ዘዳግም 28:1-13

ዘዳግም 28:1-13 NASV

ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በፍጹም ብትታዘዝና እኔ ዛሬ የምሰጥህን ትእዛዙን ሁሉ በጥንቃቄ ብትከተል፣ አምላክህ እግዚአብሔር በምድር ላይ ከሚኖሩ አሕዛብ ሁሉ በላይ ከፍ ያደርግሃል። አምላክህን እግዚአብሔርን ብትታዘዝ፣ እነዚህ በረከቶች ሁሉ ያንተ ይሆናሉ፤ አይለዩህምም። በከተማ ትባረካለህ፣ በዕርሻህም ትባረካለህ። የማሕፀንህ ፍሬ፣ የምድርህ አዝመራ፣ የእንስሳትህ ግልገሎች፣ የከብትህ ጥጃ፣ የበግና የፍየል ግልገሎችህም ይባረካሉ። እንቅብህና ቡሖ ዕቃህ ይባረካሉ። ስትገባ ትባረካለህ፤ ስትወጣም ትባረካለህ። እግዚአብሔር በአንተ ላይ የሚነሡ ጠላቶችህን በፊትህ እንዲሸነፉ ያደርጋቸዋል፤ በአንድ አቅጣጫ ይመጡብሃል፤ በሰባት አቅጣጫም ከአንተ ይሸሻሉ። እግዚአብሔር በጐተራህና እጅህ በነካው ሁሉ በረከቱን ይልካል። አምላክህ እግዚአብሔር በሚሰጥህም ምድር ላይ ይባርክሃል። የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዞች የምትጠብቅና በመንገዱ የምትሄድ ከሆነ፣ በመሐላ በሰጠህ ተስፋ መሠረት የተቀደሰ ሕዝቡ አድርጎ ያቆምሃል፤ ከዚያም የምድር አሕዛብ ሁሉ በእግዚአብሔር ስም መጠራትህን ያያሉ፤ ይፈሩሃልም። እግዚአብሔርም ሊሰጥህ ለአባቶችህ በማለላቸው ምድር በማሕፀንህ ፍሬ፣ በእንስሳትህም ግልገል፣ በምድርህም ሰብል የተትረፈረፈ ብልጽግና ይሰጥሃል። እግዚአብሔር ለምድርህ በወቅቱ ዝናብን ለመስጠትና የእጅህን ሥራ ሁሉ ለመባረክ፣ መልካሙን መዝገብ ሰማዩን ይከፍትልሃል፤ አንተም ለብዙ አሕዛብ ታበድራለህ እንጂ ከአንዳቸውም አትበደርም። እግዚአብሔርም ራስ እንጂ ጅራት አያደርግህም። ዛሬ የምሰጥህን የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በጥንቃቄ ብትጠብቅ፣ መቼውንም ቢሆን በላይ እንጂ ፈጽሞ በታች አትሆንም።