የሐዋርያት ሥራ 8:27-31

የሐዋርያት ሥራ 8:27-31 መቅካእኤ

ተነሥቶም ሄደ። እነሆም፥ ሕንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት ባለሥልጣን የነበረ በገንዘብዋም ሁሉ ኀላፊ አንድ ኢትዮጵያ ጃንደረባ ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር፤ ሲመለስም በሠረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር። መንፈስም ፊልጶስን “ወደዚህ ሠረገላ ቅረብና ተገናኝ፤” አለው። ፊልጶስም ሮጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰማና “በውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን?” አለው። እርሱም “የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል?” አለው። ወጥቶም ከእርሱ ጋር ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው።