2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 23
23
የዳዊት የመጨረሻ ቃል
1 #
1ነገ. 2፥1-9፤ ሲራ. 47፥8። የዳዊት የመጨረሻ ቃሉ ይህ ነው። ከፍ ከፍ የተደረገው፥ በያዕቆብ አምላክ የተቀባው፥ የእስራኤል ተወዳጁ ዘማሪ የሆነው፥ የእሴይ ልጅ የዳዊት የትንቢት ቃል ይህ ነው፤
2 #
ኢሳ. 59፥21፤ ኤር. 1፥9። “የጌታ መንፈስ በእኔ ተናገረ፤
ቃሉም በአንደበቴ ነው።
3 #
መዝ. 72፥1-4። የእስራኤል አምላክ ተናገረ፤
የእስራኤልም ዓለት እንዲህ አለኝ፦
ሰዎችን በጽድቅ የሚገዛ፥
እግዚአብሔርንም በመፍራት የሚያስተዳድር፥
4 #
መሳ. 5፥31፤ መዝ. 72፥6። እርሱ፥ እንደ ንጋት ብርሃን እንደ ማለዳ ፀሐይ አወጣጥ፥
ደመና በሌለበት ማለዳ እንደምታበራ የብርሃን ጸዳል፥
ከዝናብ በኋላ ከምድር እንደሚበቅል ልምላሜ ይሆናል።
5 #
2ሳሙ. 7፥11፤15-16፤ መዝ. 89፥30፤ ኢሳ. 55፥3። ሁሉንም ነገር አዘጋጅቶና ጠብቆ፥
ከእኔ ጋር ዘላለማዊ ኪዳን ያደረገ፥
መዳኔን ከፍጻሜ የሚያደርሰው፥
መሻቴን ሁሉ የሚሰጠኝ እርሱ አይደለምን?
በውኑ ቤቴ በእግዚአብሔር ዘንድ እንዲህ አይደለምን?
6 #
ዘዳ. 13፥14። ነገር ግን ክፉ ሰዎች ሁሉ፥
በእጅ እንደማይሰበሰብ እንደ እሾኽ ይጣላሉ።
7እሾኽ የሚነካ ሁሉ፥
የብረት መሣሪያ ወይም የጦር ዘንግ ይይዛል፤
እነሱም ባሉበት ስፍራ ፈጽመው በእሳት ይቃጠላሉ።”
የኀያላኑ የዳዊት ሰዎች ጀብዱ
8 #
1ዜ.መ. 11፥11-41፤ 27፥1-15። የዳዊት ኀያላን ሰዎች ስም የሚከተለው ነው፤ የታሕክሞን ሰው ዮሼብ ባሼቤት የሦስቱ አለቆች አለቃ ሲሆን፥ እርሱም ጦሩን ሰብቆ በአንድ ውጊያ ላይ ስምንት መቶ ሰው በአንዴ የገደለ ነው። 9#1ሳሙ. 17፥1።ከእርሱ ቀጥሎ የአሆህዊው የዶዶ ልጅ ኤልዔዘር ነበረ፤ እርሱም ለጦርነት አንድ ላይ ተሰብስበው የነበሩትን ፍልስጥኤማውያንን በተገዳደሩ ጊዜ፥ ከዳዊት ጋር ከነበሩት ከሦስቱ ኀያላን ሰዎች አንዱ ነበር። ከዚያም የእስራኤል ሰዎች አፈገፈጉ። 10እርሱ ግን ተነስቶ እጁ እስኪዝልና ከሰይፉ ጋር እስኪጣበቅ ድረስ ፍልስጥኤማውያንን ወጋ፤ በዚያችም ዕለት ጌታ ታላቅ ድልን አደረገ። ሕዝቡም ከእርሱ በኋላ ምርኮ ለመግፈፍ ብቻ ተመለሰ። 11#መሳ. 15፥9።ከእርሱም ቀጥሎ የሃራርታዊው የአጌ ልጅ ሻማ ነበር፤ ፍልስጥኤማውያንም ምስር በሞላበት ሌሒ በተባለ ስፍራ አንድ እርሻ ላይ በአንድነት ተሰብስበው ነበር። ሕዝቡም ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፤ 12ሻማ ግን የቆመበትን ስፍራ አለቀቀም፤ ጦርነቱንም ተቋቁሞ ፍልስጥኤማውያንን ገደለ፤ በዚያችም ዕለት ጌታ ታላቅ ድልን አደረገ።
13 #
1ሳሙ. 22፥1፤ ሚክ. 1፥15። ከሠላሳውም አለቆች ሦስቱ ወርደው በመከር ጊዜ ወደ ዳዊት ወደ ዓዱላም ዋሻ መጡ፥ የፍልስጥኤማውያንም ጭፍራ በራፋይም ሸለቆ ሰፍሮ ነበር። 14በዚያ ጊዜ ዳዊት በምሽግ ውስጥ ነበረ፤ የፍልስጥኤማውያንም ሠራዊት በቤተልሔም ነበረ፤ 15ዳዊትም በናፍቆት፥ “በበሩ አጠገብ ካለችው ከቤተልሔም ጉድጓድ ውሃ ማን ባመጣልኝ!” አለ። 16ሦስቱም ኀያላን በፍልስጥኤማውያን ሠራዊት መካከል ሰንጥቀው በማለፍ፥ በበሩ አጠገብ ካለችው ከቤተልሔም ጉድጓድ ውሃ ቀድተው ለዳዊት አመጡለት። እርሱ ግን አልጠጣውም፤ ይልቁን በጌታ ፊት አፈሰሰው፤ 17“እርሱም፥ ጌታ ሆይ፤ እንዲህ ያለውን ነገር ላደርግ? ይህስ ከእኔ ይራቅ! ይህ በነፍሳቸው ቆርጠው የሄዱ ሰዎች ደም አይደለምን?” ብሎ፥ ዳዊት ሊጠጣው አልፈለገም። ሦስቱ ኀያላን ሰዎች የፈጸሙአቸው ተግባሮች እነዚህ ነበሩ።
18የጽሩያ ልጅ የኢዮአብ ወንድም አቢሳ የሦስቱ ኀያላን አለቃ ነበረ። በሦስት መቶ ሰዎች ላይ ጦሩን ሰብቆ የገደላቸውና ስሙም ከሦስቱ ኀያላን ጋር የሚጠራ ነበረ። 19እርሱ ከሠላሳው ይልቅ እጅግ ዝነኛ ስለ ነበር፤ አለቃቸው ሆኖ ነበር፥ ነገር ግን ወደ ሦስቱ ደረጃ አልደረሰም።
20 #
2ሳሙ. 8፥18፤ 20፥23፤ መሳ. 14፥6፤ 1ነገ. 2፥29-30። የቃብጽኤል አገር ሰው የሆነው የዮዳሄ ልጅ በናያም ታላቅ ተግባር የፈፀመ ሌላው ጐበዝ ተዋጊ ነበረ፤ ሁለቱን በጣም የታወቁ የሞዓብን ሰዎችን ገድሎአል፤ እንዲሁም በረዶ በጣለበት ዕለት በጉድጓድ ውስጥ ገብቶ አንበሳ ገድሎአል፤ 21አንድ ማራኪ ግብፃዊንም ገድሎአል፤ ግብፃዊው በእጁ ጦር ይዞ፥ በናያ ግን ሊገጥመው በትር ይዞ ነበር ወደ እርሱ የሄደው፤ ከግብፃዊውም እጅ የገዛ ጦሩን በመንጠቅ ገደለው። 22የዮዳሄ ልጅ በናያ ያደረገው ይህ ነው፥ ስሙም እንደ ሦስቱ ኃያላን ተጠርቶ ነበር። 23#1ሳሙ. 22፥14።ከሠላሳዎቹ ይልቅ የከበረ ሰው ነበረ፤ ነገር ግን ከሦስቱ እንደ አንዱ አልነበረም። ዳዊትም የክብር ዘበኞቹ አለቃ አድርጎ ሾመው። 24#2ሳሙ. 2፥18-23።ከሠላሳዎቹ መካከል፦ የኢዮአብ ወንድም አሣሄል፥ የቤተልሔሙ ሰው የዶዶ ልጅ ኤልሐናን፥ 25ሐሮዳዊው ሻማ፥ ሐሮዳዊው ኤሊቃ፥ 26ፈሌጣዊው ሴሌስ፥ የቴቆአዊው የዒቄሽ ልጅ ዒራ፥ 27#2ሳሙ. 21፥18።ዓናቶታዊው አቢዔዜር፤ ሑሻዊው መቡናይ፥ 28አሆሃዊው ጻልሞን፥ ነጦፋዊው ማህራይ፥ 29የነጦፋዊው የበዓና ልጅ ሔሌብ፥ ከብንያም ተወላጅ የሆነው የጊብዓ ሰው የሪባይ ልጅ ኢታይ፥ 30ጲርዓቶናዊው በናያ፥ የገዓሽ ሸለቆ ሰው ሂዳይ፥ 31ዓረባዊው አቢዓልቦን፥ ባርሑማዊው ዓዝማዌት፥ 32ሸዓልቦናዊው ኤሊያሕባ፥ የያሼን ልጆች፤ ዮናታን፥ 33የሐራራዊው የሻማ ልጅ፥ የሐራራዊው የሻራር ልጅ አሒአም፤ 34የማዕካታዊው የአሐሰባይ ልጅ ኤሊፌሌጥ፥ የጊሎናዊው የአሒጦፌል ልጅ ኤሊአም፥ 35ቀርሜሎሳዊው ሔጽሮ፤ አርባዊው ፈዓራይ፥ 36የጾባዊው የናታን ልጅ ይግዓል፥ 37አሞናዊው ጸሌቅ፥ የጽሩያ ልጅ የኢዮአብ ጋሻ ጃግሬ የነበረው በኤሮታዊው ናሕራይ፥ 38ያቲራዊው ዒራ፥ ያቲራዊው ጋሬብ፥ 39#2ሳሙ. 11፥3።ሒታዊው ኦርዮ፤ በጠቅላላው ሠላሳ ሰባት ነበሩ።
Currently Selected:
2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 23: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ