የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሐዋርያት ሥራ 13

13
በርናባስና ሳውል ለወንጌል አገልግሎት በመንፈስ ቅዱስ እንደ ተመረጡ
1በአንጾኪያም ባለችው ቤተ ክርሲቲያን ነቢያትና መምህራን ነበሩ፤ እነርሱም በርናባስ፥ ኔጌር የተባለው ስምዖንም፥ የቀሬናው ሉክዮስም፥ የአራተኛው ክፍል ገዥ የሄሮድስም ባለምዋል ምናሔ፥ ሳውልም ነበሩ። 2እነዚህም ጌታን ሲያመልኩና ሲጦሙ መንፈስ ቅዱስ “በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ፤” አለ። 3በዚያን ጊዜም ከጦሙ ከጸለዩም እጃቸውንም ከጫኑ በኋላ አሰናበቱአቸው።
በርናባስና ጳውሎስ በቆጵሮስ እንደ ሰበኩ
4እነርሱም በመንፈስ ቅዱስ ተልከው ወደ ሴሌውቅያ ወረዱ፤ ከዚያም በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄዱ። 5በስልማናም በነበሩ ጊዜ በአይሁድ ምኵራቦች የእግዚአብሔርን ቃል ሰበኩ፤ አገልጋይም ዮሐንስ ነበራቸው። 6ደሴቲቱንም ሁሉ እስከ ጳፉ በዞሩ ጊዜ፥ በርያሱስ የሚሉትን ጠንቋይና ሐሰተኛ ነቢይ የሆነውን አንድ አይሁዳዊ ሰው አገኙ፤ 7እርሱም አስተዋይ ሰው ከሆነው ሰርግዮስ ጳውሎስ ከሚባለው አገረ ገዥ ጋር ነበረ። ይህም በርናባስንና ሳውልን ወደ እርሱ ጠርቶ የእግዚአብሔርን ቃል ሊሰማ ፈለገ። 8ጠንቋዩ ግን ኤልማስ፥ ስሙ እንዲሁ ይተረጐማልና፥ አገረ ገዡን ከማመን ሊያጣምም ፈልጎ ተቃወማቸው። 9ጳውሎስ የተባለው ሳውል ግን መንፈስ ቅዱስን ተሞልቶ ትኩር ብሎ ሲመለከተው 10“አንተ ተንኰል ሁሉ ክፋትም ሁሉ የሞላብህ፥ የዲያብሎስ ልጅ፥ የጽድቅም ሁሉ ጠላት፥ የቀናውን የጌታን መንገድ ከማጣመም አታርፍምን? 11አሁንም፥ እነሆ፥ የጌታ እጅ በአንተ ላይ ናት፤ ዕውርም ትሆናለህ እስከ ጊዜውም ፀሐይን አታይም፤” አለው። ያን ጊዜም ጭጋግና ጨለማ ወደቀበት፤ በእጁም የሚመራውን እየዞረ ፈለገ። 12በዚያን ጊዜ አገረ ገዢው የተደረገውን ባየ ጊዜ ከጌታ ትምህርት የተነሣ ተገርሞ አመነ።
በርናባስና ጳውሎስ በጲስድያ በምትገኘው በአንጾኪያ እንደ ሰበኩ
13ጳውሎስም ከጓደኞቹ ጋር ከጳፉ ተነሥቶ የጵንፍልያ ወደምትሆን ወደ ጴርጌን መጣ፤ ዮሐንስም ከእነርሱ ተለይቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። 14እነርሱ ግን ከጴርጌን አልፈው የጲስድያ ወደምትሆን ወደ አንጾኪያ ደረሱ፤ በሰንበትም ቀን ወደ ምኵራብ ገብተው ተቀመጡ። 15ሕግና ነቢያትም ከተነበቡ በኋላ የምኵራቡ አለቆች “ወንድሞች ሆይ! ሕዝብን የሚመክር ቃል እንዳላችሁ ተናገሩ፤” ብለው ላኩባቸው። 16ጳውሎስም ተነሣና በእጁ ጠቅሶ እንዲህ አለ “የእስራኤል ሰዎችና እግዚአብሔርን የምትፈሩት ሆይ! ስሙ። 17#ዘፀ. 1፥7፤ ዘፀ. 12፥51።የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ አባቶቻችንን መርጦ በግብጽ አገር በእንግድነት ሳሉ ሕዝቡን ከፍ ከፍ አደረጋቸው፤ ከፍ ባለችውም ክንዱ ከዚያ አወጣቸው። 18#ዘኍ. 14፥34፤ ዘዳ. 1፥31።በበረሃም አርባ ዓመት ያህል መገባቸው። 19#ዘዳ. 7፥1፤ ኢያ. 14፥1።በከነዓንም አገር ሰባት አሕዛብን አጥፍቶ ምድራቸውን አወረሳቸው። 20#መሳ. 2፥16፤ 1ሳሙ. 3፥20።ከዚህም በኋላ እስከ ነቢዩ እስከ ሳሙኤል ድረስ አራት መቶ አምሳ ዓመት ያህል መሳፍንትን ሰጣቸው። 21#1ሳሙ. 8፥5፤ 1ሳሙ. 10፥21።ከዚያም ወዲያ ንጉሥን ያነግሥላቸው ዘንድ ለመኑ፤ እግዚአብሔርም ከብንያም ወገን የሚሆን ሰው የቂስን ልጅ ሳኦልን አርባ ዓመት ሰጣቸው፤ 22#1ሳሙ. 13፥14፤ 1ሳሙ. 16፥12፤ መዝ. 89፥21።እርሱንም ከሻረው በኋላ ዳዊትን በእነርሱ ላይ እንዲነግሥ አስነሣው፤ ሲመሰክርለትም ‘እንደ ልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ፤’ አለ። 23ከዚህም ሰው ዘር እግዚአብሔር እንደ ተስፋው ቃል ለእስራኤል መድኃኒትን እርሱም ኢየሱስን አመጣ። 24#ማር. 1፥4፤ ሉቃ. 3፥3።ከመምጣቱ በፊት ዮሐንስ አስቀድሞ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ የንስሐን ጥምቀት ሰብኮ ነበር። 25#ዮሐ. 1፥20፤ ማቴ. 3፥11፤ ማር. 1፥7፤ ሉቃ. 3፥16፤ ዮሐ. 1፥20፤27።ዮሐንስም ሩጫውን ሲፈጽም ሳለ ‘እኔ ማን እንደሆንሁ ታስባላችሁ? እኔስ እርሱን አይደለሁም፤ ነገር ግን እነሆ፥ የእግሩን ጫማ እፈታ ዘንድ ከማይገባኝ ከእኔ በኋላ ይመጣል፤’ ይል ነበር።”
26እናንተ ወንድሞቻችን፥ የአብርሃም ዘር ልጆች ከእናንተ መካከልም እግዚአብሔርን የምትፈሩ ሆይ! ለእናንተ የዚህ የመዳን ቃል ተላከ። 27በኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሰዎችና አለቆቻቸው እርሱንና በየሰንበቱ የሚነበቡትን የነቢያትን ድምፆች ስላላወቁ በፍርዳቸው ፈጽመዋልና፤ 28#ማቴ. 27፥22፤23፤ ማር. 15፥13፤14፤ ሉቃ. 23፥21-23፤ ዮሐ. 19፥15።ለሞትም የሚያደርስ ምክንያት አንድ ስንኳ ባያገኙበት፥ ይገድለው ዘንድ ጲላጦስን ለመኑት፤ 29#ማቴ. 27፥57-61፤ ማር. 15፥42-47፤ ሉቃ. 23፥50-56፤ ዮሐ. 19፥38-42።ስለ እርሱም የተጻፈውን ሁሉ በፈጸሙ ጊዜ ከእንጨት አውርደው በመቃብር አኖሩት። 30እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው፤ 31#የሐዋ. 1፥3።በሕዝብም ዘንድ ምስክሮቹ ለሆኑት ከእርሱ ጋር ከገሊላ ወደ ኢየሩሳሌም ለወጡት ብዙ ቀን ታያቸው። 32#መዝ. 2፥7።እኛም ለአባቶች የተሰጠውን ተስፋ የምስራቹን ለእናንተ እንሰብካለን፤ 33ይህን ተስፋ እግዚአብሔር በሁለተኛው መዝሙር ደግሞ “አንተ ልጄ ነህ፤ እኔ ዛሬ ወለድሁህ፤” ተብሎ እንደ ተጻፈ፥ ኢየሱስን አስነሥቶ ለእኛ ለልጆቻቸው ፈጽሞአልና። 34#ኢሳ. 55፥3።እንደገናም ወደ መበስበስ እንዳይመለስ ከሙታን እንደ አስነሣው፥ እንዲህ “የታመነውን የዳዊትን ቅዱስ ተስፋ እሰጣችኋለሁ፤” ብሏል። 35#መዝ. 16፥10።ደግሞ በሌላ ስፍራ “ቅዱስህን መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም፤” ይላልና። 36ዳዊትም በራሱ ዘመን የእግዚአብሔርን አሳብ ካገለገለ በኋላ አንቀላፋ፤ ከአባቶቹም ጋር ተጨምሮ መበስበስን አየ፤ 37ይህ እግዚአብሔር ያስነሣው ግን መበስበስን አላየም። 38እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ የኀጢአት ይቅርታ የሚገኘው በኢየሱስ በኩል መሆኑ እንደ ተሰበከላችሁ ዕወቁ፤ 39በእርሱ የሚያምን ሁሉ በሙሴ ሕግ በኩል ማግኘት ያልተቻለውን ጽድቅ ያገኛል። 40#ዕን. 1፥5።ስለዚህ ነቢያት እንዲህ ብለው የተናገሩት እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ፤
41“እናንተ የምትንቁ፥ ተመልከቱ፤ ተደነቁም፤ ጥፉም፤
ማንም ቢተርክላችሁ የማታምኑትን
ሥራ በዘመናችሁ እኔ እሠራለሁና፤”
ተብሎ በነቢያት የተነገረው እንዳይደርስባችሁ ተጠንቀቁ።
42በወጡም ጊዜ ይህን ነገር በሚመጣው ሰንበት ይነግሩአቸው ዘንድ ለመኑአቸው። 43ጉባኤውም ከተፈታ በኋላ ከአይሁድና ወደ ይሁዲነት ገብተው ከሚያመልኩ ብዙዎች ጳውሎስንና በርናባስን ተከተሉአቸው፤ እነርሱም ሲነግሩአቸው በእግዚአብሔር ጸጋ ጸንተው እንዲኖሩ አስረዱአቸው።
44በሁለተኛውም ሰንበት ከጥቂቶቹ በቀር የከተማው ሰው ሁሉ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰሙ ዘንድ ተሰበሰቡ። 45አይሁድም ብዙ ሕዝብ ባዩ ጊዜ ቅንዓት ሞላባቸው፤ እየተሳደቡም ጳውሎስ የተናገረውን ቃል ተቃወሙ። 46ጳውሎስና በርናባስም ገልጠው “የእግዚአብሔር ቃል አስቀድሞ ለእናንተ ይነገር ዘንድ ያስፈልጋል፤ ከገፋችሁትና የዘለዓለም ሕይወት እንዳይገባችሁ በራሳችሁ ከፈረዳችሁ ግን፥ እነሆ፥ ወደ አሕዛብ ዘወር እንላለን። 47#ኢሳ. 42፥6፤ 49፥6።እንዲሁ ጌታ
“እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ለማዳን
ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ፤”
ብሎ አዞናልና፤ አሉ።
48አሕዛብም ሰምተው ደስ አላቸው፤ የእግዚአብሔርንም ቃል አከበሩ፤ ለዘለዓለም ሕይወትም የተዘጋጁ ሁሉ አመኑ፤ 49የጌታም ቃል በአገሩ ሁሉ ተስፋፋ። 50አይሁድ ግን የሚያመልኩትን የከበሩትንም ሴቶችና የከተማውን መኳንንት አወኩ፤ በጳውሎስና በበርናባስም ላይ ስደትን አስነሥተው ከአገራቸው አወጡአቸው። 51#ማቴ. 10፥14፤ ማር. 6፥11፤ ሉቃ. 9፥5፤ 10፥11።እነርሱ ግን የእግራቸውን ትቢያ አራግፈውባቸው ወደ ኢቆንዮን መጡ። 52በደቀ መዛሙርትም ደስታና መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ