የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ኦሪት ዘዳግም 4

4
የእስራኤል ሕዝብ ታዛዦች እንዲሆኑ ሙሴ መምከሩ
1 # ዘዳ. 4፥45፤ 5፥1፤ 31፤ 6፥1፤ 17፤ 20፤ 11፥32፤ 12፥1፤ 26፥16። “አሁንም፥ እስራኤል ሆይ፥ እንድታደርጉአቸው በሕይወትም እንድትኖሩ፥ የአባቶቻችሁም አምላክ ጌታ ወደሚሰጣችሁ ምድር ገብታችሁ እንድትወርሱ፥ የማስተምራችሁን ሥርዓትና ሕግጋት ስሙ። 2#ዘዳ. 13፥1።እኔ ያዘዝኋችሁን የጌታ አምላካችሁን ትእዛዝ ትጠብቃላችሁ እንጂ ባዘዝኋችሁ ቃል ላይ አትጨምሩም፥ ከእርሱም አታጎድሉም። 3#ዘኍ. 25፥1-13፤ መዝ. 106፥28፤ ሆሴዕ 9፥10።የፌዖሩን ባዓልን የተከተሉትን ሰዎች ሁሉ ጌታ አምላካችሁ ከመካከላችሁ እንዳጠፋ፥ እግዚአብሔር በባዓል ፌዖር ያደረገውን ዐይኖቻችሁ አይተዋል። 4እናንተ ግን ጌታ አምላካችሁን የተከተላችሁ ሁላችሁ እስከ ዛሬ ድረስ በሕይወት ትኖራላችሁ።
5“እነሆ፥ እናንተ ገብታችሁ በምትወርሱአት ምድር ውስጥ እንዲህ እንድታደርጉ ጌታዬ አምላኬ እንዳዘዘኝ ሥርዓትንና ሕግጋትን አስተማርኋችሁ። 6#ዘዳ. 26፥5፤ ዘፍ. 12፥2፤ 18፥18፤ 46፥3፤ ዘፀ. 32፥10።ጠብቁአት አድርጉአትም፥ ይህችን ሥርዓት ሁሉ ሰምተው፦ ‘በእውነት ይህ ታላቅ ሕዝብ ጠቢብና አስተዋይ ሕዝብ ነው’ በሚሉ በአሕዛብ ፊት ጥበባችሁና ማስተዋላችሁ ይህ ነውና።
7 # 2ሳሙ. 7፥23። “እኛ በምንለምነው ጊዜ ሁሉ ጌታ አምላካችን ለእኛ ቅርብ እንደ ሆነው፥ የየትኛው ሌላ ታላቅ ሕዝብ ነው አምላኩ ለእርሱ ቅርብ የሆነለት? 8#ዘዳ. 4፥44።በዓይናችሁ ፊት ዛሬ እንዳኖርኩት እንደዚህ ሕግ ሁሉ ጽድቅ የሆነች ሥርዓትና ሕግጋት ያለው ታላቅ ሕዝብስ የት ይገኛል?
9 # ዘዳ. 6፥7፤20-25፤ 11፥19-21፤ 29፥28፤ 31፥12-13፤ መዝ. 78፥3-6። “ብቻ አስተውል፥ ነፍስህንም በትጋት ጠብቅ፤ ዐይኖችህ ያዩትን ነገር እንዳትረሳ፥ በሕይወትህም ዘመን ሁሉ ከልብህ እንዳይለይ፥ ለልጆችህም ለልጅ ልጆችህም አሳውቃቸው። 10በጌታ በአምላካችሁ ፊት በኮሬብ በቆማችሁበት ቀን፥ ጌታ፦ ‘ሕዝቡን ወደ እኔ ሰብስብ፥ በምድርም በሕይወት በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ እኔን መፍራት እንዲማሩ፥ ልጆቻቸውንም እንዲያስተምሩ፥ ቃሌን አሰማቸዋለሁ’ ብሎ በተናገረኝ ጊዜ፥ 11#ዘፀ. 19፥7—20፥21።እናንተም ቀርባችሁ ከተራራው በታች ቆማችሁ ነበር፥ እስከ ሰማይም ድረስ እሳት በተራራው ላይ ይነድድ ነበር፥ ጨለማም ደመናና ድቅድቅ ጨለማ ነበረ። 12#ዘዳ. 4፥33፤36፤ 5፥4።ጌታም በእሳት ውስጥ ሆኖ ተናገራችሁ፤ የቃሉን ድምፅ ሰማችሁ፥ ድምፅን ብቻ ነበር እንጂ መልክ አላያችሁም። 13#ዘዳ. 5፥6-21፤ 10፥4፤ ዘፀ. 20፥1-17፤ 24፥12፤ 31፥18፤ 34፥27-28።እንድታደርጉትም ያዘዛችሁን ቃል ኪዳኑን፥ ዓሥሩን ትእዛዝ፥ ገለጸላችሁ፤ በሁለት የድንጋይ ጽላቶች ላይም ጻፋቸው። 14ትወርሱአት ዘንድ ተሻግራችሁ በምትገቡባት ምድር የምታደርጉትን ሥርዓትና ሕግጋት እንዳስተምራችሁ ጌታ በዚያን ጊዜ አዘዘኝ።
ከጣዖት አምልኮ ስለ መራቅ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ
15“ጌታ በኮሬብ በእሳት ውስጥ ሆኖ በተናገራችሁ ጊዜ ምንም መልክ አላያችሁምና፥ ለነፍሳችሁ እጅግ ተጠንቀቁ፤ 16#ዘዳ. 5፥8፤ ዘፀ. 20፥4።የማናቸውንም መልክ በየትኛውም ምስል፥ በወንድ ይሁን በሴት መልክ፥ የተቀረጸውን ምስል ለራሳችሁ በማድረግ እንዳትረክሱ፥ 17በምድር ላይ ያለውን የማንኛውንም እንስሳ ምስል በክንፉ የሚበርና የማንኛውንም ወፍ ምስል፥ 18በምድርም ላይ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱትን፥ ከምድር በታች በውሃ ውስጥ የሚኖሩትን የዓሣ ሁሉ ምስል አታድርጉ። 19#ዘዳ. 17፥3፤ ኢዮብ 31፥26-28።ዐይኖችህን ወደ ሰማይ አንሥተህ፥ ጌታ አምላካችሁ ከሰማይ በታች ላሉት ሕዝቦች ሁሉ የሰጣቸውን፥ ፀሐይንና ጨረቃን ከዋክብትንም፥ የሰማይን ሠራዊት ሁሉ ባያችሁ ጊዜ፥ በመሳት እንዳትሰግዱላቸውና እንዳታመልኳቸው ተጠንቀቁ። 20#1ነገ. 8፥51፤ ኢሳ. 48፥10፤ ኤር. 11፥4።እናንተን ግን ጌታ ወስዶ፥ እንደ ዛሬው ሁሉ የርስቱ ሕዝብ እንድትሆኑለት፥ ከብረት እቶን ከግብጽ አውጥቷችኋል። 21#ዘዳ. 1፥37፤ 3፥26።በእናንተ ቃላት ምክንያት ጌታ እኔን ተቆጣኝ፤ ዮርዳኖስንም እንዳልሻገር ጌታ አምላካችሁ ርስት አድርጎ ወደሚሰጣችሁ ወደ መልካሚቱ ምድር እንዳልገባ ማለ። 22#ዘዳ. 3፥27፤ 34፥1-12፤ ኢያ. 1—12።እኔ በዚህች ምድር እሞታለሁና፥ ዮርዳኖስን አልሻገርም፥ እናንተ ግን ትሻገራላችሁ፥ ያችንም መልካሚቱን ምድር ትወርሳላችሁ። 23#ዘዳ. 4፥16፤ 9፥12-14፤ ዘፀ. 32፥1-10።ጌታ አምላካችሁ ከእናንተ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን እንዳትረሱ፥ ጌታ አምላካችሁም የከለከለውን በማናቸውም መልክ የተቀረጸውን ምስል እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ። 24#ዘዳ. 5፥9፤ 6፥15፤ 9፥3፤ ዘፀ. 24፥17፤ 34፥14።ጌታ እግዚአብሔር የሚበላ እሳት፥ ቀናተኛ አምላክ ነውና።
25 # ዘዳ. 28፥64-67። “ልጆችን የልጅ ልጆችንም በወለዳችሁ ጊዜ፥ በምድሪቱም ብዙ ዘመን በተቀመጣችሁ ጊዜ፥ ማናቸውም ቅርጽ የተቀረጸውን ምስል አድርጋችሁ ከረከሳችሁ፥ ታስቆጡትም ዘንድ በጌታ በአምላካችሁ ፊት ክፉ የሆነውን ነገር ከሠራችሁ፥ 26#ዘዳ. 30፥19፤ 31፥28፤ 32፥1፤ ኢሳ. 1፥2።ትወርሱአት ዘንድ ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ከምትገቡባት ምድር ፈጥናችሁ እንደምትጠፉ እኔ ዛሬ ሰማይንና ምድርን በእናንተ ላይ ለምስክርነት እጠራለሁ፥ ፈጽሞም ትጠፋላችሁ እንጂ ረጅም ዘመን አትኖሩባትም። 27ጌታም በአሕዛብ መካከል ይበትናችኋል፥ ጌታ በውስጣቸው በሚያኖራችሁ በአሕዛብ መካከልም ጥቂቶች ሆናችሁ ትቀራላችሁ። 28#ዘዳ. 28፥64፤ 29፥17፤ ዘሌ. 26፥30-39፤ መዝ. 115፥4-8፤ 135፥15-18፤ ኢሳ. 44፥9-20።በዚያም ማየትም ሆነ መስማት፥ መብላት ሆነ ማሽተት የማይችሉትን፥ በሰው እጅ ከእንጨትና ከድንጋይ የተሠሩትን አማልክት ታመልካላችሁ። 29#ዘዳ. 6፥5፤ ኤር. 29፥13-14።ነገር ግን ከዚያ ጌታ አምላካችሁን ትሻላችሁ፥ በሙሉ ልባችሁ በሙሉ ነፍሳችሁም የፈለጋችሁት እንደሆን ታገኙታላችሁ፤ 30ይህም ሁሉ በደረሰባችሁ ጊዜ፥ ስትጨነቁ፥ በዘመኑ ፍጻሜ ወደ አምላካችሁ ወደ ጌታ ትመለሳላችሁ፥ ቃሉንም ትሰማላችሁ። 31#ዘዳ. 31፥8፤ ዘፍ. 9፥9-17፤ 15፥18-21፤ 17፥1-21፤ ዘፀ. 34፥6-7።ጌታ እግዚአብሔር መሐሪ አምላክ ነውና አይተዋችሁም፥ አያጠፋችሁምም፤ ለአባቶቻችሁ የገባውን ቃል ኪዳኑን አይረሳም።
32“እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ ከፈጠረው ጊዜ ጀምሮ፥ ከሰማይ ዳር እስከ ዳርቻዋ ድረስ ከቶ እንዲህ ያለ ታላቅ ነገር ወይም እንደ እርሱ ያለ ተሰምቶ እንደሆነ ከአንተ በፊት የነበረውን የቀደመውን ዘመን ጠይቅ። 33#ዘዳ. 4፥36፤ 5፥24፤ 26፤ ዘፀ. 20፥19።እናንተን ከእሳት ውስጥ ሆኖ እንደ ተናገረው፥ የእግዚአብሔርን ድምፅ ሰምቶ በሕይወት መኖር የቻለ፥ ሌላ ሕዝብ ከቶ አለን? 34#ዘዳ. 7፥19፤ 26፥8፤ 29፥2፤ ዘፀ. 7፥3፤ 15፥3-10፤ ኤር. 32፥21።ወይስ በፈተና፥ በተአምራት፥ በድንቅ፥ በጦርነት፥ በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ፥ በሚያስፈራም ኃይል፥ በዐይናችሁ ፊት ጌታ አምላካችሁ እናንተን ከግብጽ ምድር እንዳወጣችሁ፥ አንድን ሕዝብ ከሌላ ሕዝብ መካከል ወስዶ የራሱ ሕዝብ ለማድረግ የሞከረ ሌላ አምላክ አለን? 35#ዘዳ. 4፥39፤ 32፥39፤ 1ነገ. 8፥60፤ ኢሳ. 43፥10-13፤ ኢዩ. 2፥27።ጌታም አምላካችሁ እንደሆነ እንድታውቁ ይህ ለእናንተ ተገልጧል፥ ከእርሱም ሌላ አምላክ የለም። 36ያስተምራችሁ ዘንድ ከሰማይ ድምፁን አሰማችሁ፥ በምድርም ላይ ታላቁን እሳቱን አሳያችሁ፥ ከእሳቱም መካከል የእርሱን ድምፅ ሰማችሁ።። 37አባቶቻችሁን ወድዶአልና ከእነርሱ በኋላ ዘራቸውን መረጠ፥ ከእናንተ ጋር ሆኖ በታላቅ ኃይሉ ከግብጽ አወጣችሁ። 38ዛሬ እንደ ሆነው ሁሉ፥ ከእናንተ የበረቱትን ታላላቆችን አሕዛብ በፊታችሁ እንዲያስወጣ፥ እናንተንም እንዲያስገባ፥ ምድራቸውንም ርስት አድርጎ ይሰጣችሁ ዘንድ ነው። 39#ዘዳ. 4፥35፤ 32፥39፤ 1ነገ. 8፥60፤ ኢሳ. 43፥10-13፤ ኢዩ. 2፥27።እንግዲህ፥ ጌታ በላይ በሰማይ በታችም በምድር አምላክ እንደሆነ፥ ሌላም እንደሌለ ዛሬ እወቁ፥ በልባችሁም ያዙት። 40#ዘዳ. 6፥3፤ 12፥28።ለእናንተ፥ ከእናንተም በኋላ ለልጆቻችሁ መልካም ይሆን ዘንድ፥ ጌታ አምላካችሁ ለዘለዓለም በሚሰጣችሁ ምድር ዕድሜአችሁ ይረዝም ዘንድ፥ እኔ ዛሬ የማዝዛችሁን ሥርዓቱንና ትእዛዙን ጠብቁ።”
ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ የመማፀኛ ከተሞች
41 # ዘዳ. 19፥1-13፤ ዘኍ. 35፥10-28፤ ኢያ. 20፥1-9። ከዚህ በኋላ ሙሴ ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ በስተ ምሥራቅ ሦስት ከተሞች በመለየት ከለለ፤ 42ይህንንም ማድረጉ ትናንት ከትናንት በስቲያም ከዚህ ቀድሞ ጠላትነት ሳይኖረው፥ ባልንጀራውን ሳያውቅ የገደለ፥ ገዳዩ ይሸሽባቸው ዘንድ፥ ከእነዚህም ከተሞች ወደ አንዲቱ ሸሽቶ በሕይወት እንዲኖር ነው። 43ከተሞቹም ለሮቤል ነገድ በምድረ በዳ በደልዳላ ስፍራ ያለ ቤጼር፥ ለጋድም ነገድ በገለዓድ ያለ ራሞት፥ ለምናሴም ነገድ በባሳን ያለ ጎላን ነበሩ።
ስለ ሕጉ የተሰጠ ማብራሪያ
44 # ዘዳ. 4፥8፤ 17፥18-19፤ 30፥10፤ 31፥11-12። ሙሴም በእስራኤል ልጆች ፊት ያኖራት ሕግ ይህች ናት። 45#ዘዳ. 4፥1፤ 5፥1፤ 31፤ 6፥1፤ 17፤ 20፤ 11፥32፤ 12፥1፤ 26፥16፤ መዝ. 25፥10።ከግብጽ በወጡ ጊዜ ሙሴ ለእስራኤል ልጆች የተናገረው ምስክርና ሥርዓት፥ ሕጎችም እነዚህ ናቸው። 46#ዘዳ. 2፥24—3፥29።ሙሴና የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ከወጡ በኋላ ድል በነሱት፥ በሐሴቦን ተቀምጦ በነበረው በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን ምድር፥ በቤተፌዖር አንጻር ባለው ሸለቆ በዮርዳኖስ ማዶ ያወጃቸው።#ዘዳ. 3፥29፤ 34፥6። 47እነርሱም የእርሱን ምድርና እንዲሁም በዮርዳኖስ ምሥራቅ የምትገኘውን ባሳንን ይገዛ የነበረውን የሌላውን አሞራዊ ንጉሥ የዖግን ምድር ወረሱ። 48በአርኖን ወንዝ ዳር ካለችው ከአሮዔር ጀምሮ እስከ ሲሪዮን ተራራ፥ ይህም ሔርሞን ድረስ፥ 49በምሥራቅ በኩል በዮርዳኖስ ማዶ ከፒስጋ ተራራ በታች ያለውን ዓረባ ሁሉ እስከ ዓረባ ባሕር ድረስ ወሰዱ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ