በዚህም ጉዳይ ምክሬን እለግሳችኋለሁ፤ ከአምና ጀምራችሁ በመስጠት ብቻ ሳይሆን ለመስጠት በማሰብም ቀዳሚ ነበራችሁ፤ አሁንም እንዳዐቅማችሁ መጠን ለማድረግ ያላችሁ ጉጉት እንደ ሐሳባችሁ እንዲሆንላችሁ የጀመራችሁትን ከፍጻሜ አድርሱት። በጎ ፈቃድ ቢኖር፥ ባለው ባለው መጠን ተቀባይነት ይኖረዋል እንጂ የሌላውን አይጠበቅበትም። በናንተ ላይ ጫና ይብዛ ለሌሎች ደግሞ ዕረፍት ይሁን ማለቴ አይደለም፤ ነገር ግን ሁላችሁም እኩል እንድትሆኑ ነው። የእነርሱ ትርፍ ደግሞ የእናንተን ጉድለት እንዲሞላ፥ በዚህም ያላችሁን እኩል እንዲሆን፥ የአሁኑ የእናንተ ትርፍ የእነርሱን ጉድለት ይሙላ። “ብዙ ያከማቸ አላተረፈም፤ ጥቂትም ያከማቸ አላጎደለም።” ተብሎ እንደተጻፈው። ነገር ግን እኔ ለእናንተ ያለኝን በጎ ሐሳብ በቲቶ ልብ ውስጥ ያኖረ አምላክ የተመሰገነ ይሁን፤ እርሱ ምክራችንን ብቻ አይደለም የተቀበለው፥ ከቀድሞው የበለጠ በመትጋት፥ ወዶ ወደ እናንተ ይመጣል። ከእርሱም ጋር ስለ ወንጌል ስብከት በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የተመሰገነውን ወንድም እንልካለን፤ ይህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን የጌታን የራሱን ክብርና የእኛን በጎ ፈቃድ ለማሳየት በምናገለግለው በዚህ የቸርነት ሥራ ከእኛ ጋር አብሮን እንዲሄድ በአብያተ ክርስቲያናት ተመርጧል። እኛም ስለምናገለግለው ስለዚህ የቸርነት ስጦታ ማንም እንዳይነቅፈን እንጠነቀቃለን፤ ምክንያቱም በጌታ ፊት ብቻ ያልሆነ፥ ነገር ግን በሰው ፊት ደግሞ መልካም የሆነውን ስለምናስብ ነው። በብዙ ነገር ተፈትኖና በብዙ ጉዳዮች ትጉህ ሆኖ ያገኘነውን ወንድማችንን ከእነርሱ ጋር ልከነዋል። አሁንም በእናንተ እጅግ ስለሚታመን ከበፊት ይልቅ እጅግ ትጉህ ነው። ስለ ቲቶ የሚጠይቅ ቢኖር፥ እናንተን ለማገልገል አብሮኝ የሚሠራ ባልንጀራዬ ነው፤ ስለ ወንድሞቻችን የሚጠይቅ ቢኖር፥ የአብያተ ክርስቲያናት መልእክተኞችና የክርስቶስ ክብር ናቸው። እንግዲህ ስለ ፍቅራችሁና ስለ እናንተ ያለን ትምክህት ማረጋገጫ እንዲሆነን በአብያተ ክርስቲያናት ፊት ይህን ለእነርሱ በግልጽ አሳዩ።
2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 8 ያንብቡ
ያዳምጡ 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 8
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 8:10-24
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos