የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ወደ ኤፌሶን ሰዎች 5:20-33

ወደ ኤፌሶን ሰዎች 5:20-33 መቅካእኤ

ሁልጊዜ ስለ ሁሉ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አምላካችንንና አባታችንን ስለ ሁሉ አመስግኑ። እያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ። ሚስቶች ሆይ! ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ፤ ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደሆነ እርሱም አካሉን የሚያድን እንደሆነ ባል የሚስት ራስ ነው። ዳሩ ግን ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ እንዲሁ ሚስቶች ደግሞ በሁሉ ለባሎቻቸው ይገዙ። ባሎች ሆይ! ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ስለ እርሷ ራሱን አሳልፎ እንደሰጣት፥ ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ ከውሃ መታጠብ ጋር በቃሉ አንጽቶ እንዲቀድሳት፥ እንዲሁም ጉድፍ ወይም የፊት መጨማደድ ወይም አንዳች እንከን ሳይገኝባት ቅድስትና ነውር የሌለባት አድርጎ ክብርት የሆነችን ቤተ ክርስቲያንን ለራሱ ሊያቀርባ እንደፈለገ፥ እንዲሁም ባሎች ደግሞ እንደገዛ አካላቸው አድርገው ሚስቶቻቸውን ሊወዱአቸው ይገባቸዋል። ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል፤ ማንም የራሱን እካል የሚጠላ ከቶ የለምና፤ ይመግበዋል፤ ይንከባከበውማል። ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን ያደረገው እንዲህ ነው፤ ምክንያቱም እኛ የአካሉ ክፍሎች ነን። “ስለዚህ ሰው አባቱንና እናቱን ይተዋል፤ ከሚስቱም ጋር ይተባበራል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።” ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፤ እኔ ግን ይህን ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን እናገራለሁ። ሆኖም ከእናንተ እያንዳንዱ የገዛ ሚስቱን እንደ ራሱ አድርጎ ይውደዳት፤ ሚስትም ባልዋን ታክብር።