የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

የሐዋርያት ሥራ 11

11
ጴጥሮስ ወደ አሕዛብ ቤት ለምን እንደ ገባ ማስረዳቱ
1ሐዋርያትና በይሁዳም የነበሩት ወንድሞች አሕዛብ ደግሞ የእግዚአብሔርን ቃል እንደ ተቀበሉ ሰሙ። 2ጴጥሮስም ወደ ኢየሩሳሌም በወጣ ጊዜ ከተገረዙት ወገን የሆኑት ሰዎች ከእርሱ ጋር ተከራክረው 3“ወዳልተገረዙ ሰዎች ገብተህ ከእነርሱ ጋር በላህ፤” አሉት። 4ጴጥሮስ ግን ከመጀመሪያው ጀምሮ በተራ ገለጠላቸው እንዲህም አለ 5“እኔ በኢዮጴ ከተማ ስጸልይ ሳለሁ ተመስጬ ራእይን አየሁ፤ ታላቅ ሸማ የመሰለ ዕቃ በአራት ማዕዘን ተይዞ ከሰማይ ወረደና ወደ እኔ መጣ፤ 6ይህንም ትኩር ብዬ ስመለከት አራት እግር ያላቸውን የምድር እንስሶች አራዊትንም ተንቀሳቃሾችንም የሰማይ ወፎችንም አየሁ። 7‘ጴጥሮስ ሆይ! ተነሣና አርደህ ብላ፤’ የሚለኝንም ድምፅ ሰማሁ። 8እኔም ‘ጌታ ሆይ! አይሆንም፤ ርኩስ ወይም የሚያስጸይፍ ከቶ ወደ አፌ ገብቶ አያውቅምና፤’ አልሁ። 9ሁለተኛም ‘እግዚአብሔር ያነጻውን አንተ አታርክሰው፤’ የሚል ድምፅ ከሰማይ መለሰልኝ። 10ይህም ሦስት ጊዜ ሆነ፤ እንደገናም ሁሉ ወደ ሰማይ ተሳበ። 11እነሆም፥ ያንጊዜ ሦስት ሰዎች ከቂሣርያ ወደ እኔ ተልከው ወዳለሁበት ቤት ቀረቡ። 12መንፈስም ሳልጠራጠር ከእነርሱ ጋር እሄድ ዘንድ ነገረኝ። እነዚህም ስድስቱ ወንድሞች ደግሞ ከእኔ ጋር መጡ፤ ወደዚያ ሰውም ቤት ገባን። 13እርሱም መልአክ በቤቱ ቆሞ እንዳየና ‘ወደ ኢዮጴ ሰዎች ልከህ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንን አስመጣ፤ 14እርሱም አንተና የቤትህ ሰዎች ሁሉ የምትድኑበትን ነገር ይነግርሃል፤’ እንዳለው ነገረን። 15ለመናገርም በጀመርሁ ጊዜ መንፈስ ቅዱስ ለእኛ ደግሞ በመጀመሪያ እንደ ወረደ ለእነርሱም ወረደላቸው። 16#የሐዋ. 1፥5።‘ዮሐንስ በውሃ አጠመቀ እናንተ ግን በመንፈስ ቅዱስ ትጠመቃላችሁ፤’ ያለውም የጌታ ቃል ትዝ አለኝ። 17እንግዲህ እግዚአብሔር በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላመነው ለእኛ ደግሞ እንደ ሰጠን ያን ስጦታ ለእነርሱ ከሰጠ፥ እግዚአብሔርን ለመከላከል እችል ዘንድ እኔ ማን ነበርሁ?” 18ይህን በሰሙ ጊዜም ዝም አሉና “እንኪያስ እግዚአብሔር ለአሕዛብ ደግሞ ለሕይወት የሚሆን ንስሐን ሰጣቸው፤” እያሉ እግዚአብሔርን አከበሩ።
ስለ አንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን
19 # የሐዋ. 8፥1-4። በእስጢፋኖስም ላይ በተደረገው መከራ የተበተኑት እስከ ፊንቄ እስከ ቆጵሮስም እስከ አንጾኪያም ድረስ ዞሩ፤ ቃሉንም ለአይሁድ ብቻ እንጂ ለአንድ ስንኳ አይናገሩም ነበር። 20ከእነርሱ ግን የቆጵሮስና የቀሬና ሰዎች የነበሩት አንዳንዶቹ ወደ አንጾኪያ መጥተው የጌታን የኢየሱስን ወንጌል እየሰበኩ ለግሪክ ሰዎች ተናገሩ። 21የጌታም እጅ ከእነርሱ ጋር ነበረ፤ ቁጥራቸውም እጅግ የሚሆን ሰዎች አምነው ወደ ጌታ ዘወር አሉ። 22ወሬውም በኢየሩሳሌም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ስለ እነርሱ ተሰማ፤ በርናባስንም ወደ አንጾኪያ ላኩት፤ 23እርሱም መጥቶ የእግዚአብሔርን ጸጋ ባየ ጊዜ ደስ አለው፤ ሁሉንም በልባቸው ፈቃድ በጌታ ጸንተው ይኖሩ ዘንድ መከራቸው፤ 24ደግ ሰውና መንፈስ ቅዱስ እምነትም የሞላበት ነበረና። ብዙ ሕዝብም ወደ ጌታ ተጨመሩ። 25በርናባስም ሳውልን ሊፈልግ ወደ ጠርሴስ ወጣ፤ 26ባገኘውም ጊዜ ወደ አንጾኪያ አመጣው። በቤተ ክርስቲያንም አንድ ዓመት ሙሉ ተሰበሰቡ፤ ብዙ ሕዝብንም አስተማሩ፤ ደቀ መዛሙርትም መጀመሪያ በአንጾኪያ ክርስቲያን ተባሉ።
27በዚያም ወራት ነቢያት ከኢየሩሳሌም ወደ አንጾኪያ ወረዱ፤ 28#የሐዋ. 21፥10።ከእነርሱም አጋቦስ የሚሉት አንድ ሰው ተነሥቶ በዓለም ሁሉ ታላቅ ራብ ሊሆን እንዳለው በመንፈስ አመለከተ፤ ይህም በቀላውዴዎስ ቄሣር ዘመን ሆነ። 29ደቀ መዛሙርትም እያንዳንዳቸው እንደ ችሎታቸው መጠን አዋጥተው በይሁዳ ለሚኖሩት ወንድሞች እርዳታን ይልኩ ዘንድ ወሰኑ፤ 30እንዲህም ደግሞ አደረጉ፤ በበርናባስና በሳውልም እጅ ወደ ሽማግሌዎቹ ላኩት።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ