የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1ኛ መጽሐፈ ነገሥት 14

14
የኢዮርብዓም ወንድ ልጅ ሞት
1በዚያን ጊዜ የንጉሥ ኢዮርብዓም ወንድ ልጅ አቢያ ታሞ ነበር። 2ስለዚህ ኢዮርብዓም ሚስቱን እንዲህ አላት፦ “የእኔ ሚስት መሆንሽን ማንም እንዳያውቅ ልብስሽን ለውጠሽ ሌላ ሴት በመምሰል እኔ የእስራኤል ንጉሥ እንደምሆን የትንቢት ቃል የተናገረው ነቢዩ አኪያ ወደሚኖርባት ወደ ሴሎ ሂጂ።፤ 3ዐሥር እንጀራ፥ ጥቂት ሙልሙል ዳቦና አንድ ገንቦ ማር ውሰጂለት፤ ስለ ልጁ ሁኔታ እርሱ ይነግርሻል።”
4ስለዚህ የኢዮርብዓም ሚስት ይህን ሁሉ አዘጋጅታ በሴሎ ወደሚገኘው ወደ አኪያ ቤት ሄደች፤ ነቢዩ አኪያም በዕድሜው ከመሸምገሉ የተነሣ ዐይኖቹ ፈዘው ነበር። 5ይሁን እንጂ የኢዮርብዓም ሚስት ስለታመመው ልጇ ልትጠይቀው እንደምትመጣና ምን ሊነግራት እንደሚገባውም ጌታ አስቀድሞ ለነቢዩ አኪያ ገልጦለት ነበር።
የኢዮርብዓም ሚስት እዚያ በደረሰች ጊዜ ሌላ ሴት ለመምሰል ሞከረች። 6ነገር ግን ነቢዩ አኪያ ወደ በሩ ስትቀርብ የኮቴዋን ድምፅ ሰምቶ እንዲህ አላት፥ “ግቢ! የኢዮርብዓም ሚስት መሆንሽን ዐውቃለሁ፤ ሌላ ሴት ለመምሰል ስለምን ሞከርሽ? ለአንቺ እነግርሽ ዘንድ የታዘዝኩት አሳዛኝ ዜና አለ። 7ወደ ኢዮርብዓም ሂጂ፤ የእስራኤል አምላክ ጌታ የሚለውን ንገሪው፤ ቃሉም ይህ ነው፤ ‘ከሕዝብ መካከል መርጬ የሕዝቤ የእስራኤል መሪ አደረግኹህ። 8መንግሥትንም ከዳዊት ትውልድ ወስጄ ለአንተ ሰጠሁህ፤ ይሁን እንጂ አንተ ለእኔ ፍጹም ታማኝ ሆኖ ትእዛዞቼን እንደ ጠበቀውና እኔ ደስ የምሰኝበትን ነገር ሁሉ ያደርግ እንደነበረው እንደ አገልጋዬ እንደ ዳዊት ሆነህ አልተገኘህም። 9ይልቁንም ከአንተ በፊት መሪዎች ከነበሩ ሰዎች የከፋ ኃጢአት ሠራህ፤ እኔንም ትተህ ጣዖቶችና ከብረት የተቀረጹ ምስሎችን ለማምለክ በመሥራትህ ቁጣዬን አነሣሥተሃል፤ 10#1ነገ. 15፥29።በዚህ ምክንያት እነሆ፥ በኢዮርብዓም ቤት ላይ ክፉ ነገርን አመጣለሁ፤ ከቤቱም ነጻም ሆነ ባርያ፥ ወንድ ልጅንም ሁሉ ከእስራኤል አጠፋለሁ፤ ፋንድያን አቃጥለው እንደሚጨርሱት የኢዮርብዓምን ቤት አወድማለሁ። 11በከተማይቱ የሚሞተውን ማንኛውንም የቤተሰብህን አባል ውሾች ይበሉታል፤ ገላጣ በሆነው ገጠር የሚሞቱትንም አሞራ ይበላቸዋል፤ ይህን የተናገርኩ እኔ ጌታ ነኝ።’”
12አኪያም የሚናገረውን የትንቢት ቃል በመቀጠል ለኢዮርብዓም ሚስት እንዲህ አላት፤ “እንግዲህ አሁን ወደ ቤትሽ ተመልሰሽ ሂጂ፤ ወደ ከተማም እንደ ገባሽ ወዲያውኑ ልጁ ይሞታል። 13እስራኤላውያንም ሁሉ በማዘን አልቅሰው ይቀብሩታል፤ የእስራኤል አምላክ ጌታ የተደሰተበት ልጅ እርሱ ብቻ ስለ ሆነ ከኢዮርብዓምም ቤተሰብ መካከል ሥርዓተ ቀብር በሚገባ የሚፈጸምለት እርሱ ብቻ ይሆናል። 14ጌታ ለራሱ የኢዮርብዓምን ቤት የሚያጠፋ ንጉሥ ዛሬ ያስነሣል፤ ይኸውም አሁን ነው። 15ጌታ እስራኤልን ይቀጣል፤ እርሷም በውሃ ምንጭ ውስጥ እንደሚንቀጠቀጥ ሸምበቆ ትንቀጠቀጣለች፤ አሽሪም ተብላ የምትጠራውን ሴት አምላክ ጣዖት በመሥራት ስላስቆጡት፤ የእስራኤልንም ሕዝብ ከዚህች ለቀድሞ አባቶቻቸው ከሰጣቸው ለም ምድር ነቃቅሎ ከኤፍራጥስ ወንዝ ማዶ እንዲበታተኑ ያደርጋል። 16ኢዮርብዓም ኃጢአት ስለሠራና የእስራኤልንም ሕዝብ ወደ ኃጢአት ስለ መራ፥ ጌታ እስራኤልን ይተዋል።”
17የኢዮርብዓም ሚስት ወደ ቲርጻ ተመልሳ ወደ ቤትዋ ደጃፍ እንደ ደረሰች ወዲያውኑ ልጁ ሞተ። 18ጌታ ለአገልጋዩ ለነቢዩ አኪያ በነገረው መሠረት እስራኤላውያን በኀዘን አልቅሰው ቀበሩት።
የኢዮርብዓም መሞት
19ንጉሥ ኢዮርብዓም ያደረጋቸው ሌሎች ነገሮች ሁሉ፥ የተዋጋቸው ጦርነቶችና አገዛዙም እንዴት እንደ ነበር ሁሉም ነገር በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። 20ኢዮርብዓም ንጉሥ ሆኖ ኻያ ሁለት ዓመት ከገዛ በኋላ ሞቶ ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ልጁ ናዳብ ተተክቶ ነገሠ።
የይሁዳ ንጉሥ ሮብዓም
(2ዜ.መ. 11፥5—12፥15)
21የሰሎሞን ልጅ ሮብዓም በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው አርባ አንድ ዓመቱ ነበር፤ እርሱም መኖሪያውን ጌታ ከመላው የእስራኤል ግዛት መካከል ለስሙ መጠሪያ እንድትሆን በመረጣት ከተማ በኢየሩሳሌም አድርጎ ዐሥራ ሰባት ዓመት ገዛ፤ የሮብዓም እናት ናዕማ ተብላ የምትጠራ ዐሞናዊት ነበረች።
22የይሁዳ ሕዝብ በጌታ ፊት ክፉ አደረገ፤ የቀድሞ አባቶቹ ሲያደርጉት ከነበረው ይበልጥ በክፉ ሁኔታ በራሱ ላይ የጌታ ቁጣ አነሣሣ። 23#2ነገ. 17፥9፤10።ለባዕዳን አማልክትም የማምለኪያ ስፍራዎችን ሠሩ፤ በኮረብታዎች ላይና በዛፎች ጥላ ሥር የሚያመልኩአቸውን የድንጋይ ቅርጾችንና የአሼራን ምስሎች አቆሙ፤ 24#ዘዳ. 23፥17።ከዚህም ሁሉ የከፋ በእነዚያ ሕዝቦች የማምለኪያ ስፍራዎች የቤተጣዖት አመንዝራዎች ነበሩ፤ እስራኤላውያን ወደ አገሪቱ ለመግባት እየገፉ በሄዱ መጠን ጌታ ከፊታቸው ነቃቅሎ ያባረራቸው አሕዛብ ይፈጽሙት የነበረውን አሳፋሪ ነገር ሁሉ የይሁዳም ሕዝብ ይፈጽመው ነበር።
25 # 2ዜ.መ. 12፥2-8። ሮብዓም በነገሠ በአምስተኛው ዓመት የግብጽ ንጉሥ ሺሻቅ በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ ጣለ። 26#1ነገ. 10፥16፤17፤ 2ዜ.መ. 9፥15፤16።በቤተ መቅደስና በቤተ መንግሥት ተከማችቶ የነበረውንም ሀብት ሁሉ፥ ሰሎሞን ከወርቅ ያሠራቸውን ጋሻዎች ጭምር ዘርፎ ወሰደ። 27እነርሱንም ለመተካት ንጉሥ ሮብዓም ጋሻዎችን ከነሐስ አሠርቶ የቤተ መንግሥቱን ቅጽር በር የመጠበቅ ኀላፊነት ባላቸው የዘብ አለቆች እንዲጠበቁ አደረገ። 28ንጉሡ ወደ ቤተ መቅደሱ በመጣ ቍጥር፥ የቤተ መቅደሱ ዘበኞች ጋሻዎችን አንግበው ይቀበሉታል፤ ከሄደም በኋላ ጋሻዎቹን መልሰው በዘበኞች በሚጠበቁበት ክፍል ያኖሩአቸው ነበር።
29ንጉሥ ሮብዓም ያደረገው ሌላው ነገር ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ ተመዝግቦ ይገኛል። 30በዚህም ዘመን ሁሉ ሮብዓምና ኢዮርብዓም እርስ በርሳቸው በማያቋርጥ ጦርነት ላይ ነበሩ፤ 31ሮብዓም ሞተ፤ በዳዊት ከተማ በሚገኘው በነገሥታቱ መካነ መቃብር ተቀበረ፤ በእርሱም እግር ልጁ አቢያ ተተክቶ ነገሠ። የሮብዓም እናት ናዕማ ተብላ የምትጠራ ዐሞናዊት ነበረች።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ