2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 2:3-10

2ኛ ወደ ጢሞቴዎስ 2:3-10 መቅካእኤ

እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ መልካም ወታደር ሆነህ መከራን ተቀበል። በማገልገል ላይ ያለ ማንም ወታደር፥ ዐላማው ለወታደርነት የመለመለውን ሰው ለማስደሰት እስከሆነ ድረስ፥ እንደ ማናቸውም ሰው በዕለት ተዕለት ጉዳዮች አይጠመድም። እንዲሁም ደግሞ ማንም ሯጭ ውድድሩን እንደ ሕጉ ካልተወዳደረ የድሉን አክሊል አያገኝም። በርትቶ ለሚሠራው ገበሬ የፍሬው የመጀመሪያ ድርሻ ለእርሱ ሊሆን ይገባዋል። ጌታ በሁሉ ነገር ማስተዋልን ይሰጥሃልና የምለውን ደኅና አድርገህ አሰላስል። በወንጌል የምሰብከውን፥ ከሙታን የተነሣውን፥ ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስብ። ለዚህም ወንጌል ስል መከራን እቀበላለሁ፥ እንደ ወንጀለኛም በሰንሰለት እስከመታሰር ደርሻለሁ፤ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም። ስለዚህ በክርስቶስ ኢየሰሱስ ያለውን መዳን ከዘለዓለም ክብር ጋር እንዲያገኙ ስል ስለ ተመረጡት ደግሞ ሁሉን ነገር እታገሣለሁ።