2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 23:16-21

2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 23:16-21 መቅካእኤ

ዮዳሄም በእርሱና በሕዝቡ ሁሉ በንጉሡም መካከል የጌታ ሕዝብ እንዲሆኑ ቃል ኪዳን አደረገ። ሕዝቡም ሁሉ ወደ ባዓል ቤት ሄደው አፈረሱት፥ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹንም አደቀቁ፥ የባዓልንም ካህን ማታንን በመሠዊያው ፊት ገደሉት። ዮዳሄም በሙሴ ሕግ እንደተጻፈው፥ እንደ ዳዊትም ትእዛዝ፥ በደስታና በመዝሙር ለጌታ የሚቃጠለውን መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ዳዊት በጌታ ቤት የከፈላቸውን ካህናትና ሌዋውያን በጌታ ቤት አገልግሎት ላይ ሾመ። በማናቸውም ነገር ሁሉ ርኩስ የሆነ ሰው እንዳይገባ በጌታ ቤት በር በጠባቂዎችን አኖረ። የመቶ አለቆችንም፥ ከበርቴዎቹንም፥ የሕዝቡንም አለቆች፥ የአገሩንም ሕዝብ ሁሉ ወሰደ፥ ንጉሡንም ከጌታ ቤት ወስደው በላይኛው በር በኩል ወደ ንጉሡ ቤት መጡ፥ ንጉሡንም በመንግሥቱ ዙፋን ላይ አስቀመጡት። የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ደስ አላቸው፥ ከተማይቱም ጸጥ አለች፤ ጎቶሊያንም በሰይፍ ገደሉአት።