1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 3:10-23

1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 3:10-23 መቅካእኤ

የእግዚአብሔር ጸጋ እንደተሰጠኝ መጠን እንደ ብልኅ ግንበኛ መሠረትን ጣልኩ፤ ሌላውም በዚያ ላይ ያንጻል። እያንዳንዱ ግን በዚያ ላይ እንዴት እንደሚያንጽ ይጠንቀቅ። ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልም፤ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ማንም ግን በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ፥ በብር፥ በከበሩ ድንጋዮች፥ በእንጨት፥ በሣር፥ በገለባ ቢያንጽ፥ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤ በእሳት ስለሚገለጥ፥ ያ ቀን በገሃድ ያሳያልና፤ የእያንዳንዱም ሥራ ምን መሆኑን እሳቱ ራሱ ይፈትነዋል። ማንም በዚያ ላይ ያነጸው ሥራ ቢጸናለት ሽልማቱን ይቀበላል፤ የማንም ሥራ የተቃጠለበት ቢሆን ይጎዳበታል፤ እርሱ ራሱ ግን ይድናል፤ ሆኖም ግን በእሳት አልፎ ይሆናል። የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደ ሆናችሁ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደሚኖርባችሁ አታውቁምን? ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነው፤ ይኼውም እናንተ ናችሁ። ማንም ራሱን አያታልል፤ ከእናንተ ማንም በዚህ ዓለም ጥበበኛ የሆነ ቢመስለው፥ ጥበበኛ ይሆን ዘንድ ሞኝ ይሁን። የዚህ ዓለም ጥበብ በእግዚአብሔር ዘንድ ሞኝነት ነው። እንደተጻፈውም፥ “እርሱ ጥበበኞችን በተንኰላቸው ይይዛቸዋል፤” ደግሞም “ጌታ የጥበበኞችን ሐሳብ ከንቱ እንደሆነ ያውቃል።” ስለዚህም፥ ሁሉ ነገር የእናንተ ነውና፥ ማንም በሰው አይመካ፤ ጳውሎስ ቢሆን አጵሎስም ቢሆን ኬፋም ቢሆን ዓለምም ቢሆን ሕይወትም ቢሆን ሞትም ቢሆን ያለውም ቢሆን የሚመጣውም ቢሆን፥ ሁሉ የእናንተ ነው፤ እናንተም የክርስቶስ ናችሁ፤ ክርስቶስም የእግዚአብሔር ነው።