ኦሪት ዘዳግም 28:1-13

ኦሪት ዘዳግም 28:1-13 መቅካእኤ

“ለጌታ እግዚአብሔር ፍጹም ብትታዘዝና እኔ ዛሬ የምሰጥህን ትእዛዙን ሁሉ በጥንቃቄ ብትጠብቅ፥ ጌታ እግዚአብሔር በምድር ላይ ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ በላይ ከፍ ከፍ ያደርግሃል። የጌታ እግዚአብሔርን ቃል ብትታዘዝ፥ እነዚህ በረከቶች ሁሉ ይደርሱሃል፤ አይለዩህምም። “በከተማ ትባረካለህ፥ በዕርሻህም ትባረካለህ። “የማሕፀንህ ፍሬ፥ የምድርህ አዝመራ፥ የእንስሳትህ ግልገሎች፥ የከብትህ ጥጃ፥ የበግና የፍየል ግልገሎችህም ይባረካሉ። “እንቅብህና ቡሓቃህ ይባረካል። “ስትገባ ትባረካለህ፤ ስትወጣም ትባረካለህ። “ጌታ በአንተ ላይ የሚነሡ ጠላቶችህን በፊትህ እንዲሸነፉ ያደርጋቸዋል፤ በአንድ አቅጣጫ ይመጡብሃል፤ ነገር ግን በሰባት አቅጣጫም ከአንተ ይሸሻሉ። “ጌታ በጐተራህና እጅህ በነካው ሁሉ ላይ በረከቱን ይልካል። ጌታ እግዚአብሔር በሚሰጥህም ምድር ላይ ይባርክሃል። “የጌታ የእግዚአብሔርን ትእዛዞች የምትጠብቅና በመንገዱ የምትሄድ ከሆነ፥ እንደ ማለልህ ለእርሱ የተቀደሰ ሕዝብ አድርጎ ያቆምሃል። የምድር አሕዛብም ሁሉ በጌታ ስም መጠራትህን ያያሉ፤ ይፈሩሃልም። ጌታ ሊሰጥህ ለአባቶችህ በማለላቸው ምድር በሆድህ ፍሬ፥ በከብትህ ፍሬ፥ በእርሻህም ፍሬ፥ ብልጽግና ይሰጥሃል። ጌታ መልካሙን መዝገብ ሰማዩን ይከፍትልሃል፤ ለምድርህ በወቅቱ ዝናብን ይሰጣል፤ የእጅህንም ሥራ ሁሉ ይባርካል፤ አንተም ለብዙ አሕዛብ ታበድራለህ፥ አንተ ግን ከማንም አትበደርም። ጌታም ራስ እንጂ ጅራት አያደርግህም። ዛሬ የምሰጥህን የጌታ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ብትታዘዝ በጥንቃቄም ብትጠብቅ ሁልጊዜም በላይ እንጂ እታች አትሆንም።