የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 2

2
ዳዊት ለሰሎሞን የሰጠው የመጨረሻ መመሪያ
1ዳዊት የሚሞትበት ወቅት በተቃረበ ጊዜ ልጁን ሰሎሞንን ጠርቶ ይህን የመጨረሻ ትእዛዝ ሰጠው፤ 2“እነሆ እኔ ሰው ሁሉ እንደሚሞት የምሞትበት ጊዜ ተቃርቧል፤ እንግዲህ በርታ! ቆራጥ ሰው ሁን፤ 3#ዘዳ. 17፥18-19።አምላክህ ጌታ እንድታደርግ የሚያዝህን ሁሉ አድርግ፤ በምትሄድበት ስፍራ ሁሉ የምታደርገው ማንኛውም ነገር እንዲከናወንልህ በሙሴ አማካይነት በተሰጠው ሕግ የተጻፉትን የእግዚአብሔርን ሕግና ትእዛዝ፥ ሥርዓትና ፈቃድ ሁሉ ጠብቅ፤ 4#2ሳሙ. 7፥11-16፤ መዝ. 132፥11-12።በዚህ ሁሉ ነገር ታዛዥ ብትሆንለት፥ ‘ዘሮችህ በጥንቃቄ ተጠብቀው ቢኖሩ፥ በፍጹም ልባቸውና በፍጹም ነፍሳቸው በፊቴ በቅንነት ቢመላለሱ፥ በእስራኤል ዙፋን ላይ ነግሦ የሚገዛ ዘር አላሳጣህም’ ብሎ ጌታ የነገረኝን የተስፋ ቃል ይፈጽማል።
5 # 2ሳሙ. 3፥22-30፤ 20፥8-10። “የጽሩያ ልጅ ኢዮአብ የእስራኤል ሕዝብ የጦር መሪዎች ከነበሩት በኔር ልጅ አበኔርና በይቴር ልጅ ዐማሣ ላይ ያደረገውን ታስታውሳለህ፤ ሁለት በጦርነት ጊዜ ላፈሰሱት ደም በቀል በሰላም ጊዜ እነርሱን ገድሎ የወገቡን መታጠቂያ የእግሩን ጫማ በደም በክሎ በእኔ ላይ ምን እንዳደረገ ታውቃለህ። 6እንግዲህ ባለህ ጥበብ፥ ሊፈጸም የሚገባውን ነገር አድርግ፤ ዕድሜ ጠግቦ በሰላም እንዲሞት አትፍቀድለት።
7 # 2ሳሙ. 17፥27-29፤ 19፥32-41። “ከወንድምህ ከአቤሴሎም ፊት በሸሸሁ ጊዜ የቸርነት ሥራ ስላደረጉልኝ ለገለዓዳዊው ለባርዚላይ ልጆች ግን መልካም ነገር በማድረግ ተንከባከባቸው፤ በማዕድህም ከሚመገቡት መካከል ይሁኑ።
8 # 2ሳሙ. 16፥5-13፤ 19፥17-24። “ከዚህም ጋር መረሳት የሌለበት የብንያም ክፍል በሆነችው በባሑሪም ከተማ ውስጥ የሚኖረው የጌራ ልጅ ሺምዒ አለ፤ እርሱ ወደ ማሕናይም በሄድኩበት ቀን በእኔ ላይ የስድብ ውርጅብኝ አውርዶብኛል፤ ይሁን እንጂ በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ባገኘኝ ጊዜ እንደማላስገድለው በጌታ ስም ቃል ገብቼለት ነበር፤ 9አንተ ግን እርሱንም ከቅጣት ነጻ አታድርገው፤ ባለህ ጥበብ ምን መደረግ እንዳለበት አንተ ራስህ ታውቃለህ፤ በሞት የሚቀጣ መሆኑንም አትዘንጋ።”
የዳዊት መሞት
10 # የሐዋ. 2፥29። ዳዊት ሞተ፤ የእርሱ ከተማ በሆነችው በኢየሩሳሌምም ተቀበረ። 11#2ሳሙ. 2፥1-4፤ 5፥1-5።ዳዊት በኬብሮን ሰባት ዓመት፥ በኢየሩሳሌም ሠላሳ ሦስት ዓመት በድምሩ አርባ ዓመት በእስራኤል ላይ ነገሠ። 12#1ዜ.መ. 29፥23።ሰሎሞንም በአባቱ እግር ተተክቶ ነገሠ፤ የመንግሥቱም ሥልጣን እጅግ የጸና ሆነ።
የአዶንያስ መሞት
13የሐጊት ልጅ አዶንያስ ወደ ሰሎሞን እናት ወደ ቤርሳቤህ ሄደ፤ ቤርሳቤህም “ወደ እኔ የመጣኸው በሰላም ነውን?” ስትል ጠየቀችው።
እርሱም “አዎን በሰላም ነው የመጣሁት” ሲል መለሰ። 14ቀጠል አድርጎም “እኔ የምጠይቅሽ ጉዳይ አለኝ” አላት።
እርሷም “ጉዳይህ ምንድነው?” አለችው።
15አዶንያስም እንዲህ አላት፦ “ንጉሥ መሆን የሚገባኝ እኔ እንደ ነበርኩና ይህንንም በእስራኤል ምድር የሚኖር ሁሉ በተስፋ ይጠባበቅ እንደ ነበር አንቺ ራስሽ ታውቂያለሽ፤ ነገር ግን ጉዳዩ ከጌታ ስለ ተወሰነ ለእኔ መሰጠት የሚገባው መንግሥት ተላልፎ ለወንድሜ ሆኖአል። 16አሁንም የምጠይቅሽ አንድ ጉዳይ ስላለኝ እምቢ በማለት አታሳፍሪኝ።”
ቤርሳቤህም “ጉዳይህ ምንድነው?” ስትል ጠየቀችው።
17 # 1ነገ. 1፥3፤4። እርሱም “ንጉሥ ሰሎሞን አንቺን እምቢ እንደማይልሽ ዐውቃለሁ፤ ስለዚህ አቢሻግ ተብላ የምትጠራውን ሹኔማይት ልጃገረድ በሚስትነት እንዲድርልኝ እባክሽ አማልጅኝ” አላት።
18እርሷም “መልካም ነው! ይህን ለንጉሡ እነግርልሃለሁ” አለችው።
19ስለዚህም ቤርሳቤህ የአዶንያስን ጉዳይ ልትነግር ወደ ንጉሡ ገባች፤ ንጉሡም ከተቀመጠበት ተነሥቶ እናቱን እጅ በመንሣት ተቀበላት፤ እርሱም በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠ በኋላ ሌላ ዙፋን አስመጥቶ በቀኙ አስቀመጣት፤ 20እርሷም “እንድትፈጽምልኝ የምጠይቅህ አንድ ትንሽ ጉዳይ አለኝ፤ እባክህ እምቢ በማለት አታሳፍረኝ” አለችው።
ንጉሡም “እናቴ ሆይ! አላሳፍርሽም፤ ጉዳዩ ምንድነው” አላት።
21እርሷም “ወንድምህ አዶንያስ አቢሻግን ሚስት አድርጎ ያገባ ዘንድ ፍቀድለት” አለችው።
22ንጉሡም “አቢሻግን በሚስትነት እንድድርለት ብቻ ለምን ትጠይቂኛለሽ? መንግሥቴንም ጭምር እንድለቅለት ለምን አልጠየቅሽኝም? እርሱ እኮ ታላቅ ወንድሜ ነው፤ ለምን ለካህኑ አብያታርና ለኢዮአብም ልዩ አስተያየት እንዳደርግላቸው አትጠይቂላቸውም!” አላት። 23ከዚህ በኋላ ሰሎሞን በጌታ ስም እንዲህ ሲል ማለ፦ “አዶንያስ ይህን በማቀዱ በሕይወቱ እንዲከፈል ባላደርግ እግዚአብሔር ይፍረድብኝ በበለጠም ይቅጣኝ! 24#2ሳሙ. 7፥11-16።እግዚአብሔር በአባቴ በዳዊት ዙፋን ላይ አስቀምጦ መንግሥቴን የጸና አድርጎልኛል፤ ይህን መንግሥት ለእኔና ለዘሮቼ በመስጠት ቃሉን ጠብቆአል፤ እንግዲህ አዶንያስ በዚህ በዛሬው ቀን በሞት እንደሚቀጣ በሕያው ጌታ ስም እምላለሁ!”
25ስለዚህም አዶንያስን እንዲገድለው ንጉሥ ሰሎሞን ለዮዳሄ ልጅ ለበናያ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ በናያም ሄዶ አዶንያስን ገደለው።
የአብያታር መሳደድና የኢዮአብ በሞት መቀጣት
26 # 1ሳሙ. 22፥20-23። ንጉሥ ሰሎሞን ካህኑን አብያታርን፤ “ወደ ትውልድ አገርህ ወደ ዐናቶት ሂድ፤ አንተ በሞት ልትቀጣ ይገባህ ነበር፤ ነገር ግን የልዑል እግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት በአባቴ በዳዊት ፊት ትሸከም ስለ ነበርክ ከእርሱም ጋር የመከራው ሁሉ ተካፋይ ስለ ነበርክ እኔ አሁን አልገድልህም” አለው። 27#1ሳሙ. 2፥27-33።ስለዚህ ሰሎሞን አብያታርን የጌታ ካህን ሆኖ ከሚያገለግልበት የክህነት ሥልጣን ሽሮ አባረረው፤ በዚህም ዓይነት ጌታ በሴሎ ስለ ካህኑ ዔሊና ስለ ትውልዱ የተናገረው ቃል ተፈጸመ።
28በአንድ በኩል የአዶንያስ ደጋፊ፥ በሌላ በኩል ደግሞ የአቤሴሎም ተቃዋሚ የሆነው ኢዮአብ የተፈጸመውን ነገር ሁሉ ሰማ፤ ስለዚህም ሸሽቶ ወደ ጌታ ድንኳን ሄደ፤ በዚያም የመሠዊያውን ቀንዶች ይዞ ተማጠነ። 29ኢዮአብ ወደ ጌታ ድንኳን ሸሽቶ መሄዱንና በመሠዊያው አጠገብ መገኘቱን ሰሎሞን በሰማ ጊዜ፥ ኢዮአብን እንዲገድለው ለበናያ ትእዛዝ አስተላለፈ። 30እርሱም ወደ ጌታ ድንኳን ሄዶ ኢዮአብን “ከዚህ ድንኳን እንድትወጣ ንጉሡ አዞሃል” አለው።
ኢዮአብ ግን “አልወጣም! እዚሁ እሞታለሁ!” አለ።
በናያም ተመልሶ ኢዮአብ ያለውን ለንጉሡ ነገረው።
31ሰሎሞንም በናያን እንዲህ አለው፤ “ኢዮአብ እንዳለህ ግደለውና ቅበረው፤ በዚህ አኳኋን ኢዮአብ ካፈሰሰው ንጹሕ ደም በደል የእኔንና የአባቴን ቤት የነጻን አድርገን። 32#2ሳሙ. 3፥22-30፤ 20፥8-10።አባቴ ዳዊት ሳያውቅ ኢዮአብ ስለ ገደላቸው ስለ እነዚያ ሰዎች ደም ጌታ ኢዮአብን ይቀጣዋል፤ ኢዮአብ ከእርሱ የተሻሉትን ሁለት ንጹሓን ሰዎች ገድሎአል፤ እነርሱም የእስራኤል ጦር አዛዥ አበኔርና የይሁዳ ጦር አዛዥ ዐማሣ ነበሩ። 33ኢዮአብ እነዚህን ሰዎች በመግደሉ በእርሱ ላይ የተፈጸመበት ቅጣት በእርሱና በዘሮቹ ላይ ለዘለዓለም ጸንቶ ይኑር፤ በዙፋኑ ላይ ለሚቀመጡት ለዳዊት ዘሮች ግን የጌታ ሰላም ለዘለዓለም አይለያቸው።”
34ስለዚህ በናያ በታዘዘው መሠረት ኢዮአብን ገደለው፤ በቤቱም አጠገብ በሚገኘው በረሓ ተቀበረ። 35ንጉሥ ሰሎሞን በኢዮአብ ፈንታ በናያን የሠራዊቱ አዛዥ፥ በአብያታርም ፈንታ ሳዶቅን ካህን አድርጎ ሾመ።
የሺምዒ መሞት
36ከዚህ በኋላ ንጉሥ ሰሎሞን ሽምዒን አስጠርቶ እንዲህ ሲል አዘዘው፤ “በዚህ በኢየሩሳሌም የራስህን መኖሪያ ቤት ሠርተህ ተቀመጥ፤ ከዚያ ወደየትም አትሂድ፤ 37ከከተማይቱ ወጥተህ የቄድሮንን ወንዝ ተሻግረህ ብትገኝ በእርግጥ ትሞታለህ፤ ለደምህም ተጠያቂ ራስህ ነህ።”
38ሺምዒም “ንጉሥ ሆይ! ውሳኔህ ትክክል ነው፤ እኔ አገልጋይህ አንተ ጌታዬ እንዳልከው አደርጋለሁ” ሲል መለሰ፤ ስለዚህ በኢየሩሳሌም ብዙ ጊዜ ተቀመጠ።
39ከሦስት ዓመት በኋላ ግን ሁለቱ የሺምዒ አገልጋዮች የማዕካ ልጅ ወደ ሆነው አኪሽ ተብሎ ወደሚጠራው ወደ ጋት ንጉሥ ኰብልለው ሄዱ፤ ሺምዒም ባርያዎቹ በጋት መኖራቸው ተነገረው፤ 40አህያውን ጭኖ እነርሱን ለማግኘት በጋት ወደሚኖረው ወደ ንጉሥ አኪሽ ሄደ፤ እነርሱንም በዚያ ስላገኛቸው ወደ ቤቱ መልሶ አመጣቸው። 41ሰሎሞን ሺምዒ ከኢየሩሳሌም ወደ ጋት ሄዶ መመለሱን ሰማ። 42ንጉሡም ሽምዒን አስጠርቶ “ከኢየሩሳሌም እንዳትወጣ በጌታ ስም አስምዬህ አልነበረምን? ወጥተህ ብትገኝ ግን በእርግጥ እንደምትሞት አስጠንቅቄህ አልነበረምን? በዚህስ ተስማምተህ ትእዛዜን እንደምትፈጽም ቃል ገብተህልኝ አልነበረምን?” አለው። 43“ታዲያ፥ በጌታ ስም ከማልክ በኋላ ለምን መሐላውን አልጠበቅህም? ያዘዝኩህን ትእዛዝስ ለምን አላከበርክም? 44#2ሳሙ. 16፥5-13፤ 19፥17-24።በአባቴ በንጉሥ ዳዊት ላይ የፈጸምከውን በደል ሁሉ በደንብ ታውቃለህ፤ አንተ ስላደረግኸው ክፉ ነገር ጌታ ራሱ ይቀጣሃል፤ 45እኔን ንጉሥ ሰለሞንን ግን ጌታ ይባርከኛል፤ የዳዊት መንግሥትም ለዘለዓለም ጸንቶ ይኖራል።”
46ከዚህም በኋላ ለዮዳሄ ልጅ ለበናያ ሺምዒን እንዲገድል ትእዛዝ አስተላለፈ፤ በናያም ሄዶ ሺምዒን ገደለው፤ በዚህም ዓይነት መንግሥቱ በሰሎሞን እጅ የጸና ሆነ።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ