ወደ መቄዶንያ በመጣን ጊዜ፣ ከየአቅጣጫው መከራ ደረሰብን እንጂ ሰውነታችን ዕረፍት አላገኘም፤ ከውጭ ጠብ፣ ከውስጥ ደግሞ ፍርሀት ነበረብን። ይሁን እንጂ ሐዘንተኞችን የሚያጽናና አምላክ በቲቶ መምጣት አጽናናን። የተጽናናነውም በመምጣቱ ብቻ ሳይሆን፣ እርሱንም ልታጽናኑት በመቻላችሁ ጭምር ነው። ስለ ናፍቆታችሁ፣ ስለ ሐዘናችሁና ለእኔም ስላላችሁ ቅናት ነግሮናል፤ ስለዚህ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ደስ ብሎኛል። በመልእክቴ ባሳዝናችሁም በዚህ አልጸጸትም፤ ብጸጸትም እንኳ መልእክቴ ያሳዘናችሁ ለጥቂት ጊዜ እንደ ሆነ ተረድቻለሁ። አሁን ግን ደስ ብሎኛል፤ ደስታዬም ስላዘናችሁ ሳይሆን፣ ሐዘናችሁ ንስሓ ለመግባት ስላበቃችሁ ነው፤ ምክንያቱም ሐዘናችሁ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ ከእኛ የተነሣ ምንም አልተጐዳችሁም። እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ሐዘን ወደ ድነት ለሚያደርስ ንስሓ ያበቃል፤ ጸጸትም የለበትም። ዓለማዊ ሐዘን ግን ለሞት ያበቃል። ይህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነው ሐዘን እንዴት ያለ ትጋት፣ እንዴት ያለ መልስ የመስጠት ችሎታ፣ እንዴት ያለ ቍጣ፣ እንዴት ያለ ፍርሀት፣ እንዴት ያለ ናፍቆት፣ እንዴት ያለ በጎ ቅናት፣ እንዴት ያለ በቀል እንዳስገኘላችሁ ተመልከቱ። በዚህም ጕዳይ ንጹሓን መሆናችሁን በሁሉ ረገድ አስመስክራችኋል። እንግዲህ እኔ የጻፍሁላችሁ ስለ በደለው ወይም ስለ ተበደለው ሰው አይደለም፤ ነገር ግን ለእኛ ምን ያህል ታማኞች እንደ ሆናችሁ፣ በእግዚአብሔር ፊት ራሳችሁን እንድታዩ በማለት ነው። እኛም የተጽናናነው በዚህ ምክንያት ነው። ከእኛም መጽናናት በተጨማሪ በቲቶ ደስታ እኛም ይበልጥ ደስ ብሎናል፤ ምክንያቱም ሁላችሁም መንፈሱን አሳርፋችኋል። በእናንተ ላይ ያለኝን ትምክሕት ለርሱ ነግሬው ነበር፤ እናንተም አላሳፈራችሁኝም። ነገር ግን ስንነግራችሁ የነበረው ሁሉ እውነት እንደ ሆነ፣ እንደዚሁም ስለ እናንተ ለቲቶ በትምክሕት የነገርነው እውነት መሆኑ ተረጋግጧል። እርሱም በፍርሀትና በመንቀጥቀጥ እንዴት እንደ ተቀበላችሁትና ሁላችሁም እንደ ታዘዛችሁ ሲያስታውስ ለእናንተ ያለው ፍቅር እየበረታ ሄዷል። እኔም በማናቸውም ነገር ልተማመንባችሁ በመቻሌ ደስ ብሎኛል።
2 ቆሮንቶስ 7 ያንብቡ
ያዳምጡ 2 ቆሮንቶስ 7
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 2 ቆሮንቶስ 7:5-16
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos