ስለዚህ ጕዳይ የምሰጣችሁ ጠቃሚ ምክር ይህ ነው፤ ባለፈው ዓመት በመስጠት ብቻ ሳይሆን ለመስጠት በማሰብም ቀዳሚ ነበራችሁ፤ አሁንም የጀመራችሁትን ተግባር በዐቅማችሁ መጠን ከፍጻሜ አድርሱት፤ ይህም ለመስጠት የነበራችሁ በጎ ፈቃድ እውን እንዲሆን ነው። ለመስጠት በጎ ፈቃድ ካለን ስጦታው ተቀባይነት የሚያገኘው ባለን መጠን ስንሰጥ እንጂ፣ በሌለን መጠን ለመስጠት ስንሞክር አይደለም። ይህን የምንለው እናንተ ተቸግራችሁ ሌሎች ይድላቸው ለማለት ሳይሆን፣ ሁላችሁም እኩል እንድትሆኑ ነው። በአሁኑ ጊዜ የእናንተ ትርፍ የእነርሱን ጕድለት ያሟላል፤ የእነርሱም ደግሞ በተራው የእናንተን ጕድለት ያሟላል፤ በዚህም ያላችሁን እኩል ትካፈላላችሁ። ይህም፣ “ብዙ የሰበሰበ አላተረፈም፤ ጥቂትም የሰበሰበ አልጐደለበትም” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። እኔ ለእናንተ ያለኝን በጎ ሐሳብ በቲቶ ልብ ውስጥ ያኖረ አምላክ የተመሰገነ ይሁን፤ ምክንያቱም ቲቶ ወደ እናንተ የመጣው ልመናችንን በመቀበል ብቻ ሳይሆን፣ በታላቅ ጕጕትና በራሱ ፈቃድ በመነሣሣት ነበር። ከርሱም ጋራ በወንጌል ስብከት በአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ የተመሰገነውን ወንድም ልከነዋል። ከዚህም በላይ ስጦታውን በምንወስድበት ጊዜ ዐብሮን እንዲሄድ በአብያተ ክርስቲያናት ተመርጧል፤ ስጦታውንም የምንወስደው ጌታን ራሱን ለማክበርና ሌሎችን ለመርዳት ካለን በጎ ፈቃድ የተነሣ ነው። በዚህ በምናከናውነው የቸርነት ሥራ አንዳች ነቀፋ እንዳይገኝብን እንጠነቀቃለን። ምክንያቱም ዐላማችን በጌታ ፊት ብቻ ሳይሆን፣ በሰውም ፊት መልካም የሆነውን ነገር ማድረግ ነው። ደግሞም ብዙ ጊዜ በብዙ መንገድ ተፈትኖ ትጉ ሆኖ የተገኘውን ወንድማችንን ከእነርሱ ጋራ ልከነዋል፤ አሁንም በእናንተ እጅግ ከመታመኑ የተነሣ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ እየተጋ ነው። ስለ ቲቶ የሚጠይቅ ቢኖር፣ እርሱ እናንተን ለማገልገል ዐብሮኝ የሚሠራ ባልደረባዬ ነው፤ ስለ ወንድሞቻችንም የሚጠይቅ ቢኖር እነርሱ የአብያተ ክርስቲያናት ተወካዮችና የክርስቶስ ክብር ናቸው። ስለዚህ የፍቅራችሁን እውነተኛነትና በእናንተም የምንታመነው የቱን ያህል እንደ ሆነ በአብያተ ክርስቲያናት ፊት ግለጡላቸው።
2 ቆሮንቶስ 8 ያንብቡ
ያዳምጡ 2 ቆሮንቶስ 8
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2 ቆሮንቶስ 8:10-24
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos