የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

2ኛ መጽሐፈ መቃብያን 12

12
የኢዮጴ እና የያምንያ አጋጣሚዎች
1ይህን ውል ከፈጸሙ በኋላ ሊስያስ ወደ ንጉሡ ተመለሰ፤ አይሁዳውያንም እርሻቸውን ማረስ ጀመሩ። 2ነገር ግን እዚያ ከነበሩት የጦር አለቆች መካከል ጢሞቴዎስና የጌኔይ ልጅ አጰሎንዮስ፤ እንዲሁም ሄሮኒሞስና ደሞፎን የቆጱሮሱ ኒቃኖር ሰላምና ጸጥታ ነሡዋቸው፤ 3በተለይ የኢዮጴ ሰዎች ክፉ ሥራ ሠሩባቸው፤ ከእነርሱ ጋር የሚኖሩትን አይሁዳውያን ከሚስቶቻቸውና ከልጆቻቸው ጋር ሆነው ባዘጋጅዋው መርከቦች እንዲሣፈሩ ጠሩዋቸው፤ በእነርሱ ላይ ክፉ ሐሳብ እንደሌላቸውም አስታወቁ፤ 4የከተማው ሕዝብ ባደረገው ውሳኔ መሠረት አይሁዳውያን ሰላም ፈላጊዎችና ምንም የማይጠራጠሩ መሆናቸውን ለማስታወቅ ሲሉ ጥሪያቸውን ተቀበሉ፤ ግን በባሕሩ መካከል በደረሱ ጊዜ ሁለት መቶ ያህል ሰዎችን ወደ ባሕር ጣሏቸው። 5ይሁዳ መቃቢስ በእርሱ ሀገር ሰዎች ላይ ይህ ጭካኔ መደረጉን በሰማ ጊዜ ትእዛዙን ወዲያው ለእርሱ ሰዎች አስተላለፈ። 6ትክክለኛ ፍርድ ወደሚሰጠው አምላክ ጸሎት ካደረገ በኋላ ወንድሞቹን ወደገደሉ ሰዎች ገሠገሠ። መርከብ የሚቆምበትን ጠረፍ በሌሊት እሳት ለቀቀበት፤ መርከቦቹን አቃጠለ፤ መጠጊያ ፈለገው ይሸሹ የነበሩትን አስገደለ፤ 7ግን የከተማው በር ተዘግቶ ስለ ነበር የኢዮጴን ሰዎች ሌላ ጊዜ ተመልሼ እደመስሳቸዋለሁ ብሎ ሄደ። 8እንዲሁም የያምንያ ሰዎች ከእነርሱ ጋር በሚኖሩ አይሁዳውያን ላይ ክፉ ለማድረግ እንዳቀዱ ሰማ፤ 9የያምንያ ሰዎችንም በሌሊት መጣባቸውና ጠረፉን ከመርከቦቹ ጋር በእሳት አጋየ፤ የእሳቱም ብርሃን እስከ ኢየሩሳሌም ማለትም እስከ ሠላም ምዕራፍ (45 ኪ. ሜትር) ርቀት ድረስ ታየ።
በገለዓድ የተደረገ ጦርነት
10ከጢሞቴዎስ ጋር ሊዋጉ ሲሄዱ ከዚያ አንድ ምዕራፍ (1.5 ኪ.ሜ) እንደራቁ አምስት ሺህ የሚያህሉ እግረኛ ጦረኞችና አምስት መቶ ፈረሰኞች ያሉት የዓረቦች ጦር ገጠሟቸው። 11ብርቱ ውጊያ ከተካሄደ በኋላም የይሁዳ ወታደሮች በእግዚአብሔር እርዳታ አሸንፈው ዘላኖቹ ዓረቦች ተሸንፈው ይሁዳን የሰላም እጁን እንዲዘረጋላቸው ለመኑት፤ ከብት እንሰጥሃለን፥ በሰላም ጊዜ ሁሉ እንጠቅምሃለን ሲሉ ተስፋ ሰጡት፤ 12ይሁዳም እነርሱ በእውነቱ ብዙ እንደሚያገለግሉት ተረድቶ ከእነርሱ ጋር ሰላም ማድረግ ፈለገ፤ ከተጨባበጡም በኋላ ዓረቦች ወደየድንኳኖቻቸው ገቡ። 13እንዲሁም ይሁዳ ብዙ ድብልቅ ሕዝቦች የሚኖሩባትን በግንብ ምሽግ የከበበችውን ቃስጴስ የምትባለዋን ሀገር ወጋ። 14እነዚያ በጦር የተከበቡ ሰዎች በግንባቸው ጥንካሬና በምግባቸው ክምችት ተማምነው የይሁዳን ወታደሮች በጣም ንቀዋቸው ነበር፤ ይራገሙና ይሳደቡም ነበር፤ የማይገባውን ነገር ይናገሩ ነበር። 15ግን ይሁዳና የእርሱ ሰዎች ያለመዋጊያና ያለ ጦር መሣሪያ በኢያሱ ዘመን ኢያሪኮን የገለባበጠ ታላቁን የዓለም ጌታን ከለመኑ በኋላ በቁጣ ግንቡን ከበው ይዋጉ ጀመር፤ 16በእግዚአብሔር ፈቃድ ከተማዋን ይዘው ለቍጥር የሚያስቸግር ሰው ፈጁ፤ ስፋቱ ሩብ ምዕራፍ (375 ሜትር) የነበረውን እዚያ አጠገብ የሚገኘውን ቀላይ የፈሰሰው ደም ሞላው። በቀርኒዩን የተደረገ ጦርነት 17ከዚያ ዘጠና አምስት ምዕራፍ 138 ኪሎ ሜትር ያህል ርቀው አይሁዳውያን ጦባውያን ወደሚሉት ወደ ካራስ ደረሱ። 18ጢሞቴዎስን ግን እዚያ አላገኘሁትም፤ ምክንያቱም እርሱ ምንም ሳያደርግ ከዚያ ቦታ ርቆ ሄዶ ነበር፤ በአንድ ቦታ ላይ ግን ብርቱ ጦር ሠራዊት ትቶ ነው የሄደው። 19የይሁዳ መቃቢስ ጦር መሪዎች ያስጦስና ሱሊ ጳጥሮስ ሄደው ከዐሥር ሺህ በላይ የሆኑትን ጢሞቴዎስ በምሽጉ ውስጥ ትቶአቸው የነበሩትን ሰዎች አጠፍዋቸው (ደመሰሱዋቸው)። 20ይሁዳ መቃቢስ በበኩሉ ጦር ሠራዊቱን በክፍል በክፍል አሰልፎ፥ ለየክፍሉም አለቃ ሾሞ መቶ ሃያ ሺህ እግረኛ እና ሁለት ሺህ አምስት መቶ ፈረሰኞች አሰልፎ የነበረውን ጢሞቴዎስን ለመውጋት ገሠገሠ። 21የይሁዳን መቃረብ በሰማ ጊዜ ጢሞቴዎስ ሴቶች ልጆች ከጓዝ ጋር ቀርንዮን ወደሚባል አገር ቀድመው እንዲጓዙ አደረገ፤ ምክንያቱም ቦታው የማይደፈርና በቦታው ጥበት ምክንያት መተላለፊያው የሚያስቸግር ስለ ነበር ነው። 22በይሁዳ የሚመራው ጦር ሠራዊት በመጀመሪያ ብቅ ባለ ጊዜ ጠላት ተሸበረ፤ ሁሉን የሚያይ አምላክ በግልጽ ፍርሃት አሳደረባቸው፤ በያሉበት ሸሹ፤ እርስ በርሳቸው ተቋሰሉ፥ በጐራዴም (በሰይፍም) አንዱ ሌላውን ይወጋ ነበር። 23ይሁዳ በልዩ ጥንካሬ ተከታተላቸው፤ እነዚህን ጨካኞች በሰይፍ ፈጃቸው፤ እስከ ሰላሳ ሺህ ሰዎች ተገደሉ። 24ጢሞቴዋስም በጰሲጦስና በሱሊጳጥሮስ ወታደሮች እጅ ወደቀ፤ እንዳይገሉትና እንዲለቁት ለመናቸው፥ “ዘመዶቻችሁና ከወንድሞቻችሁ አብዛኞቹ በእኔ ሥልጣን ሥር ያሉ ናቸው፤ በእኔ ሞት ምክንያት እነርሱ ጉዳት እንዳይደርስባቸው” ሲል እንዲለቁት በተንኮል ተናገራቸው። 25ግዴታውን ካረጋገጠላቸው በኋላና ሰዎቹን በደኀና እለቃቸዋለሁ ብሎ ብዙ በመናገር ቃሉን ከሰጣቸው በኋላ ወንድሞቻቸውን ለማዳን ለቀቁት። 26ይሁዳ ወደ ቀርኒዮን ወደ አተርጋቶን ሄዶ ሃያ አምስት ሺህ ሰው ገደለ።
በኤፍሮን እና በሽቶፖሊስ በኩል የተደረገው የመልስ ጉዞ
27ጠላቶቹን ካሸነፈና ካጠፋ በኋላ ጦር ሠራዊቱን ወደ ኤፍሮን አዘመተ፤ ኤፍሮን ሊስያስ የሚኖርባት ምሽግ ከተማ ናት፤ እዚያ ጠንካራ ወጣቶች ከግንቡ ፊት ለፊት ቦታቸውን ይዘው በጥንካሬ ይዋጉ ነበር፤ በክልሉም ብዙ የጦር መሳሪያዎች ተምዘግዛጊዎች ነበሩ። 28ግን አይሁዳውያን የጠላቶችን ኃይል የሚሰብረውን ጌታ ከለመኑ በኋላ ከተማዋን መያዝ ቻሉ፤ በግንቡ ውስጥ ከሚገኙት ሰዎች መካከል ሃያ አምስት ሺህውን አጋደሙ። 29ቦታውን ትተው ከኢየሩሳሌም ሰባ አምስት ምዕራፍ፤ (አንድ ሺ አንድ መቶ ሃያ ሦስት ኪሎ.ሜ ተኩል) ርቃ ወደምትገኘው ወደ ሽቶፖሊስ ገሠገሡ። 30ነገር ግን እዚያ የነበሩ አይሁዳውያን ሲቲያውን ያደረጉላቸውን መልካም ነገር ስለመሰከሩላቸውና በችግራቸው ጊዜ በመልካም የተቀበሏቸው መሆኑን ስለተናገሩላቸው 31ይሁዳና የእርሱ ወታደሮች ሰዎቹን አመስግነው ለወደፊቱም ለሕዝበቸው ደጐች እንዲሆኑ መክረዋቸው የሳምንቱ በዓል (የጴንጤቆስጤ በዓል) ቀርቦ ስለ ነበር ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሰው ሄዱ። ከጐርጊያስ ጋር የተደረገ ጦርነት 32ከጴንጤቆስጠ በዓል በኋላ የኤያምያስ ገዥ ከነበረው ከጐርጊያስ ጋር ለመዋጋት ገሠገሡ፤ 33ጐርጊያስ ሦስት ሺህ እግረኛ ጦርና አራት መቶ ፈረሰኛ እየመራ መጣ። 34በተደረገው ጦርነት ጥቂቶች አይሁዳውያን ወደቁ (ሞቱ)። 35ይሲጦስ ከባኬኖር (ከጦብ) ሰዎች አንድ ጀግና ፈረሰኛ የሆነው ሰው ጐርጊያስን በልብሱ ይዞ ይህን እርጉም ሰው ለመማረክ ይጐትተው ነበር፤ ነገር ግን አንድ የትራኪስ አገር ፈረሰኛ ወደ ይሲጦስ ሮጠና ትከሻውን በሰይፍ መታው፤ ጐርጊያስም አመለጠና ወደ ማሬሳ ሸሸ። 36የአዝሪ ወታደሮች ግን ብዙ ጊዜ ከተዋጉ በኋላ ድካም ተሰማቸው፤ እግዚአብሔር በጦርነቱ ላይ ረዳታቸውና መሪአቸው እንዲሆን ይሁዳ ጸለየላቸው። 37በሀገሩ ቋንቋ ጮክ ብሎ የጦር መዝሙር ከዘመረ በኋላ የጐርጊያስን ሰዎች አባረራቸው። ስለ ሙታን የቀረበ መሥዋዕት 38ይሁዳ ሠራዊቱን አስተባበረና ወደ አይላም አገር ሄደ፤ ነገር ግን የሳምንቱ ሰባተኛ ቀን ስለ ደረሰ እንደተለመደው የመንጻት ሥራን አደረጉና በዚያ ቦታ የሰንበትን በዓል አከበሩ። 39በማግስቱ ይሁዳና የእርሱ ሰዎች በጦርነት የሞቱትን ሰዎች በጊዜው አስክሬናቸውን ለማንሣትና ከዘመዶቻቸው ጋር በአባቶቻቸው መቃብር ለመቅበር መጡ። 40ከሞቱት ከእያንዳዳቸው ልብስ ውስጥ ለያመንያ ጣዖት የቀረበውን በአይሁድ ሕግ የተከለከለውን መባ አገኙ፤ 41ስለዚህ ሁሉም የተሠወረውን ነገር የሚገልጽ ትክክለኛ ፈራጅ የሆነውን አምላክ አመሰገኑ፤ 42የሠሩት ኃጢአትም በሙሉ እንዲሰረይላቸው ጸለዩ፤ ጀግናው ይሁዳም ወታደሮቹ በኃጢአታቸው ምክንያት በሞት የተቀጡትን ሰዎች (ወታደሮች) በማየት ከኃጢአት ሁሉ ንጹሕ እንዲሆኑ መከራቸው። 43ከእያንዳንዳቸውም ገንዘብ በመሰብሰብ በኃጢአት ምክንያት መሥዋዕት እንዲቀርብ ሁለት ሺህ ድራህም ወደ ኢየሩሳሌም ላከ፤ ይህንንም ያደረገው ስለ ትንሣኤ መልካምና ትክክል የሆነውን ነገር በማሰብ ነው። 44የሞቱት ወታደሮች ከሞት የሚነሡ መሆናቸውን ተስፋ ባያደርግ ኖሮ ለሙታን ጸሎት ማድረግ ሞኝነት እና የማያስፈልግ በሆነ ነበር፤ 45በመንፈሳዊነት (በመልካም) የሞቱ ሰዎች መልካም ሽልማት የሚያገኙ መሆናቸውን ማሰቡ ቅዱስና መልካም ሐሳብ ነው። ስለዚህ ኃጢአታቸው ይቅር እንዲባልላቸው ይህ የኃጢአት ማስተሣረያ (ኃጢአት ይቅር ማሰኛ) የሆነው መሥዋዕት ለሙታን እንዲደረግላቸው አስደረገ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ