2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 6
6
ቤተ መቅደሱ መቀደሱ
1ሰሎሞንም እንዲህ አለ፦ “ጌታ፦ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እኖራለሁ ብሏል፤ 2እኔ ግን ለዘለዓለም እንድትኖርበት ታላቅ የሆነ ማደሪያ ቤትን ሠራሁልህ።” 3ንጉሡም ፊቱን ወደ ጉባኤ ዘወር አድርጎ የእስራኤልን ጉባኤ ሁሉ መረቀ፤ የእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ ቆመው ነበር። 4#2ሳሙ. 7፥1-13፤ 1ዜ.መ. 17፥1-12።እርሱም እንዲህ አለ፦ “ለአባቴ ለዳዊት እንዲህ ብሎ በአፉ የተናገረው በእጁም የፈፀመው የእስራኤል አምላክ ጌታ ይባረክ፤ እርሱም እንዲህ አለው፦ 5‘ህዝቤን ከግብጽ ካወጣሁበት ቀን ጀምሮ ስሜ የሚጠራበት ቤት በዚያ እንዲሠራልኝ ከእስራኤል ነገድ ሁሉ ማንኛውንም ከተማ አልመረጥሁም፤ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ አለቃ እንዲሆን ማንንም አልመረጥሁም፤ 6ነገር ግን ስሜ በዚያ እንዲጠራባት ኢየሩሳሌምን መርጫለሁ፥ በሕዝቤም በእስራኤል ላይ እንዲሆን ዳዊትን መርጫለሁ።’ 7አባቴም ዳዊት ለእስራኤል አምላክ ለጌታ ቤት ለመሥራት በልቡ አስቦ ነበር። 8ጌታም አባቴን ዳዊትን እንዲህ አለው፦ ‘ለስሜ ቤት ለመሥራት በልብህ አስበሃልና ይህን በልብህ ማሰብህ መልካም አደረግህ። 9ነገር ግን ከአብራክህ የተገኘው ልጅህ እርሱ ለስሜ ቤትን ይሠራል እንጂ ቤት የምትሠራልኝ አንተ አይደለህም።’ 10ጌታም የተናገረውን ቃል ፈጸመ፤ ጌታም ተስፋ እንደሰጠ በአባቴ በዳዊት ፋንታ ተነሣሁ፥ በእስራኤልም ዙፋን ላይ ተቀመጥሁ፥ ለእስራኤልም አምላክ ለጌታ ስም ቤት ሠራሁ። 11ከእስራኤልም ልጆች ጋር ያደረገው የጌታ ቃል ኪዳን ያለበትን ታቦት በዚያው ውስጥ አኖርሁ።”
የንጉሥ ሰሎሞን ጸሎት
12ሰሎሞንም የእስራኤል ጉባኤ ሁሉ እያዩት በጌታ መሠዊያ ፊት ቆሞ እጆቹን ዘረጋ፤ 13ሰሎሞንም ርዝመቱ አምስት ክንድ፥ ወርዱም አምስት ክንድ፥ ቁመቱም ሦስት ክንድ የሆነ የናስ መደገፊያ ሠርቶ በአደባባዩ መካከል ተክሎት ነበር፥ በእርሱም ላይ ቆመ፥ በእስራኤልም ጉባኤ ሁሉ ፊት በጉልበቱ ተንበርክኮ እጁን ወደ ሰማይ ዘርግቶ፥ 14እርሱ እንዲህ አለ፦ “አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ! በሰማይ ወይም በምድር አንተን የሚመስል አምላክ የለም፤ በፍጹም ልባቸው በፊትህ ለሚሄዱ ባርያዎችህ ቃል ኪዳንንና ጽኑ ፍቅርን የምትጠብቅ፥ 15ለባርያህ ለአባቴ ለዳዊት የሰጠኸውን ተስፋ የጠበቅህ፤ በአፍህ ተናገርህ፥ ዛሬም እንደ ሆነው በእጅህ ፈጸምኸው። 16#1ነገ. 2፥4።እንግዲህ አሁን፥ አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ! ‘አንተ በፊቴ እንደ ሄድህ ልጆችህ በሕጌ እንዲሄዱ መንገዳቸውን ቢጠብቁ በእስራኤል ዙፋን የሚቀመጥ ሰው በፊቴ አታጣም’ ብለህ ተስፋ የሰጠኸውን ለባርያህ ለአባቴ ለዳዊት ጠብቅ። 17ስለዚህ፥ አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ! ለባርያህ ለዳዊት የተናገረኸው ቃል ይጽና።
18 #
2ዜ.መ. 2፥6። “በውኑ እግዚአብሔር ከሰው ጋር በምድር ላይ ይኖራልን? እነሆ፥ ሰማይ ከሰማያትም በላይ ያለ ሰማይ አንተን መያዝ አይችልም፤ ይልቁንስ እኔ የሠራሁት ቤት እንዴት ያንስ ይሆን? 19ነገር ግን፥ አቤቱ አምላኬ ሆይ! ወደ ባርያህ ጸሎትና ልመና ተመልከት፥ ባርያህም በፊትህ የሚጸልየውን ጸሎትና ጥሪውን ስማ። 20#ዘዳ. 12፥11።ባርያህ ወደዚህ ስፍራ የሚጸልየውን ጸሎት እንድትሰማ በዚያ ስሜ ይሆናል ወዳልኸው ስፍራ፥ ወደዚህ ቤት ዐይኖችህ ቀንና ሌሊት የተገለጡ ይሁኑ። 21ባርያህና ሕዝብህ እስራኤል ወደዚህ ስፍራ የሚጸልዩትን ልመና ስማ፤ በማደሪያህ በሰማይ ስማ፤ ሰምተህም ይቅር በል።
22“ሰው በባልንጀራው ላይ ኃጢአት ቢሠራ፥ እርሱም መሐላ እንዲምል ቢደረግ፥ እርሱም መጥቶ በዚህ ቤት በመሠዊያህ ፊት ቢምል፥ 23አንተ በሰማይ ሆነህ ስማ፥ አድርግም፥ በባርያዎችህንም ፍረድ፥ በደለኛውንም እንደ በደሉ ክፈለው፥ መንገዱንም በራሱ ላይ መልስበት፤ ንጹሑንም አጽድቀው፥ እንደ ጽድቁም ክፈለው።
24“ሕዝብህም እስራኤል በአንተ ላይ ኃጢአት ስለ ሠሩ በጠላት ፊት ድል ተመትተው ወደ አንተ ቢመለሱ፥ ስምህንም ቢጠሩ፥ በዚህም ቤት በፊትህ ቢጸልዩና ቢለምኑህ፥ 25አንተ በሰማይ ሆነህ ስማ፥ የሕዝብህንም የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል፤ ለእነርሱም ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጠሃት ምድር መልሳቸው።
26“በአንተ ላይ ኃጢአት ስለ ሠሩ ሰማያት በተዘጉ ጊዜ ዝናብም ባልዘነበ ጊዜ፥ ወደዚህ ስፍራ ቢጸልዩ፥ ስምህንም ቢጠሩ፥ ባሠቃየሃቸውም ጊዜ ከኃጢአታቸው ቢመለሱ፥ 27አንተ በሰማይ ሆነህ ስማ፥ የባርያዎችህንና የሕዝብህን የእስራኤልን ኃጢአት ይቅር በል፥ የሚሄዱበትንም መልካም መንገድ አሳያቸው፤ ለሕዝብህም ርስት አድርገህ ለሰጠሃት ምድር ዝናብን ስጥ።
28“በምድር ላይ ራብ ወይም ቸነፈር ወይም ዋግ ወይም አረማሞ ወይም አንበጣ ወይም ኩብኩባ ቢሆን፥ ጠላቶቻቸውም የአገሩን ከተሞች ከብበው ቢያስጨንቁአቸው፥ ማናቸውም መቅሠፍትና ደዌ ቢሆን፥ 29ማንም ሰው ወይም ሕዝብህ እስራኤል ሁሉ፥ እያንዳንዱም ሰው ሕመሙንና ኀዘኑን አውቆ ጸሎትና ልመና ቢያደርግ እጆቹንም ወደዚህ ቤት ቢዘረጋ፥ 30በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ስማ፥ ይቅርም በል፤ አንተ ብቻ የሰውን ልጆች ልብ ታውቃለህና ልቡን ለምታውቀው ሰው ሁሉ እንደ መንገዱ ሁሉ መጠን ክፈለው። 31ስለዚህ ለአባቶቻችን በሰጠኸው ምድር ላይ በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ ይፍሩህ በመንገዶችህም ይሂዱ።
32“ከሕዝብህም ከእስራኤል ያልሆነ እንግዳ ስለ ታላቁ ስምህ ስለ ብርቱውም እጅህ ስለ ተዘረጋውም ክንድህ ከሩቅ አገር በመጣ ጊዜ፥ መጥቶም ወደዚህ ቤት በጸለየ ጊዜ፥ 33አንተ በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ስማ፤ የምድርም አሕዛብ ሁሉ ስምህን እንዲያውቁ፥ እንደ ሕዝብህም እንደ እስራኤል እንዲፈሩህ፥ ይህም የሠራሁት ቤት በስምህ እንደ ተጠራ እንዲያውቁ፥ እንግዳው የሚለምንህን ሁሉ አድርግ።
34“ሕዝብህም ጠላቶቻቸውን ለመውጋት አንተ በምትልካቸው መንገድ ቢወጡ፥ አንተም ወደ መረጥሃት ወደዚህች ከተማ እኔም ለስምህ ወደ ሠራሁት ቤት ለአንተ ቢጸልዩ፥ 35ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በሰማይ ሆነህ ስማ፥ ፍርድንም አድርግላቸው።
36“ኃጢአት የማይሠራ ሰው የለምና በአንተ ላይ ኃጢአት ቢሠሩ፥ ተቈጥተህም ለጠላት አሳልፈህ ብትሰጣቸው፥ ሩቅም ወይም ቅርብ ወደ ሆነ አገር ቢማርኩአቸው፥ 37በተማረኩበትም አገር ሆነው በልባቸው ንስሐ ቢገቡ፥ በምርኮአቸውም አገር ሳሉ ተመልሰው፦ ‘ኃጢአት ሠርተናል፥ ስሕተት ፈጽመናል፥ ክፉም አድርገናል’ ብለው ቢለምኑህ፥ 38በተማረኩበትም በምርኮአቸው አገር ሳሉ በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው ወደ አንተ ቢመለሱ፥ ለአባቶቻቸውም ወደ ሰጠሃት ወደ ምድራቸው ወደ መረጥሃትም ከተማ ለስምህም ወደ ሠራሁት ቤት ቢጸልዩ፥ 39ጸሎታቸውንና ልመናቸውን በማደሪያህ በሰማይ ሆነህ ስማ፥ ፍርድንም አድርግላቸው፤ በአንተም ላይ ኃጢአት የሠሩብህን ሕዝብህን ይቅር በል።
40“አሁንም፥ አምላኬ ሆይ! በዚህ ስፍራ ወደሚሆነው ጸሎት ዐይኖችህ የተገለጡ፥ ጆሮችህም የሚያደምጡ እንዲሆኑ እባክህ እለምንሃለሁ። 41#መዝ. 132፥8-10።አሁንም፥ አቤቱ አምላክ ሆይ! ተነሥተህ አንተና የኃይልህ ታቦት ወደ ማረፍያ ስፍራህ ሂዱ፤ አቤቱ አምላክ ሆይ! ካህናትህ ደኅንነትን ይልበሱ፤ ቅዱሳንህም በደስታ ደስ ይበላቸው። 42አቤቱ አምላክ ሆይ! የቀባኸውን ሰው አታሳፍረው ለባርያም ለዳዊት ያደረግህለትን ጽኑ ፍቅር አስብ።”
Currently Selected:
2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 6: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ