የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ወደ ኤፌሶን ሰዎች 5:20-33

ወደ ኤፌሶን ሰዎች 5:20-33 አማ05

በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ስለ ሁሉ ነገር እግዚአብሔር አብን ዘወትር አመስግኑ። ለክርስቶስ ክብር ብላችሁ ከእናንተ እያንዳንዱ ለሌላው ይታዘዝ። ሚስቶች ሆይ! ለጌታ ኢየሱስ እንደምትታዘዙ ለባሎቻችሁ ታዘዙ፤ ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደ ሆነ ባልም የሚስቱ ራስ ነው፤ ደግሞም ክርስቶስ አካሉ ለሆነችው ቤተ ክርስቲያን አዳኝዋ ነው። ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትታዘዝ እንዲሁም ሚስቶች በሁሉ ነገር ለባሎቻቸው ይታዘዙ። ባሎች ሆይ! ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ራሱንም ስለ እርስዋ አሳልፎ እንደ ሰጠ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ ክርስቶስ ይህን ያደረገው ቤተ ክርስቲያንን ሊቀድሳት ፈልጎ ነው፤ የቀደሳትም በቃሉ አማካይነት በውሃ አጥቦ ነው። በዚህ ዐይነት ዕድፍ ወይም የፊት መጨማደድ ወይም ይህን የመሰለ ሌላ መጥፎ ነገር ሳይገኝባት ቅድስት፥ እንከን የሌለባትና ውብ አድርጎ ወደራሱ ያቀርባታል። እንዲሁም ባሎች የገዛ ራሳቸውን እንደሚወዱ ሚስቶቻቸውን መውደድ ይገባቸዋል፤ ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል። የገዛ ራሱን አካል የሚጠላ ማንም የለም፤ ይልቅስ ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን እንደሚያደርገው ዐይነት ራሱን ይመግባል፤ ይንከባከባልም። እኛም የክርስቶስ አካል ክፍሎች ነን፤ “በዚህ ምክንያት ሰው አባቱንና እናቱን ትቶ ከሚስቱ ጋር ይጣበቃል፤ ሁለቱም አንድ አካል ይሆናሉ” ተብሎአል። ይህ ምሥጢር ታላቅ ነው፤ ይህንንም የምለው ስለ ክርስቶስና ስለ ቤተ ክርስቲያን ምሳሌ አድርጌ ነው። ነገር ግን ይህ ነገር እናንተንም ይመለከታል፤ ስለዚህ ባል ሚስቱን እንደ ራሱ አድርጎ ይውደድ፤ ሚስትም ባልዋን ታክብር።