1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 3
3
ንጉሥ ሰሎሞን ጥበብ ይሰጠው ዘንድ እግዚአብሔርን ስለ መለመኑ
(2ዜ.መ. 1፥3-12)
1ሰሎሞን የግብጽን ንጉሥ ሴት ልጅ በማግባት ከንጉሡ ጋር ወዳጅነት መሠረተ፤ እርሷንም አምጥቶ ቤተ መንግሥቱን፥ የጌታን ቤትና የኢየሩሳሌምን ዙሪያ ቅጽር ሠርቶ እስኪጨርስ ድረስ በዳዊት ከተማ አኖራት። 2በዚያን ጊዜ በጌታ ስም ቤተ መቅደሱ ገና አልተሠራም ነበር፤ ከዚህም የተነሣ በየኮረብታው መሥዋዕት ያቀርቡ ነበር። 3ሰሎሞን ጌታን ይወድ ነበር፤ የአባቱንም የዳዊትን መመሪያ ይጠብቅ ነበር፤ ይሁን እንጂ እንስሶችን እያረደ በተለያዩ ኰረብቶች ላይ መሥዋዕት ያቀርብ፥ ዕጣንም ያጥን ነበር።
4 #
ጥበ. 9፥1-18። ታላቁ መሠዊያ የሚገኘው በገባዖን ስለ ነበር አንድ ቀን ሰሎሞን መሥዋዕትን ለማቅረብ ወደዚያ ሄደ፤ ከዚህም በፊት በዚያ መሠዊያ ላይ አንድ ሺህ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል። 5በዚያች ሌሊት ጌታ በገባዖን ለሰሎሞን በሕልም ተገለጠለትና “ምን እንድሰጥህ ትፈልጋለህ?” አለው።
6ሰሎሞንም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “አገልጋይህ የነበረው አባቴ ዳዊት ደግ፥ ታማኝና ቅን ሰው በመሆኑ ጽኑ ፍቅርህን ስታሳየው ኖረሃል፤ ዛሬም በእርሱ እግር ተተክቶ በዙፋኑ የሚቀመጥ ልጅ በመስጠት ታላቅና ጽኑ የሆነውን የማያቋርጥ ፍቅርህን ገልጠህለታል። 7አቤቱ፥ ጌታ እግዚአብሔር ሆይ! እነሆ እኔ በዕድሜ አነስተኛ ነኝ፤ የአመራር ልምድም የለኝም፤ አንተ ግን በአባቴ እግር ተተክቼ እንድነግሥ ፈቃድህ ሆኖአል። 8እነሆ እኔ የአንተ እንዲሆን በመረጥከውና ከብዛቱ የተነሣ ሊቆጠር በማይችል ሕዝብ መካከል እገኛለሁ። 9ስለዚህ ክፉውንና በጎውን በመለየት ሕዝብህን በትክክለኛ ፍርድ ለመምራት የሚያስችለኝን ጥበብ ስጠኝ፤ ይህ ካልሆነ ግን ታላቅ ሕዝብህን እንዴት ልመራ እችላለሁ?”
10ሰሎሞን ይህን በመጠየቁ ጌታን ደስ አሰኘው። 11እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “ለራስህ ረጅም ዕድሜ ወይም ሀብት ለማግኘት ወይም ጠላቶችህ እንዲጠፉልህ መመኘት ሳይሆን በትክክለኛ ፍርድ ማስተዳደር የምትችልበትን ጥበብ ስለ ጠየቅህ፥ 12እነሆ የጠየቅኸውን አደርጋለሁ፤ እንዲያውም ማንም ሰው ከዚህ በፊት ካገኘውና ወደፊትም ሊያገኘው ከሚችለው የበለጠ ጥበብንና አስተዋይነትን እሰጥሃለሁ። 13ከዚህም በላይ አንተ ያልጠየቅከውንም ሁሉ ጨምሬ እሰጥሃለሁ፤ ይኸውም በዘመንህ ማንኛውም ሌላ ንጉሥ ያላገኘውን ብልጽግናና ክብር አበዛልሃለሁ። 14አባትህ ዳዊት እንዳደረገው በመንገዴ ብትሄድና ለእኔም ብትታዘዝ፥ ሕጌንና ትእዛዞቼንም ብትፈጽም ረጅም ዕድሜ እሰጥሃለሁ።”
15ሰሎሞን ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ እግዚአብሔር በሕልም ተገልጦ ያነጋገረው መሆኑን ተገነዘበ፤ ከዚህ በኋላ ሰሎሞን ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ ሄደ፤ በጌታ የቃል ኪዳን ታቦት ፊት ቆሞ የሚቃጠል መሥዋዕትንና የኅብረት መሥዋዕት አቀረበ፤ ለባለሟሎቹም ሁሉ ግብዣ አደረገ።
ጥበብ የሞላበት የሰሎሞን ፍትሕ
16አንድ ቀን ሁለት ጋለሞታዎች መጥተው በሰሎሞን ፊት ቀረቡ። 17ከእነርሱም አንደኛይቱ እንዲህ አለች፤ “ንጉሥ ሆይ! ይህች ሴትና እኔ በአንድ ቤት አብረን ስንኖር በዚያው በምንኖርበት ቤት ወንድ ልጅ ወለድኩ። 18እኔ በወለድኩ በሦስተኛው ቀን እርሷም ወንድ ልጅ ወለደች፤ በዚያ ቤት ውስጥ ከሁለታችን በቀር ሌላ ማንም አልነበረም። 19ከዕለታት አንድ ቀን ሌሊት በላዩ ላይ ተኝታበት ስለ ታፈነ ልጇ ሞተ። 20እኔ ተኝቼ ሳለሁ ሌሊት ተነሥታ ታቅፌው የተኛሁትን ልጄን ወስዳ በእርሷ አልጋ ላይ ካስተኛች በኋላ የሞተውን ልጇን አምጥታ በእኔ አልጋ ላይ በጐኔ አስተኛችው። 21በማግስቱ ማለዳ ተነሥቼ ልጄን ለማጥባት ስዘጋጅ የሞተ ሆኖ አገኘሁት፤ ትኲር ብዬ ስመለከተው እኔ የወለድኩት ልጅ አለመሆኑን ተገነዘብኩ።”
22ሁለተኛይቱ ሴት ግን፥ “አይደለም! በሕይወት ያለው ልጅ የእኔ ነው፤ የሞተው ግን የአንቺ ነው!” አለች።
የመጀመሪያይቱ ሴት “አይደለም! የሞተው የአንቺ ልጅ ነው፤ በሕይወት ያለው ግን የእኔ ልጅ ነው!” አለች።
በዚህም ዓይነት በንጉሡ ፊት ተከራከሩ።
23ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን “አንደኛዋ ‘በሕይወት ያለው ልጅ የእኔ ነው፤ የሞተው ግን የአንቺ ነው!’ ትላለች፤ ሌላይቱ ደግሞ ‘አይደለም! የአንቺ ልጅ ሞቷል፤ የእኔ ልጅ በሕይወት ያለው ነው!’ ትላታለች አለ።” 24ንጉሡም ሰይፍ እንዲያመጡለት አዘዘ፤ ሰይፍም አመጡለት። 25“በሉ እንግዲህ በሕይወት ያለውን ልጅ ለሁለት ቁረጡና ለእያንዳንዷ ሴት ግማሽ አካሉን ስጡ” ሲል አዘዘ።
26እውነተኛይቱ እናት ግን ለልጇ በመራራት አዝና፥ “ንጉሥ ሆይ! እባክህ ልጁን አትግደለው! ለእርሷ ይሰጣት!” አለች።
ሌላይቱ ሴት ግን “ለእኔም ለእርሷም አይሁን! ለሁለት ይቆረጥ!” አለች።
27ከዚህ በኋላ ሰሎሞን “ሕፃኑን አትግደሉት! እውነተኛይቱ እናት እርሷ ስለ ሆነች ለመጀመሪያይቱ ሴት ስጡአት!” ሲል አዘዘ።
28እስራኤላውያን ይህን የፍርድ ውሳኔ በሰሙ ጊዜ ሰሎሞን የሕዝብ ጉዳዮችን በትክክለኛ ፍርድ የሚወስንበትን ጥበብ እግዚአብሔር የሰጠው መሆኑን ስለ ተገነዘቡ ታላቅ አክብሮት ሰጡት።
Currently Selected:
1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 3: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ