ወደ ቈላስይስ ሰዎች 2
2
1ስለ እናንተና በሎዶቅያ ስላሉት ፊቴንም አይተውት ስለማያውቁት ሰዎች ሁሉ ምን ያኽል እንደምጋደል እንድታውቁ እወዳለሁና፤ 2እንዲህም የምጋደለው ልባቸው እንዲጽናና፥ በፍቅርም በአንድነት እንዲተሳሰሩ፥ በፍጹም ማስተዋልም የሚገኘውን ባለጠግነት ሁሉ እንዲኖራቸው፥ የእግዚአብሔርንም ምሥጢር እርሱንም ክርስቶስን እንዲያውቁ ነው፤ 3የጥበብና የእውቀት ሀብት ሁሉ ተሰውሮ የሚገኘው በክርስቶስ ዘንድ ነውና። 4ይህንንም የምለው ማንም አሳማኝ በሚመስል ንግግር እንዳያታልላችሁ ብዬ ነው። 5በአካል ምንም እንኳ ብርቅ፥ በመንፈስ ከእናንተ ጋር ነኝና፤ መልካሙንም ሥነ ሥርዓታችሁንና በክርስቶስም ላይ ያላችሁን የእምነታችሁን ጽናት እያየሁ ደስ ይለኛል።
በክርስቶስ የሚገኝ የተሟላ ሕይወት
6እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ፤ 7አብዝታችሁ ምስጋናን በማቅረብ እንደ ተማራችሁት ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፤ በእምነትም ጽኑ። 8እንደ ክርስቶስ ትምህርት ሳይሆን እንደ ሰው ወግና እንደ መሠረታዊው የዓለም ረቂቅ መንፈስ በፍልስፍናና በከንቱ መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠንቀቁ። 9በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በአካል ተገልጦ ይኖራልና፤ 10የአለቅነትና የሥልጣን ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል። 11በክርስቶስ መገረዝ የሥጋዊውን አካል በመግፈፍ በሰው እጅ ባልተከናወነ መገረዝ በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ፤ 12#ሮሜ 6፥4።በጥምቀትም ከእርሱ ጋር ተቀብራችሁ፥ በጥምቀት ደግሞ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አሠራር በማመናችሁ ከእርሱ ጋር ተነሣችሁ። 13#ኤፌ. 2፥1-5።እናንተም በበደላችሁና ሥጋችሁን ባለመገረዝ ሞታችሁ የነበራችሁትን በደላችንን ሁሉ ይቅር ባለን ጊዜ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ፤ 14#ኤፌ. 2፥15።እርሱም ይፃረረንና ይቃወመን የነበረውን በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው፤ በመስቀልም ላይ ቸንክሮ ከእኛ አስወገደው፤ 15አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ በመስቀሉ ድል በመንሣት እነርሱን በይፋ አጋለጣቸው።
16 #
ሮሜ 14፥1-6። እንግዲህ በመብል ወይም በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለ ሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ፤ 17እነዚህ ወደ ፊት ለሚመጡት ነገሮች እንደ ጥላ ናቸውና፤ እውነቱ የሚገኘው ግን በክርስቶስ ነው። 18ራስን ማዋረድና የመላእክትን አምልኮ እየወደደ፥ ባየውም ራእይ ላይ በጽኑ እየተመረኮዘ፥ በሥጋዊም አእምሮ በከንቱ እየታበየ ማንም አይፍረድባችሁ፤ 19#ኤፌ. 4፥16።እንዲሁም እግዚአብሔር በሚሰጠው ማደግ የሚያድገውን አካል ሁሉ የሚንከባከበውን በመገጣጠምያዎቹና በጅማቶቹ አብሮ የሚያስተሳስረውን ራስ በጽኑ ሳይዝ ማንም አያውግዛችሁ።
በክርስቶስ የሚገኝ አዲስ ሕይወት
20ከመሠረታዊው የዓለም ረቂቅ መንፈስ ርቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ፥ ከዓለም እንዳልተለያችሁ ዓይነት ኑሮ ለምን ትኖራላችሁ? ለምንስ እንደነዚህ ላሉት ትእዛዞች ትገዛላችሁ? 21እነርሱም፦ “አትያዝ፥ አትቅመስ፥ አትንካ” የሚሉ ናቸው። 22እነዚህ ሁሉ ትእዛዛት በጥቅም ላይ በመዋላቸው የሚጠፉትን ነገሮች የሚጠቁሙ ናቸው፤ እንዲያው በቀላሉ የሰው ትእዛዛትና አስተምሮ ናቸው። 23እነዚህም በገዛ ፈቃድ የሚደረግ አምልኮንና ራስን ማዋረድ ሥጋንም የመጨቆን ጥበብ ያላቸው ይመስላሉ፤ ነገር ግን ሥጋ ያለ ልክ እንዳይጠግብ ለመከልከል ምንም አይጠቅሙም።
Currently Selected:
ወደ ቈላስይስ ሰዎች 2: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ