2ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 17

17
1አኪጦፌልም፥ አቤሴሎምን እንዲህ አለው፤ “ዐሥራ ሁለት ሺህ ሰው ልምረጥና፥ ዛሬ ሌሊት ተነሥቼ ዳዊትን አሳድደዋለሁ፤ 2በደከመውና በዛለ ጊዜም ሽብር እለቅበታለሁ፤ አብሮት ያለውም ሕዝብ ሁሉ ትቶት ይሸሻል፤ ንጉሡን ብቻውን እመታዋለሁ፥ 3ሕዝቡን ሁሉ ወደ አንተ እመልሳለሁ፤ አንተ የምትፈልገው የአንድ ሰው መሞት ብቻ ነውና፥ ሕዝቡ ሁሉ በሰላም ይኖራል።” 4ምክሩም አቤሴሎምንና አብረውት የነበሩትን የእስራኤልን ሽማግሌዎች ሁሉ ደስ አሰኘ። 5ከዚያም አቤሴሎም፥ “እስቲ ደግሞ አርካዊውን ሑሻይን ጥሩትና የሚለውን እንስማ” አለ። 6ሑሻይም ወደ እርሱ በመጣ ጊዜ አቤሴሎም፥ “አኪጦፌል ይህን ምክር አቅርቧል፤ ታዲያ የእርሱን ምክር እንከተል? ካልሆነ እስቲ አንተ ተናገር” አለው። 7ሑሻይም አቤሴሎምን እንዲህ አለው፤ “አኪጦፌል የሰጠው ምክር በዚህ ጊዜ መልካም አይደለም፤” 8#ሆሴዕ 13፥8።ሑሻይም በተጨማሪ እንዲህ አለው፥ “አባትህና ሰዎቹ ብርቱ ጦረኞችና ግልገሎችዋም እንደተነጠቁባት የዱር ድብ አምርረው የሚነሡ መሆኑን ታውቃለህ፤ በተጨማሪም አባትህ በጦር ሜዳ ልምድ ያለው ነው፤ ሌሊቱን ከሠራዊቱ ጋር አያድርም፤ 9እነሆ፥ አሁን እንኳ በአንዱ ዋሻ ወይም በሌላ ቦታ ተደብቆ ይሆናል። ጥቂት ሰዎች በመጀመሪያ በሚጥልባቸው ጥቃት ቢሞቱ ይህን የሰማ ሁሉ፥ ‘አቤሴሎምን የተከተለው ሠራዊት ተፈጀ’ ብሎ ያወራል። 10አባትህ ታላቅ ጦረኛ፥ አብረውት ያሉትም ጀግኖች መሆናቸውን እስራኤል ሁሉ ስለሚያውቅ፥ ልቡ እንደ አንበሳ ልብ የሚደፍረው እንኳ በፍርሀት ይርዳል። 11እኔ የምመክርህ፥ ቁጥሩ እንደ ባሕር ዳር አሸዋ የበዛው፥ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ያለው እስራኤል ሁሉ ወዳንተ ይሰብሰብና አንተው ራስህ ወደ ጦርነቱ ምራው፤ 12ከዚያም እርሱ ይገኝበታል የተባለው ቦታ ገብተን እናገኝዋለን፥ ጠል መሬት ላይ እንደሚወርድ እንወርድበታለን፤ እርሱም ሆነ ሰዎቹ አንድ እንኳ አይተርፉም፤ 13ከአንዲቱ ከተማ ቢገባ፥ እስራኤል ሁሉ ገመድ አምጥቶ አንድ ድንጋይ እንኳ እስከማይቀር ድረስ፥ ከተማዪቱን ወደ ሸለቆ ስበን እንከታታለን።” 14#2ሳሙ. 15፥31፤34።አቤሴሎምና የእስራኤል ሰዎች ሁሉም “ከአኪጦፌል ምክር ይልቅ የአርካዊው የሑሻይ ምክር ይሻላል” አሉ፤ ጌታ በአቤሴሎም ላይ ጥፋት ለማምጣት፥ ጌታ መልካም የነበረው የአኪጦፌል ምክር ተቀባይነት እንዲያጣ አድርጎአል። 15ሑሻይ ካህናቱን ሳዶቅንና አብያታርን እንዲህ አላቸው፥ “አኪጦፌል አቤሴሎምንና የእስራኤልን ሽማግሌዎች እንዲህ እንዲህ አድርጉ ሲል መክሮአቸው ነበር፤ እኔ ግን እንዲህ እንዲህ አድርጉ ብዬ መክሬአቸዋለሁ። 16አሁንም በፍጥነት ላኩና፥ ‘ንጉሡና ከእርሱ ጋር ያለው ሕዝብ ሁሉ እንዳትዋጡ፥ በዚህች ሌሊት በምድረ በዳ መሻገሪያ እንዳታድር ሳትዘገይ ተሻገር፤’ ብላችሁ ለዳዊት ንገሩት፤ አላቸው።” 17በዚህ ጊዜ ዮናታንና አሒማዓጽ ወደ ከተማዪቱ ከገቡ ስለሚታዩ በዔንሮጌል ይጠባበቁ ነበር፤ አንዲት ልጃገረድ አገልጋይ ወደዚያ እየሄደች በምትነግራቸው ጊዜ፥ እነርሱ ደግሞ ይህንኑ ወስደው ለንጉሥ ዳዊት ይነግሩት ነበር። 18ሆኖም አንድ ወጣት አይቷቸው ለአቤሴሎም ነገረው፤ ሁለቱም በፍጥነት ተነሥተው በባሑሪም በግቢው ውስጥ ጉድጓድ ወደሚገኝ ወደ አንድ ሰው ቤት ሄዱ፤ ወደዚያም ውስጥ ወረዱ። 19ሚስቱም በጉድጓዱ አፍ ላይ የስጥ ማስጫ ዘርግታ እህል አሰጣች፤ ማንም ይህን አላወቀም ነበር። 20የአቤሴሎም ሰዎች እዚያ ቤት ወደ ሴቲቱ ዘንድ መጥተው፥ “አሒማዓጽና ዮናታን የት አሉ?” ብለው ጠየቋት። ሴቲቱም፥ “ወንዙን ተሻግረው ሄደዋል” ብላ መለሰችላቸው፤ እነርሱም ፈልገው ስላጧቸው፥ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።
21ሰዎቹ ከሄዱ በኋላ ሁለቱም ከጉድጓዱ ወጥተው ሄዱ፤ ለንጉሥ ዳዊትም፥ “አኪጦፌል በአንተ ላይ እንዲህ እንዲህ ብሎ ስለመከረብህ ተነሥተህ በፍጥነት ወንዙን ተሻገር” አሉት። 22ስለዚህ ዳዊትና አብሮት ያለው ሕዝብ በሙሉ ተነሥቶ ዮርዳኖስን ተሻገረ፤ ሲነጋም ዮርዳኖስን ሳይሻገር የቀረ አንድም ሰው አልነበረም።
23 # 2ሳሙ. 15፥31፤ 16፥23። አኪጦፌልም ምክሩን እንዳልተከተሉት ባየ ጊዜ፥ አህያውን ጭኖ ቤቱ ወደሚገኝበት ወደ መኖሪያ ከተማው ሄደ፤ ቤቱንም አስተካክሎ በገዛ እጁ ታነቀ፤ ከሞተ በኋላ በአባቱም መቃብር ተቀበረ። 24አቤሴሎም ከመላው የእስራኤል ሰዎች ጋር ዮርዳኖስን ሲሻገር፥ ዳዊት ግን ማሕናይም ደርሶ ነበር። 25#2ሳሙ. 19፥14፤ 20፥4-13።አቤሴሎምም በኢዮአብ ምትክ አማሳይን በሠራዊቱ ላይ ሾመ፤ አማሳይ የእስማኤላዊው የዮቴር ልጅ ነበረ፤ ዮቴርም የኢዮአብን እናት፥ የጽሩያን እኅት፥ የናዖስን ልጅ አቢግያንሰ አግብቶ ነበር። 26እስራኤላውያንና አቤሴሎም በገለዓድ ምድር ሰፈሩ። 27#2ሳሙ. 9፥4፤ 19፥32፤ 1ነገ. 2፥7፤ ዕዝ. 2፥61።ዳዊት ማሕናይም ሲደርስ፥ ከአሞናውያን ከተማ ከራባ የመጣው፥ የናዖስ ልጅ ሾቢ፥ ከሎዶባር የመጣው የዓሚኤል ልጅ ማኪርና ከሮግሊም የመጣው ገለዓዳዊው ቤርዜሊ 28መተኛ ምንጣፎች፥ ወጭቶችና የሸክላ ዕቃዎች ይዘው መጡ፤ እንዲሁም ስንዴና ገብስ፥ ዱቄትና የተጠበሰ እሸት፥ ባቄላና ምስር፥ 29ማር፥ እርጎ፥ በጎችና የላም አይብ እንዲበሉ ለዳዊትና ለሕዝቡ አመጡላቸው፤ ይህን ያደረጉትም፥ “ሕዝቡ በምድረ በዳ ተርቧል፤ ደክሞአል፤ ተጠምቶአል” ብለው ነው።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ