2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 29

29
ሕዝቅያስ መንገሡ
1ሕዝቅያስም የሀያ አምስት ዓመት ጎልማሳ በነበረ ጊዜ መንገሥ ጀመረ፥ በኢየሩሳሌም ሀያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ፤ እናቱም የዘካርያስ ልጅ አቡ ትባል ነበር። 2አባቱም ዳዊት እንዳደረገ ሁሉ በጌታ ፊት ቅን ነገር አደረገ።
መቅደሱ መጽዳቱ
3በነገሠም በመጀመሪያው ዓመት በመጀመሪያውም ወር የጌታን ቤት ደጆች ከፈተ፥ አደሳቸውም። 4ካህናቱንና ሌዋውያኑንም አስመጣ፥ በምሥራቅ በኩል ባለው አደባባይም ሰበሰባቸው፥ 5እንዲህም አላቸው፦ “ሌዋውያን ሆይ! ስሙኝ፤ ተቀደሱ፥ የአባቶቻችሁንም አምላክ የጌታን ቤት ቀድሱ፤ ርኩሱንም ነገር ሁሉ ከመቅደሱ አስወግዱ። 6አባቶቻችን ተላልፈዋል፥ በአምላካችንም በጌታ ፊት ክፉ አድርገዋል፤ እርሱንም ትተዋል፥ ፊታቸውንም ከጌታ መኖሪያ መልሰዋል፥ ወደ እርሷም ጀርባቸውን አዙረዋል፤ 7ደግሞም ዋና የመግቢያ ደጆችን ዘጉ፥ መብራቶቹንም አጥፍተዋል፥ በመቅደሱም ውስጥ ለእስራኤል አምላክ አላጠኑም፥ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት አላቀረቡም። 8ስለዚህም የጌታ ቁጣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ወረደ፥ በዓይናችሁም እንደምታዩ ለድንጋጤና ለመደነቂያ ለመዘበቻም አሳልፎ ሰጣቸው። 9እነሆም፥ ስለዚህ አባቶቻችን በሰይፍ ወደቁ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችንም ሚስቶቻችንም ተማረኩ። 10አሁንም የቁጣው ጽናት ከእኛ እንዲመለስ ከእስራኤል አምላክ ከጌታ ጋር ቃል ኪዳን ለማድረግ በልቤ አስቤአለሁ። 11ልጆቼ ሆይ! በፊቱ ቆማችሁ እንድታገለግሉት፥ አገልጋዮቹም እንድትሆኑ፥ እንድታጥኑለትም ጌታ መርጦአችኋልና ቸል አትበሉ።”
12ሌዋውያኑም፥ ከቀዓት ልጆች የአማሢ ልጅ መሐትና የዓዛርያስ ልጅ ኢዮኤል፥ ከሜራሪም ልጆች የአብዲ ልጅ ቂስና የይሃሌልኤል ልጅ ዓዛርያስ፥ ከጌድሶንም ልጆች የዛማት ልጅ ዮአክና የዮአክ ልጅ ዔድን፥ 13ከኤሊጸፋንም ልጆች ሺምሪና ይዒኤል፥ ከአሳፍም ልጆች ዘካርያስና መታንያ፥ 14ከኤማንም ልጆች ይሒኤልና ሰሜኢ፥ ከኤዶታምም ልጆች ሸማያና ዑዝኤል ተነሡ። 15ወንድሞቻቸውንም ሰብስበው ተቀደሱ፤ የጌታንም ቃላት መሠረት አድርጎ#29፥15 እንደ ጌታም ቃላት፤ ንጉሡ እንዳዘዘው የጌታን ቤት ለማንጻት ገቡ። 16ካህናቱም መቅደሱን ለማንጻት ወደ ጌታ ቤት ወደ ውስጡ ገቡ፥ በጌታም መቅደስ ያገኙትን ርኩስ ነገር ሁሉ ወደ ጌታ ቤት አደባባይ አወጡት። ሌዋውያንም ወስደው ወደ ሜዳ ወደ ቄድሮን ወንዝ ጣሉት። 17በመጀመሪያውም ወር በመጀመሪያው ቀን ይቀድሱ ጀመር፥ በዚያውም ወር በስምንተኛው ቀን ወደ ጌታ ቤት ዋና የመግቢያ ደጅ ደረሱ የጌታንም ቤት በስምንት ቀን ውስጥ ቀደሱት፥ በመጀመሪያውም ወር በዓሥራ ስድስተኛው ቀን ፈጸሙ። 18ወደ ውስጡም ወደ ንጉሡ ወደ ሕዝቅያስ ገብተው እንዲህ አሉት፦ “የጌታን ቤት ሁሉ፥ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያና ዕቃውንም ሁሉ፥ የተቀደሰውም ሕብስት የሚቀመጥበትን ገበታና ዕቃውን ሁሉ አንጽተናል፤ 19ንጉሡም አካዝ ነግሦ ሳለ በመተላለፍ ያረከሰውን ዕቃ ሁሉ አዘጋጅተናል ቀድሰናልም፤ እነሆም፥ በጌታ መሠዊያ ፊት ተቀምጠዋል።”
በመቀደሱ ውስጥ የሚደረገው አምልኮ ዳግመኛ መደረጉ
20ንጉሡም ሕዝቅያስ ማልዶ ተነሣ የከተማይቱንም አለቆች ሰበሰበ፥ ወደ ጌታም ቤት ወጣ። 21ስለ መንግሥቱና ስለ መቅደሱም ስለ ይሁዳም ሰባት ወይፈኖች፥ ሰባትም አውራ በጎች፥ ሰባትም የበግ ጠቦቶች፥ ሰባትም አውራ ፍየሎች ለኃጢአት መሥዋዕት አመጡ። የአሮንንም ልጆች ካህናቱን፦ “በጌታ መሠዊያ ላይ አሳርጉአቸው” አላቸው። 22ወይፈኖቹንም አረዱ፥ ካህናቱም ደሙን ተቀብለው በመሠዊያው ላይ ረጩት፤ አውራ በጎቹንም አረዱ፥ ደሙንም በመሠዊያው ላይ ረጩት፤ ጠቦቶቹንም አረዱ ደሙንም በመሠዊያው ላይ ረጩት። 23የኃጢአትም መሥዋዕት የሚሆኑትን አውራ ፍየሎች በንጉሡና በጉባኤው ፊት አቀረቡ፥ እጃቸውንም ጫኑባቸው፥ ካህናቱም አረዱአቸው፤ 24ንጉሡም የሚቃጠል መሥዋዕትና የኃጢአት መሥዋዕት ለእስራኤል ሁሉ እንዲደረግ አዝዞ ነበርና ለእስራኤል ሁሉ ማስተሰረያ እንዲያደርጉ የኃጢአቱን መሥዋዕት ደም በመሠዊያው ላይ አቀረቡ።
25ይህንም ትእዛዝ ጌታ በነቢያቱ እጅ አዝዞአልና እንደ ዳዊትና እንደ ንጉሡ ባለ ራእይ እንደ ጋድ፥ እንደ ነቢዩም እንደ ናታን ትእዛዝ፥ ጸናጽልና በገና መሰንቆም አስይዞ ሌዋውያንን በጌታ ቤት አቆመ። 26ሌዋውያንም የዳዊትን የዜማ ዕቃ ይዘው፥ ካህናቱም መለከቱን ይዘው ቆመው ነበር። 27ሕዝቅያስም የሚቃጠለውን መሥዋዕት በመሠዊያ ላይ እንዲያሳርጉ አዘዘ፤ የሚቃጠለውም መሥዋዕት ማሳረግ በተጀመረ ጊዜ የጌታ መዝሙር ደግሞ ይዘመር ጀመር፥ መለከቱም ተነፋ፥ የእስራኤልም ንጉሥ የዳዊት ዜማ ዕቃ መዝሙሩን ያጅብ ነበር። 28ጉባኤውም ሁሉ ሰገዱ፥ መዘምራኑም ዘመሩ፥ መለከተኞችም ነፉ፤ የሚቃጠለው መሥዋዕት እስኪፈጸም ድረስ ይህ ሁሉ ያለማቋረጥ ተከነናወነ። 29ማቅረቡንም በፈጸሙ ጊዜ ንጉሡና ከእርሱ ጋር የነበሩ ሁሉ አጐነበሱ ሰገዱም። 30ንጉሡም ሕዝቅያስና ሹማምንቱ ሌዋውያንን በዳዊትና በባለ ራእዩ በአሳፍ ቃል ጌታን እንዲያመሰግኑ አዘዙ። በደስታም እያመሰገኑ፥ አጐነበሱም ሰገዱም።
31ሕዝቅያስም፦ “አሁን ለጌታ ተቀድሳችኋል፤ ቅረቡ፥ መሥዋዕቱንና የምስጋናውን መሥዋዕት ወደ ጌታ ቤት አምጡ” ብሎ ተናገረ። ጉባኤውም መሥዋዕቱንና የምስጋናውን መሥዋዕት አመጡ፤ ልባቸውም የፈቀደ ሁሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕት አመጡ። 32ጉባኤውም ያመጡት የሚቃጠል መሥዋዕት ቍጥር ሰባ በሬዎች፥ መቶም አውራ በጎች፥ ሁለት መቶም የበግ ጠቦቶች ነበረ፤ ይህ ሁሉ ለጌታ የሚቃጠል መሥዋዕት ነበረ። 33የተቀደሱትም ስድስት መቶ በሬዎች ሦስት ሺህም በጎች ነበሩ። 34ነገር ግን ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለመግፈፍ ጥቂቶች ነበሩ፤ ስለዚህም ሌዋውያን በቅን ልብ ከካህናት ይልቅ ይቀደሱ ነበርና ሥራው እስኪፈጸም ድረስ፥ ካህናቱም እስኪቀደሱ ድረስ ወንድሞቻቸው ሌዋውያን ያግዙአቸው ነበር። 35እጅግ ብዙ ከነበረው የሚቃጠል መሥዋዕት ጋር የአንድነቱ መሥዋዕት ስብ ነበረ፤ ለሚቃጠለውም መሥዋዕት የሚቀርበው የመጠጥ ቁርባን በዚያ ነበረ። እንዲህ ባለ መንገድ የጌታ ቤት አገልግሎት ተዘጋጀ። 36ሕዝቅያስና ሕዝቡም ሁሉ ጌታ ለሕዝቡ ስላዘጋጀላቸው ነገር ደስ አላቸው። ይህም ነገር በድንገት ተደረገ።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ