2ኛ መጽሐፈ ነገሥት 15:1-26

2ኛ መጽሐፈ ነገሥት 15:1-26 መቅካእኤ

ዳግማዊ ኢዮርብዓም በእስራኤል በነገሠ በሀያ ሰባተኛው ዓመት የአሜስያስ ልጅ ዖዝያ በይሁዳ ንጉሥ ሆነ፤ እርሱም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ዐሥራ ስድስት ዓመት ነበር፤ መኖሪያውንም በኢየሩሳሌም አድርጎ ኃምሳ ሁለት ዓመት ገዛ፤ እናቱም ይኮልያ ተብላ የምትጠራ የኢየሩሳሌም ተወላጅ ነበረች። እርሱም የአባቱን መልካም አርአያነት በመከተል እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ሠራ፤ ነገር ግን በየኰረብቶች ላይ የነበሩትን የአሕዛብን የማምለኪያ ቦታዎች አልደመሰሰም፤ ስለዚህም ሕዝቡ በየኰረብቶች ላይ መሥዋዕት ማቅረባቸውንና ዕጣን ማጠናቸውን እንደ ቀጠሉ ነበር፤ በኋላም እግዚአብሔር በዖዝያ ላይ የቆዳ በሽታ አሳደረበት፤ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ይህ በሽታ ስላልለቀቀው ከሥራው ሁሉ ተገልሎ በተለየ ቤት ውስጥ ለብቻው ይኖር ነበር፤ በዚህም ጊዜ መንግሥቱን ሲመራ የቆየው ልጁ ኢዮአታም ነበር። ንጉሥ ዖዝያ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግቦ ይገኛል። ዖዝያ ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘው በቀድሞ አባቶቹ መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ኢዮአታም ነገሠ። ዖዝያ በይሁዳ በነገሠ በሠላሳ ስምንተኛው ዓመት የዳግማዊ ኢዮርብዓም ልጅ ዘካርያስ በእስራኤል ነገሠ፤ መኖሪያውንም በሰማርያ አድርጎ ስድስት ወር ገዛ፤ እርሱም ከእርሱ በፊት እንደነበሩት ነገሥታት ሁሉ ኃጢአት በመሥራት እግዚአብሔርን አሳዘነ፤ እንዲሁም እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የናባጥ ልጅ የንጉሥ ኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነት ተከተለ፤ ሻሉም ተብሎ የሚጠራው የያቤሽ ልጅ ሤራ በማድረግ ዪብለዓም ተብላ በምትጠራው ስፍራ ንጉሥ ዘካርያስን ገድሎ በእርሱ እግር ነገሠ። ንጉሥ ዘካርያስ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። በዚህም ዓይነት እግዚአብሔር ለንጉሥ ኢዩ “ልጆችህ እስከ አራት ትውልድ በእስራኤል ይነግሣሉ” ሲል የተናገረው የተስፋ ቃል ተፈጸመ። ዖዝያ በይሁዳ በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት የያቤሽ ልጅ ሻሉም የእስራኤል ንጉሥ ሆነ፤ መኖሪያውንም በሰማርያ አድርጎ አንድ ወር ብቻ ገዛ። ምናሔም ተብሎ የሚጠራው የጋዲ ልጅ ከቲርጻ ተነሥቶ ወደ ሰማርያ ሄደ፤ ሻሉምንም ገድሎ በእርሱ እግር ነገሠ። ሻሉም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ፥ እንዲሁም እርሱ የጠነሰሰው ሤራ ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። ምናሔም ከቲርጻ ተነሥቶ በሚያልፍበት ጊዜ እግረ መንገዱን የቲፍሳሕን ከተማ፥ ነዋሪዎችዋንና በዙሪያዋ የነበረውን ግዛት ሁሉ ደመሰሰ፤ ይህንንም ያደረገበት ምክንያት የከተማይቱ ነዋሪዎች ለእርሱ እጃቸውን ለመስጠት ባለመፍቀዳቸው ነበር፤ ከዚህም የተነሣ ነፍሰ ጡሮችን እንኳ ሳይምር ሆዳቸውን ቀደደ። ዖዝያ በይሁዳ በነገሠ በሠላሳ ዘጠነኛው ዓመት የጋዲ ልጅ ምናሔም በእስራኤል ነገሠ፤ መኖሪያውን በሰማርያ አድርጎ ዐሥር ዓመት ገዛ። እስከ ዕድሜው ፍጻሜ ድረስ እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የናባጥ ልጅ ኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነት በመከተል ኃጢአት በመሥራቱም እግዚአብሔርን አሳዘነ። የአሦር ንጉሠ ነገሥት ቲግላት ፐሌሴር እስራኤልን ወረረ፤ ምናሔም በአገሩ መንግሥት ላይ ሥልጣኑን እንዲያጸናለትና እንዲደግፈው ለመማጠን ሠላሳ አራት ሺህ ኪሎ የሚመዝን ብር እጅ መንሻ አድርጎ ለቲግላት ፐሌሴር ሰጠው። ምናሔም ገንዘቡን የሰበሰበው የእስራኤል ከበርቴዎች እያንዳንዳቸው ኀምሳ ጥሬ ብር አዋጥተው እንዲሰጡ በማስገደድ ነበር። በዚህም ዓይነት ቲግላት ፐሌሴር በሰላም ወደ አገሩ ተመልሶ ሄደ። ምናሔም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። ምናሔም ሞተ፤ ተቀበረም፤ በእርሱም እግር ተተክቶ ልጁ ፈቃሕያ ነገሠ። ዖዝያ በይሁዳ በነገሠ በኀምሳኛው ዓመት የምናሔም ልጅ ፈቃሕያ በእስራኤል ነገሠ፤ መኖርያውንም በሰማርያ አድርጎ ሁለት ዓመት ገዛ፤ እስራኤልን ወደ ኃጢአት የመራ የናባጥ ልጅ የንጉሥ ኢዮርብዓምን መጥፎ አርአያነት በመከተል ኃጢአት ስለ ሠራ እግዚአብሔርን አሳዘነ። ከፈቃሕያ ሠራዊት መካከል ፈቁሔ ተብሎ የሚጠራ የረማልያ ልጅ የሆነ አንድ የጦር መኰንን ከኀምሳ የገለዓድ ሰዎች ጋር ሆኖ ሤራ ጠነሰሰ፤ በሰማርያ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ በሚገኘው ምሽግ ውስጥ ዘልቆ በመግባትም ፈቃሕያን ከአርጎብና ከሃርዬ ጋር ገድሎ በፈቃሕያ እግር ተተክቶ ነገሠ። ፈቃሕያ ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል።