጠልና ከቂጣ ጋራ ይብሉት። ጥሬውን ሥጋ ወይም ቅቅሉን አትብሉ፤ ነገር ግን ጭንቅላቱን፣ እግሮቹንና ሆድ ዕቃውን በእሳት ላይ ጠብሳችሁ ብሉት። ከሥጋው ተርፎ አይደር፤ ያደረ ቢኖር ግን በእሳት ይቃጠል። ስትበሉም ልብሳችሁን ለብሳችሁ፣ በዐጭር ታጥቃችሁ፣ ጫማችሁን አድርጋችሁ በትራችሁን ይዛችሁ በጥድፊያ ብሉት፤ የእግዚአብሔር ፋሲካ ነው። “እኔም በዚያች ሌሊት በግብጽ ምድር ላይ ዐልፋለሁ፤ ከሰውም ከእንስሳም የተወለደውን የበኵር ልጅ ሁሉ እገድላለሁ፤ የግብጽን አማልክት ሁሉ እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። ደሙም ያላችሁበትን ቤት ለይቶ የሚያሳይ ምልክት ይሆንላችኋል፤ እኔ ደሙን በማይበት ጊዜ እናንተን ዐልፋለሁ፤ ግብጽን ስቀጣ መቅሠፍቱ አይደርስባችሁም። “ይህን ቀን መታሰቢያ ታደርጉታላችሁ፤ በሚቀጥሉት ትውልዶች ሁሉ ቋሚ ሥርዐት ሆኖ የእግዚአብሔር በዓል አድርጋችሁ አክብሩት። ለሰባት ቀናት እርሾ የሌለበት ቂጣ ብሉ። በመጀመሪያው ቀን እርሾን ሁሉ ከቤታችሁ አስወግዱ፤ በእነዚህ ሰባት ቀናት እርሾ ያለበትን ቂጣ የበላ ማንኛውም ሰው ከእስራኤል ይወገድ። በመጀመሪያውና በሰባተኛው ቀን የተቀደሰ ጉባኤ አድርጉ። በእነዚህ ቀናት ምንም ዐይነት ሥራ አትሥሩ፤ የምትሠሩት ሥራ ቢኖር ለእያንዳንዱ ምግብ ማዘጋጀት ብቻ ይሆናል። “የቂጣን በዓል አክብሩ፤ ሰራዊታችሁን ከግብጽ ምድር ያወጣሁት በዚች ዕለት ነውና። ይህን ዕለት ለሚቀጥለው ትውልድ ቋሚ ሥርዐት በማድረግ አክብሩት። ከመጀመሪያው ወር ከዐሥራ አራተኛው ቀን ምሽት እስከ ሃያ አንደኛው ቀን ምሽት ድረስ ቂጣ ትበላላችሁ። ለሰባት ቀን እርሾ በቤታችሁ አይኑር፤ መጻተኛም ሆነ የአገር ተወላጅ እርሾ ያለበትን ቂጣ የበላ ከእስራኤል ማኅበር ይወገድ። እርሾ ያለበትን ምንም ነገር አትብሉ፤ በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ቂጣ ነው መብላት ያለባችሁ።” ከዚያም ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ አለቆች በሙሉ አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ቶሎ ሄዳችሁ ለየቤተ ሰቦቻችሁ የሚሆን ጠቦት መርጣችሁ የፋሲካን በግ ዕረዱ። ከዚያም ጭብጥ የሂሶጵ ቅጠል በመውሰድ፣ በሳሕን ውስጥ ካለው ደም ነክራችሁ የየቤቶቻችሁን ጕበንና ግራ ቀኝ መቃኑን ቀቡ። ከእናንተ አንድም ሰው እስኪነጋ ድረስ ከቤቱ አይውጣ። እግዚአብሔር ግብጻውያንን ለመቅሠፍ በምድሪቱ ላይ በሚያልፍበት ጊዜ በጕበኑና በመቃኑ ላይ ያለውን ደም ሲያይ ያን ደጃፍ ዐልፎ ይሄዳል፤ ቀሣፊውም ወደ ቤታችሁ ገብቶ እንዳይገድላችሁ ይከለክለዋል። “እናንተም ሆነ ልጆቻችሁ ይህን መመሪያ ቋሚ ሥርዐት አድርጋችሁ ትታዘዛላችሁ። እግዚአብሔር እሰጣችኋለሁ ብሎ በገባው ቃል መሠረት ወደ ምድሪቱ ስትገቡ ይህን ሥርዐት ጠብቁ። ልጆቻችሁ ስለ ሥርዐቱ ምንነት ሲጠይቋችሁ፣ ‘ግብጻውያንን በቀሠፈ ጊዜ፣ በግብጽ ምድር የእስራኤላውያንን ቤት ዐልፎ በመሄድ ቤታችንን ላተረፈ፣ ለእግዚአብሔር የፋሲካ መሥዋዕት ነው’ ብላችሁ ንገሯቸው።” ከዚያም ሕዝቡ አጐነበሱ፤ ሰገዱም። እስራኤላውያንም እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዳዘዛቸው አደረጉ። እኩለ ሌሊት ላይ እግዚአብሔር በግብጽ ምድር በዙፋን ላይ ከተቀመጠው ከፈርዖን የበኵር ልጅ ጀምሮ፣ በጨለማ እስር ቤት ውስጥ እስካለው እስረኛ የበኵር ልጅ ድረስ ያለውንና የእንስሳቱን በኵሮች ሁሉ ቀሠፋቸው። ፈርዖን፣ ሹማምቱና የግብጽ ሕዝብ በሙሉ ሌሊቱን ከመኝታቸው ተነሡ፤ እነሆ በመላዪቱ ግብጽ ልቅሶና ዋይታ ነበር፤ ሰው ያልሞተበት አንድም ቤት አልነበረምና። ፈርዖን ሙሴንና አሮንን ሌሊቱን አስጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ተነሡ፤ እናንተና እስራኤላውያን ከሕዝቤ መካከል ውጡ፤ ሂዱ፤ በጠየቃችሁት መሠረት እግዚአብሔርን አምልኩ፤ እንዳላችሁት የበግና የፍየል መንጋችሁን፣ የቀንድና የጋማ ከብቶቻችሁን ይዛችሁ ሂዱ፤ እኔንም ባርኩኝ።” ግብጻውያን አገራቸውን በአስቸኳይ ለቅቀው እንዲወጡላቸው እስራኤላውያንን አጣደፏቸው። “አለዚያማ ሁላችንም ማለቃችን ነው” አሉ። ስለዚህ ሕዝቡ ያልቦካውን ሊጥ በየቡሖ ዕቃው አድርገው በጨርቅ ጠቅልለው በትከሻቸው ተሸከሙ።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}