2ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል 23

23
1በሰባተኛውም ዓመት ዮዳሄ በረታ፥ የመቶ አለቆቹንም፥ የይሮሐምን ልጅ ዓዛርያስን፥ የይሆሐናንንም ልጅ ይስማኤልን፥ የዖቤድንም ልጅ ዓዛሪያስን፥ የዓዳያንም ልጅ መዕሤያን፥ የዝክሪንም ልጅ ኤሊሳፋጥን ወስዶ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። 2ይሁዳንም ዞሩ፥ በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ሌዋውያንንና የእስራኤልን አባቶች ቤቶች አለቆች ሰብስበው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። 3#2ሳሙ. 7፥12።ጉባኤውም ሁሉ በጌታ ቤት ውስጥ ከንጉሥ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። ዮዳሄም እንዲህ አላቸው፦ “እነሆ፥ ጌታ ስለ ዳዊት ልጆች እንደ ተናገረ የንጉሡ ልጅ ይነግሣል። 4የምታደርጉት ይህ ነው፤ በሰንበት ቀን ከምትገቡት ከእናንተ ከካህናትና ከሌዋዊውያን ከሦስቱ አንዱ በመግቢያ በሮች ላይ ጠባቂዎች ሁኑ፤ 5ከሦስቱም አንዱ በንጉሥ ቤት ሁኑ፤ እንዲሁም ከሦስቱ አንዱ በመካከለኛው በር ሁኑ፤ ሕዝቡም ሁሉ በጌታ ቤት አደባባይ ይሁኑ። 6ወደ ጌታ ቤት ግን ከካህናትና ከአገልጋዮቹ ሌዋውያን በቀር ማንም አይግባ፤ እነርሱ ቅዱሳን ናቸውና ይግቡ፤ ሕዝቡም ሁሉ ግን የጌታን ሕግ ይጠብቅ። 7ሌዋውያንም የጦር መሣሪያቸውን በእጃቸው ይዘው ንጉሡን በዙሪያው ይክበቡት፤ ወደ ቤቱም የሚገባ ይገደል ንጉሡም ሲገባና ሲወጣ ከእርሱ ጋር ሁኑ።”
ኢዮአስ ዘውድ መጫኑ
8ሌዋውያንና ይሁዳም ሁሉ ካህኑ ዮዳሄ ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ፤ ካህኑም ዮዳሄ ሰሞነኞቹን አላሰናበተም ነበርና እያንዳንዱ በሰንበት ቀን ይገቡ የነበሩትን በሰንበትም ቀን ይወጡ የነበሩትን ሰዎች ወሰደ። 9ካህኑም ዮዳሄ በጌታ ቤት የነበረውን የንጉሡን የዳዊትን ጋሻና ጦር አላባሽ አግሬውንም ጋሻ ለመቶ አለቆች ሰጣቸው። 10ሕዝቡም ሁሉ እያንዳንዱ የጦር መሣሪያውን በእጁ እየያዘ በንጉሡ ዙሪያ ከቤቱ ቀኝ እስከ ቤቱ ግራ ድረስ በመሠዊያውና በቤቱ አጠገብ እንዲቆም አደረገ። 11የንጉሡንም ልጅ አውጥተው ዘውዱን ጫኑበት፥ ምስክሩንም ሰጡት፥ አነገሡትም፤ ዮዳሄና ልጆቹም፦ “ንጉሡ ሺህ ዓመት ይንገሥ” እያሉ ቀቡት።
ጎቶሊያ መገደልዋ
12ጎቶሊያም የሚሮጡትንና ንጉሡን የሚያመሰግኑትን የሕዝቡን ድምፅ በሰማች ጊዜ ወደ ሕዝቡ ወደ ጌታ ቤት መጣች። 13እነሆም፥ ንጉሡ በመግቢያው በዓምዱ አጠገብ ሆኖ ከንጉሡም ጋር አለቆችና መለከተኞች ቆመው አየች። የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ደስ ብሎአቸው መለከቱን ይነፉ ነበር፤ መዘምራንም በዜማ ዕቃ እያዜሙ የምስጋና መዝሙር ይዘምሩ ነበር። ጎቶሊያም ልብስዋን ቀድዳ፦ “ዓመጽ ነው፥ ዓመጽ ነው” ብላ ጮኸች። 14ካህኑም ዮዳሄ በጭፍራው ላይ የተሾሙትን የመቶ አለቆች፦ “ከሰልፉ መካከል አውጡአት የሚከተላትም በሰይፍ ይገደል” ብሎ አዘዛቸው። ካህኑም፦ “በጌታ ቤት ውስጥ አትግደሉአት” አለ። 15እጃቸውን በእስዋ ላይ ጭነው ያዝዋት፤ እርሷም ወደ ፈረሱ በር መግቢያ ወደ ንጉሡ ቤት ሄደች፥ በዚያም ገደሉአት።
16ዮዳሄም በእርሱና በሕዝቡ ሁሉ በንጉሡም መካከል የጌታ ሕዝብ እንዲሆኑ ቃል ኪዳን አደረገ። 17ሕዝቡም ሁሉ ወደ ባዓል ቤት ሄደው አፈረሱት፥ መሠዊያዎቹንና ምስሎቹንም አደቀቁ፥ የባዓልንም ካህን ማታንን በመሠዊያው ፊት ገደሉት። 18ዮዳሄም በሙሴ ሕግ እንደተጻፈው፥ እንደ ዳዊትም ትእዛዝ፥ በደስታና በመዝሙር ለጌታ የሚቃጠለውን መሥዋዕት እንዲያቀርቡ ዳዊት በጌታ ቤት የከፈላቸውን ካህናትና ሌዋውያን በጌታ ቤት አገልግሎት ላይ ሾመ። 19በማናቸውም ነገር ሁሉ ርኩስ የሆነ ሰው እንዳይገባ በጌታ ቤት በር በጠባቂዎችን አኖረ። 20የመቶ አለቆችንም፥ ከበርቴዎቹንም፥ የሕዝቡንም አለቆች፥ የአገሩንም ሕዝብ ሁሉ ወሰደ፥ ንጉሡንም ከጌታ ቤት ወስደው በላይኛው በር በኩል ወደ ንጉሡ ቤት መጡ፥ ንጉሡንም በመንግሥቱ ዙፋን ላይ አስቀመጡት። 21የአገሩም ሕዝብ ሁሉ ደስ አላቸው፥ ከተማይቱም ጸጥ አለች፤ ጎቶሊያንም በሰይፍ ገደሉአት።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ