ሳሙኤልም ሞተ፤ መላው እስራኤል ሁሉ ተሰብስበው አለቀሱለት፤ ራማ ባለው ቤቱም ቀበሩት። ከዚያም ዳዊት ተነሥቶ ወደ ፋራን ምድረ በዳ ወረደ። በማዖን ምድር በቀርሜሎስ ንብረት ያለው አንድ ባለጸጋ ሰው ነበረ፤ እርሱም አንድ ሺህ ፍየሎችና በቀርሜሎስ የሚሸልታቸው ሦስት ሺህ በጎች ነበሩት። የሰውየው ስም ናባል፥ የሚስቱም ስም አቢጌል ነበረ። እርሷም አስተዋይና ውብ ነበረች፤ ባሏ ግን ባለጌና ምግባረ ብልሹ ሰው ነበረ፤ እርሱም ከካሌብ ወገን ነበር። ዳዊት በምድረ በዳ ሳለ ናባል በጎቹን እንደሚሸልት ሰማ። እርሱም ዐሥር ወጣቶችን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ “ወደ ቀርሜሎስ ወደ ናባል ውጡ፤ በስሜም ሰላምታ አቅርቡለት። እንዲህም በሉት፤ ‘ሰላም ለአንተ ይሁን፤ ሰላም ለቤተሰብህና የአንተ ለሆነው ሁሉ ይሁን። በዚህ ጊዜ በጎች እንደምትሸልት ሰምቻለሁ፤ እረኞችህ ከእኛ ጋር በነበሩበት ጊዜ፥ ያደረስንባቸው ጉዳት የለም፤ ቀርሜሎስ በነበሩበት ጊዜ ሁሉ፥ የጠፋባቸው አንዳች ነገር አልነበረም። የገዛ አገልጋዮችህን ጠይቅ፤ እነርሱም ይነግሩሃል። ስለዚህ እነዚህ ወጣቶቼ በፊትህ ሞገስ ያግኙ። አመጣጣችን በግብዣ ቀን በመሆኑ እባክህን ለአገልጋዮችህና ለልጅህ ለዳዊት የምትችለውን ያህል ስጥ።’ ” የዳዊት ሰዎች ከዚያ እንደ ደረሱም፥ በዳዊት ስም ይህንኑ መልእክት ለናባል ከተናገሩ በኋላ ምላሹን ይጠባበቁ ጀመር። ናባልም ለዳዊት አገልጋዮች እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ለመሆኑ ይህ ዳዊት ማነው? የእሴይስ ልጅ ማን ነው? በአሁኑ ጊዜ ከጌቶቻቸው የሚኰበልሉ አገልጋዮች ብዙ ናቸው። ታዲያ እንጀራዬንና ውሃዬን እንዲሁም በጎቼን ለሚሸልቱልኝ ሰዎች ያረድሁትን ፍሪዳ ከየት እንደመጡ ለማይታወቁ ሰዎች የምሰጠውስ ለምንድን ነው?” የዳዊት ሰዎችም ወደመጡበት ተመለሱ፤ እዚያም እንደ ደረሱ የተባሉትን ሁሉ ነገሩት። ዳዊትም ሰዎቹን፥ “በሉ ሁላችሁም ሰይፋችሁን ታጠቁ” አላቸው። ስለዚህ ሁሉም ሰይፋቸውን ታጠቁ፤ ዳዊትም የራሱን ታጠቀ። አራት መቶ ያህል ሰዎች ከዳዊት ጋር ሲወጡ መቶ ያህሉ ግን ጓዝ ለመጠበቅ ቀሩ። ከአገልጋዮቹ አንዱ ለናባል ሚስት ለአቢጌል እንዲህ አላት፤ “እነሆ፤ ዳዊት ሰላምታውን እንዲያቀርቡለት ከምድረበዳ ወደ ጌታችን መልእክተኞች ልኮ ነበር፤ እርሱ ግን በስድብ አዋረዳቸው። እነዚህ ሰዎች ግን እጅግ መልካም ነበሩ፤ ጉዳትም አላደረሱብንም፤ በዱር አብረናቸው በነበርንበት ጊዜም ሁሉ፥ ምንም ነገር አልጠፋብንም። በጎቻችንን እየጠበቅን አብረናቸው ባሳለፍነው ጊዜ ሁሉ፥ ቀንም ሆነ ሌሊት በዙሪያችን አጥር ሆነውን ነበር። አሁንም በጌታችንና በመላው ቤተሰቡ ላይ መከራ እያንዣበበ ስለሆነ፥ ምን እንደምታደርጊ አስቢበት፤ እርሱ እንደሆነ እንዲህ ያለ ባለጌ ሰው ስለሆነ፥ ማንም ደፍሮ የሚነግረው የለም።” አቢጌልም ጊዜ አላጠፋችም፤ ሁለት መቶ እንጀራ፥ ሁለት አቁማዳ የወይን ጠጅ፥ አምስት የተሰናዱ በጎች፥ አምስት መስፈሪያ የተጠበሰ እሸት፥ መቶ የወይን ዘለላና ዘቢብ፥ ሁለት መቶ ጥፍጥፍ የበለስ ፍሬ ወስዳ በአህዮች ላይ ጫነች። ከዚያም አገልጋዮቹን፥ “ቀድማችሁኝ ሂዱ፤ እኔም እከተላችኋለሁ” አለቻቸው፤ ለባሏ ለናባል ግን አልነገረችውም። እርሷም በአህያዋ ላይ ተቀምጣ ወደ ሸለቆው በምትወርድበት ጊዜ ዳዊትና ሰዎቹ ወደ እርሷ ወረዱ፤ እርሷም አገኘቻቸው። ዳዊትም እንዲህ ብሎ ነበር፤ “ምንም ነገር እንዳይጠፋበት የዚህን ሰው ሀብት በምድረ በዳ ያን ያህል መጠበቄ ለካ በከንቱ ኖሯል፤ ደግ በሠራሁ ይኸው ክፉ መለሰልኝ። ነገ ጠዋት የእርሱ ከሆነው ሁሉ አንድ ወንድ እንኳ በሕይወት ባስቀር እግዚአብሔር በዳዊት ላይ እንዲህ ያለውን ነገር ያድርግበት፥ ከዚህም የከፋ ይጨምርበት!”
1ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 25 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1ኛ መጽሐፈ ሳሙኤል 25:1-22
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos