ኦሪት ዘዳግም 23:1-11

ኦሪት ዘዳግም 23:1-11 መቅካእኤ

“የተኰላሸ ወይም ብልቱም የተሰለበ ሰው ወደ ጌታ ጉባኤ አይግባ። “ከጋብቻ ውጪ የተወለደ ወደ ጌታ ጉባኤ አይግባ፤ እስከ ዐሥር ትውልድ ድረስ እንኳን ቢሆን ወደ ጌታ ጉባኤ አይግባ። “አሞናዊም ሆነ ሞዓባዊ ወይም ማናቸውም የእርሱ ዘር፥ እስከ ዐሥር ትውልድ እንኳን ቢሆን ወደ ጌታ ጉባኤ አይግባ። ምክንያቱም ከግብጽ ከወጣችሁ በኋላ በጉዞ ላይ በነበራችሁበት ጊዜ እህል ውሃ ይዘው አልተቀበሏችሁም፤ በመስጴጦምያ በምትገኘው በፐቶር ይኖር የነበረውን የቢዖርን ልጅ በለዓምም አንተን እንዲረግም በገንዘብ ገዝተውት ነበር። ነገር ግን ጌታ እግዚአብሔር በለዓምን መስማት አልፈለገም፥ ጌታ እግዚአብሔር ወድዶሃልና እርግማኑን በረከት አደረገልህ። በዘመንህ ሁሉ ለዘለዓለም ሰላምና ልማት ለእነርሱ አትሻ። “ኤዶማዊ ወንድምህ ነውና አትጸየፈው፥ ግብፃዊውንም በአገሩ ስደተኛ ነበርህና አትጸየፈው። ከእነርሱም በሦስተኛው ትውልድ የሚወለዱ ልጆች ወደ ጌታ ጉባኤ ይግቡ።” “ጠላቶችህን ልትወጋ በወጣህ ጊዜ ከክፉ ነገር ሁሉ ሰውነትህን ጠብቅ። ከእናንተ መካከል ሌሊት ዘር በማፍሰስ የረከሰ ሰው ቢኖር ከሰፈር ወደ ውጭ ይውጣ፥ እዚያው ይቆይ። በመሸም ጊዜ በውኃ ይታጠብ፥ ፀሐይም በገባ ጊዜ ወደ ሰፈር ይመለስ።