ወደ መቄዶንያም በመጣን ጊዜ፥ በሁሉ ነገር መከራን ተቀበልን እንጂ ሰውነታችን ዕረፍት አልነበረውም፤ ከውጭ ጠብ ነበረ፤ ከውስጥ ደግሞ ፍርሃት ነበረብን። ነገር ግን ኀዘንተኞችን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን፤ በመምጣቱም ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ናፍቆታችሁንና ልቅሶአችሁን ስለ እኔም የነበራችሁን ቅንዓት ሲነገረን በእናንተ ስለተጽናናን ማለቴ ነው፤ ስለዚህም ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ደስ አለኝ። በመልእክቴ ያሳዘንኋችሁ ብሆን እንኳ አልጸጸትም፤ የተጸጸትሁ ብሆን እንኳ፥ ያ መልእክት ለጥቂት ጊዜ ብቻ እንዳሳዘናችሁ ተረድቻለሁ፤ አሁን ግን ሐዘናችሁ ወደ ንስሓ ስለመራችሁ ደስ ብሎኛል እንጂ ደስታዬ ስለ ሐዘናችሁ አይደለም፤ በማንኛውም መንገድ በእኛ በኩል እንድትጎዱ አንፈልግም። እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ወደ መዳን ለሚያደርስ ንስሓ ያበቃል፤ ጸጸትም የለበትም፤ ዓለማዊው ኀዘን ግን ሞትን ያመጣል። እነሆ፥ ይህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ኀዘን ለእንዴት ዓይነት ትጋት፥ ለእንዴት ዓይነት ራስን የማንጻት ጉጉት፥ ለእንዴት ዓይነት ቊጣ፥ ለእንዴት ዓይነት ፍርሃት፥ ለእንዴት ዓይነት ናፍቆት፥ ለእንዴት ዓይነት ቅንዓት፥ ለእንዴት ዓይነት ቅጣት እንዳደረሳችሁ ተመልከቱ! በዚህም ጉዳይ ንጹሓን መሆናችሁን በሁሉ ረገድ አስመስክራችኋል። እንግዲያስ ጽፌው እንኳን ቢሆን ኖሮ፥ ስለ እኛ ያላችሁ ትጋት በእናንተ በኩል በእግዚአብሔር ፊት እንዲገለጥ እንጂ፥ ስለ በደለኛ ወይም ስለ ተበዳይ አይደለም የጻፍኩት። ስለዚህ ተጽናንተናል፤ ክመጽናናታችንም ሌላ ስለ ቲቶ ደስታ እጅግ ደስ ብሎናል፤ ምክንያቱም ልቡ በሁላችሁም እረፍት አግኝቷል። በእርሱ ፊት ስለ እናንተ በተመካሁበት ነገር አላሳፈራችሁኝም፤ ነገር ግን ሁሉን ለእናንተ የተናገርነው እውነት እንደሆነ ሁሉ፥ እንደዚሁም ትምክህታችን በቲቶ ፊት እውነት ሆነ። ስለዚህም በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ እንዴት እንደ ተቀበላችሁት፥ የሁላችሁን መታዘዝ እያሰበ ለእናንተ ያለው ፍቅር እጅግ ጨምሯል። በነገር ሁሉ ተማምኜባችኋለሁና ደስ ይለኛል።
2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 7 ያንብቡ
ያዳምጡ 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 7
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 7:5-16
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos