2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 30

30
ታላቁ የፋሲካ በዓል
1 # ዘኍ. 9፥9-11። ለእስራኤልም አምላክ ለጌታ ፋሲካን ለማክበር ወደ ጌታ ቤት ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመጡ ሕዝቅያስ ወደ እስራኤልና ወደ ይሁዳ ሁሉ ላከ፥ ደግሞም ወደ ኤፍሬምና ወደ ምናሴ ደብዳቤ ጻፈ። 2ንጉሡና አለቆቹ የኢየሩሳሌምም ጉባኤ ሁሉ በሁለተኛው ወር ፋሲካውን ለማክበር ተመካክረው ነበር። 3ዳሩ ግን በጊዜው ለማክበር አልቻሉም ነበር ምክንያቱም በቊጥር በቂ የሆኑ ካህናት ስላልተቀደሱ፥ ሕዝቡም ገና በኢየሩሳሌም ስላልተሰባሰቡ ነበር። 4ነገሩም በንጉሡና በጉባኤው ሁሉ ዘንድ መልካም ነበረ። 5እንደ ተጻፉትም ያህል በብዙ ቍጥር ፋሲካን አላከበሩም ነበርና የእስራኤልን አምላክ የጌታን ፋሲካ በኢየሩሳሌም ለማክበር እንዲመጡ ከቤር-ሳቤህ ጀምሮ እስከ ዳን ድረስ ለእስራኤል ሁሉ አዋጅ እንዲነገር ወሰኑ። 6እንደ ንጉሡም ትእዛዝ መልክተኞቹ እንዲህ የሚለውን የንጉሡንና የሹማምንቱን ደብዳቤ ይዘው ወደ እስራኤልና ወደ ይሁዳ ሁሉ ሄዱ እንዲህም አሉ፦ “የእስራኤል ልጆች ሆይ! ጌታ ከአሦር ነገሥታት እጅ ወዳመለጠ የእናንተ ወደ ሆኑት ትሩፋን እንዲመለስ ወደ አብርሃምና ወደ ይስሐቅ ወደ እስራኤልም አምላክ ተመለሱ። 7እናንተም እንደምታዩት መሣቀቅያ እስኪያደርጋቸው ድረስ የአባቶቻቸውን አምላክ ጌታን እንደ በደሉ እንደ አባቶቻችሁና እንደ ወንድሞቻችሁ አትሁኑ። 8አባቶቻችሁም እንደ ነበሩ አንገተ ደንዳና አትሁኑ፤ እጃችሁንም ለጌታ ስጡ፥ ለዘለዓለም ወደተቀደሰው ወደ መቅደሱም ግቡ፥ ጽኑ ቁጣውም ከእናንተ እንዲመለስ አምላካችሁን ጌታን አገልግሉ። 9አምላካችሁ ጌታ ቸርና መሐሪ ነውና፥ ወደ እርሱም ብትመለሱ ፊቱን ከእናንተ አያዞርምና ወደ ጌታ ብትመለሱ ወንድሞቻችሁና ልጆቻችሁ በማረኩአቸው ፊት ምሕረትን ያገኛሉ፥ ደግሞም ወደዚህች ምድር ይመለሳሉ።”
10መልእክተኞቹም ከከተማ ወደ ከተማ በኤፍሬምና በምናሴ አገር እስከ ዛብሎን ድረስ ሄዱ፤ በእዚያ ያሉ ሰዎች ግን በንቀት ሳቁባቸው፤ አፌዙባቸውም። 11ነገር ግን ከአሴርና ከምናሴ ከዛብሎንም ጥቂት ሰዎች ብቻ ራሳቸውን አዋረዱ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ። 12ደግሞም አንድ ልብ እንዲሰጣቸው፥ በጌታም ቃል የሆነውን የንጉሡንና የሹማምንቱን ትእዛዝ እንዲያደርጉ የጌታ እጅ በይሁዳ ላይ ነበረ።
13በሁለተኛውም ወር የቂጣውን በዓል ሊያከብር እጅግ ታላቅ ጉባኤ የሆነ ሕዝብ በኢየሩሳሌም ተሰበሰበ። 14ተነሥተውም በኢየሩሳሌም የነበሩትን መሠዊያዎችና ለጣዖታት የሚያጥኑበትን ዕቃ ሁሉ አስወገዱ፥ በቄድሮንም ወንዝ ጣሉት። 15በሁለተኛውም ወር በዓሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካውን ጠቦት አረዱ፤ ካህናቱና ሌዋውያኑም ራሳቸውን አዋረዱ፥ ተቀደሱም፥ ወደ ጌታም ቤት የሚቃጠል መሥዋዕት አመጡ። 16እንደ እግዚአብሔርም ሰው እንደ ሙሴ ሕግ በሥርዓታቸው ቆሙ፤ ካህናቱም ከሌዋውያን እጅ የተቀበሉትን ደም ይረጩ ነበር። 17በጉባኤውም ያልተቀደሱ እጅግ ሰዎች ነበሩ፤ ስለዚህም ሌዋውያን ለጌታ የተቀደሱ ለማድረግ ንጹሐን ላልሆኑት ሁሉ የፋሲካውን ጠቦት ያርዱላቸው ነበር። 18እንደ ትእዛዙም ሳይሆን ከኤፍሬምና ከምናሴ ከይሳኮርና ከዛብሎንም ወገን እጅግ ብዙ ሰዎች ሳይነጹ ፋሲካውን በሉ። ሕዝቅያስም ስለ እነርሱ እንዲህ ብሎ ጸለየ፦ “ቸሩ ጌታ ሆይ! ሁሉንም ሰው ይቅር በል፤ 19እንደ መቅደሱ የማንጻት ሥርዓት ሳይሆን የአባቶቹን አምላክ ጌታን ለመፈለግ ልቡን አቅንቶአልና።” 20ጌታም ሕዝቅያስን ሰማው፥ ሕዝቡንም ፈወሰ። 21በኢየሩሳሌምም ተገኝተው የነበሩ የእስራኤል ልጆች የቂጣውን በዓል በታላቅ ደስታ ሰባት ቀን አከበሩ፤ ሌዋውያኑና ካህናቱም በዜማ ዕቃ ለጌታ እየዘመሩ ዕለት ዕለት ጌታን ያመሰግኑ ነበር። 22ሕዝቅያስም በጌታ አገልግሎት አስተዋዮች የነበሩትን ሌዋውያን ሁሉ ያበረታታ ነበር። የአንድነትንም መሥዋዕት እያቀረቡ፥ የአባቶቻቸውንም አምላክ እያመሰገኑ ለሰባት ቀን ለበዓሉ የተዘጋጀውን ማዕድ በሉ።
23ከካህናቱም እጅግ ብዙ ተቀድሰው ነበርና ጉባኤው ሁሉ እንደገና ሰባት ቀን በዓሉን ለማክበር ተማከሩ፤ በደስታም እንደገና ሰባት ቀን በዓሉን አከበሩ፤ 24እንዲህም ያከበሩት የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ እንደ ቁርባን ስለሚቀርበው መሥዋዕት አንድ ሺህ ወይፈኖችና ሰባት ሺህ በጎች እንዲሁም ሹማምንቱ አንድ ሺህ ወይፈኖችና ዐሥር ሺህ በጎች ለጉባኤው ሰጥተው ስለ ነበረ ነው። 25የይሁዳም ጉባኤ ሁሉ፥ ካህናቱና ሌዋውያኑ፥ ከእስራኤልም የመጡ ጉባኤ ሁሉ፥ ከእስራኤልም አገር የመጡትና በይሁዳ የኖሩት እንግዶች ደስ አላቸው። 26በኢየሩሳሌምም ታላቅ ደስታ ሆነ፤ ከእስራኤል ንጉሥ ከዳዊት ልጅ ከሰሎሞን ዘመን ጀምሮ እንደዚህ ያለ በዓል በኢየሩሳሌም አልተከበረም ነበር። 27ካህናቱና ሌዋውያኑም ተነሥተው ሕዝቡን ባረኩ፤ ድምጻቸውም ተሰማ፥ ጸሎታቸውም ወደ ቅዱስ መኖሪያው ወደ ሰማይ ዐረገ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ