የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘፀአት 12

12
የመጀመሪያው ፋሲካ
1 # ዘሌ. 23፥5፤ ዘኍ. 9፥1-5፤ 28፥16፤ ዘዳ. 16፥1፤2። ጌታም በግብጽ ምድር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ 2“ይህ ወር የወሮች መጀመሪያ ይሁናችሁ፤ ከዓመቱ ወሮችም የመጀመሪያ ይሁናችሁ። 3ለእስራኤል ልጆች ማህበር ሁሉ እንዲህ ብላችሁ ንገሩ። በዚህ ወር በአሥረኛው ቀን ሰው ሁሉ ለአባቱ ቤት አንድ ጠቦት፥ ለአንድ ቤትም አንድ ጠቦት ይውሰድ። 4የቤተሰቡ ቍጥር ም ለጠቦቱ የሚያንስ ከሆነ እርሱና ለቤቱ የቀረበው ጎረቤቱ በእያንዳንዱ ሰው ቍጥር አንድ ጠቦት ይውሰድ፤ እያንዳንዱም እንደሚበላው መጠን ከጠቦቱ ይካፈሉ። 5የእናንተ ጠቦት ነውር የሌለበት፥ ተባዕት፥ የአንድ ዓመት ይሁን፤ ከበጎች ወይም ከፍየሎች ውሰድ። 6በዚህም ወር እስከ ዐሥራ አራተኛው ቀን ድረስ ጠብቁት፤ የእስራኤልም ማኅበር ጉባኤ ሁሉ ሲመሽ ይረዱት። 7ከደሙም ጥቂት ወስደው በሚበሉበት ቤት ሁለቱን መቃንና ጉበኑን ይቀቡት። 8ሥጋውን በዚያች ሌሊት ይብሉ፤ በእሳት የተጠበሰውን ካልቦካ ቂጣና ከመራራ ቅጠል ጋር ይብሉት። 9ጥሬውን ወይም በውኃ የበሰለውን አትብሉ፥ ነገር ግን ራሱ፥ ከእግሮቹና ከሆድ ዕቃው ጋር በእሳት የተጠበሰውን ብሉት። 10ከእርሱም እስከ ጥዋት አንዳች አታስቀሩ፤ እስከ ጥዋት የቀረውንም በእሳት አቃጥሉት። 11እንግዲህ ወገቦቻችሁን ታጥቃችሁ፥ ጫማችሁን በእግራችሁ፥ በትራችሁንም በእጃችሁ አድርጋችሁ ብሉት፥ ፈጥናችሁም ብሉት፤ ለጌታ ፋሲካ ነው። 12እኔም በዚያች ሌሊት በግብጽ ምድር አልፋለሁ፥ በግብጽም ምድር ከሰው እስከ ከብት ድረስ በኩርን ሁሉ እገድላለሁ፤ በግብጽም አማልክት ሁሉ ላይ እፈርድባቸዋለሁ፤ እኔ ጌታ ነኝ። 13ደሙም በምትኖሩባቸው ቤቶች ምልክት ይሆንላችኋል፤ ደሙንም ባየሁ ጊዜ ከእናንተ አልፋለሁ፤ እኔም የግብጽን ምድር በመታሁ ጊዜ መቅሰፍቱ ለጥፋት አይመጣባችሁም። 14#ዘፀ. 23፥15፤ 34፥18፤ ዘሌ. 23፥6-8፤ ዘኍ. 28፥17-25፤ ዘዳ. 16፥3-8።ይህም ቀን መታሰቢያ ይሁናችሁ፥ በዓል አድርጋችሁ ጠብቁት፥ ለጌታ በዓል ነው፤ ለትውልዳችሁ ለዘለዓለም ሥርዓት አድርጋችሁ ትጠብቁታላችሁ። 15ሰባት ቀን ያልቦካ ቂጣ ትበላላችሁ፤ በመጀመሪያው ቀን ከቤቶቻችሁ እርሾ ታስወግዳላችሁ፤ ከመጀመሪያውም ቀን አንሥቶ እስከ ሰባተኛው ቀን የቦካ የሚበላ ያቺ ነፍስ ከእስራኤል ተለይታ ትጥፋ። 16በመጀመሪያውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ እንዲሁም በሰባተኛውም ቀን የተቀደሰ ጉባኤ ይሆንላችኋል። ለሁሉም ሰው የሚሆን የሚበላ ካልሆነ በቀር በእነርሱ ቀናት ምንም አትሥሩ፥ ይህንም ብቻ ታደርጋላችሁ። 17በዚህም ቀን ሠራዊታችሁን ከግብጽ ምድር አውጥቼአለሁና የቂጣውን በዓል ጠብቁት፤ እንግዲህ ይህን ቀን በትውልዳችሁ ለዘለዓለም ሥርዓት ትጠብቃላችሁ። 18በመጀመሪያው ወር ከወሩም በዓሥራ አራተኛው ቀን ምሽት እስከ ከወሩ ሀያ አንድ ቀን ምሽት ድረስ ያልቦካ ቂጣ ትበላላችሁ። 19ሰባት ቀን በቤታችሁ እርሾ አይገኝ፤ እርሾ ያለበትንም እንጀራ የሚበላ ነፍስ፥ ከመጻተኛው ጀምሮ እስከ አገሩ ተወላጅ ድረስ፥ ከእስራኤል ማኅበር ተለይቶ ይወገድ። 20እርሾ ያለበትን ምንም አትብሉ፥ በምትኖሩበትም ቦታ ሁሉ ያልቦካ ቂጣ ብሉ።”
21ሙሴም የእስራኤልን ሽማግሌዎች ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “ሂዱ ለራሳችሁና ለቤተሰቦቻችሁ በግ ውሰዱ፥ ለፋሲካም እረዱት። 22ከሂሶጵ ቅጠልም ጭብጥ ውሰዱ፥ በዕቃ ውስጥ ባለው ደም ውስጥ ንከሩት፥ በዕቃውም ውስጥ ካለው ደም ጉበኖችንና ሁለቱን መቃኖች ቀቡ፤ ከእናንተም ማንም ሰው እስኪ ነጋ ድረስ ከቤቱ ደጅ አይውጣ። 23#ዕብ. 11፥28።ጌታ ግብጽን ሊመታ ያልፋል፤ ደሙንም በጉበኖቹና በሁለቱ መቃኖች ላይ ያያል፥ ጌታም በበሩ ያልፋል፥ አጥፊውም ሊመታችሁ ወደ ቤታችሁ እንዲገባ አይፈቅድም። 24ይህንን ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ለዘለዓለም ሥርዓት አድርጋችሁ ጠብቁት። 25እንዲህም ይሆናል፥ ጌታ እንደ ተናገረ ወደሚሰጣችሁ ምድር በገባችሁ ጊዜ ይህንን አገልግሎት ጠብቁት። 26እንዲህም ይሆናል፤ ልጆቻችሁ፦ ‘ይህ አገልግሎት ለእናንተ ምንድነው?’ ባሉአችሁ ጊዜ፥ 27እናንተም፦ ‘ለጌታ የፋሲካ#12፥27 በዕብራይስጡ ፔሳኽ ፋሲካ ማለት ሲሆን፥ ፓሳኽ ማለት ደግሞ አለፈ ማለት ነው። መሥዋዕት ነው፥ በግብጽ በእስራኤል ልጆች ቤቶች ላይ አልፎ ግብፃዊያንን በመታ ጊዜ፥ ቤቶቻችንን ያዳነበት ነው’ ትሉአቸዋላችሁ።” ሕዝቡም ተጎነበሱ ሰገዱም። 28የእስራኤልም ልጆች ሄዱ፥ እንዲሁም አደረጉ፤ ጌታ ሙሴንና አሮንን እንዳዘዘ እንዲሁ አደረጉ።
10. የግብፃውያን የበኩር ልጆች ሞት
29 # ዘፀ. 4፥22፤23። እንዲህም ሆነ እኩለ ሌሊት ላይ ጌታ በግብጽ ምድር ያለውን በኩር ሁሉ፥ በዙፋን ከተቀመጠው ከፈርዖን በኩር ጀምሮ በእስር ቤት እስካሉት እስከ እስረኞች በኩር ድረስ፥ የከብቶችንም በኩር ሁሉ መታ። 30ፈርዖን፥ አገልጋዮቹ ሁሉና ግብጽ ሁሉ በሌሊት ተነሡ፤ የሞተ የሌለበት ቤት አልነበረምና በግብጽ ምድር ታላቅ ልቅሶ ሆነ። 31ሙሴንና አሮንን በሌሊት ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ የእስራኤልም ልጆች ተነሡ፥ ከሕዝቤ መካከል ውጡ፤ ሂዱም፤ እንዳላችሁትም ጌታን አገልግሉ፤ 32እንዳላችሁትም መንጎቻችሁንና ከብቶቻችሁን ውሰዱ፥ ሂዱም፥ እኔንም ደግሞ ባርኩኝ።”
ከራዓምሴስ ወደ ሱኮት መውጣት
33ግብፃውያንም ፈጥነው ከምድሩ እንዲወጡ ሕዝቡን ያስቸኩሉአቸው ነበር፥ “ሁላችንም ልንሞት ነው” አሉ። 34ሕዝቡም ሊጡን ሳይቦካ ተሸከሙ፥ ማቡኪያውንም በልብሳቸው ጠቅልለው በትከሻቸው ተሸከሙት። 35#ዘፀ. 3፥21፤22።የእስራኤልም ልጆች እንደ ሙሴ ቃል አደረጉ፥ ከግብፃውያንም የብርንና የወርቅን ዕቃ ልብስንም ለመኑ። 36ጌታም ለሕዝቡ በግብፃውያን ፊት ሞገስን ሰጣቸው እነርሱም የፈለጉትን ሰጡአቸው። እነርሱም ግብጽን በዘበዙ።
37የእስራኤልም ልጆች ከራዓምሴስ ወደ ሱኮት በእግር ተጓዙ፤ ከሕፃናቱም ሌላ ስድስት መቶ ሺህ ሰው የሚያህሉ ነበሩ። 38ደግሞም ሌላ ብዙ ድብልቅ ሕዝብ መንጎችና ላሞችም እጅግ ብዙም ከብቶች ከእነርሱ ጋር ወጡ። 39ከግብጽም ከእነርሱ ጋር ያወጡትን ሊጥ ጋገሩ፥ አልቦካም ነበርና ቂጣ አደረጉት፤ ግብፃውያን በመውጣት ስላስቸኮሉአቸው ይቆዩ ዘንድ አልተቻላቸውም፥ ስንቅም አላሰናዱም ነበር።
40 # ዘፍ. 15፥13፤ ገላ. 3፥17። የእስራኤልም ልጆች በግብጽ የኖሩበት ጊዜ አራት መቶ ሠላሳ ዓመት ነበር። 41እንዲህም ሆነ አራት መቶ ሠላሳ ዓመት ከተፈጸመ በኋላ በዚህ ቀን የጌታ ሠራዊት ሁሉ ከግብጽ ምድር ወጡ። 42ከግብጽ ምድር ስላወጣቸው ለጌታ የተጠበቀች ሌሊት ናት፤ ይህች ሌሊት በእስራኤል ልጆች ሁሉ ዘንድ በትውልዳቸው ሁሉ ለጌታ የተጠበቀች ናት።
የፋሲካ ሥርዓት
43ጌታም ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፦ “ይህ የፋሲካ ሥርዓት ነው፤ ማንም እንግዳ ሰው ከእርሱ አይብላ። 44በብር የተገዛ የማንም ባርያ ቢኖር ከተገረዘ በኋላ ከእርሱ ይብላ። 45እንግዳና ደሞዝተኛ ግን ከእርሱ አይብላ። 46#ዘኍ. 9፥12፤ ዮሐ. 19፥36።በአንድ ቤት ይበላ፤ ከሥጋውም አንዳች ከቤት ወደ ውጭ አይውጣ፤ አጥንቱንም አትስበሩት። 47የእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ ያድርጉት። 48እንግዳ ሰውም በመካከላችሁ ቢቀመጥ ለጌታም ፋሲካን ሊያደርግ ቢፈልግ፥ እርሱና የእርሱ ወንዶች ሁሉ ይገረዙ ከዚያም ይቅረብ ያድርግም፤ እንደ አገሩ ተወላጅም ይሆናል፤ ያልተገረዘ ሁሉ ግን ከእርሱ አይብላ። 49ለአገሩ ተወላጅና በእናንተ መካከልም ለሚቀመጡ መጻተኞች አንድ ሥርዓት ይሆናል።” 50የእስራኤልም ልጆች ሁሉ እንዲህ አደረጉ፤ ጌታ ሙሴንና አሮንን እንዳዘዘ እንዲሁ አደረጉ። 51በዚያም ቀን ጌታ የእስራኤልን ልጆች ከሠራዊታቸው ጋር ከግብጽ ምድር አወጣ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ