ክርስቶስ ከሙታን እንደ ተነሣ የሚሰበክ ከሆነ፥ ከእናንተ አንዳንዶቹ እንዴት የሙታን ትንሣኤ የለም ይላሉ? የሙታን ትንሣኤ ከሌለማ ክርስቶስም አልተነሣም ማለት ነው። ክርስቶስም ካልተነሣ ስብከታችን ዋጋ ቢስ ነው፤ እምነታችሁም ከንቱ ነው። ደግሞም እግዚአብሔር ክርስቶስን ከሞት አስነሥቶታል ብለን በመመስከራችን፥ ሐሰተኞች የእግዚአብሔር ምስክሮች ሆነን ተገኝተናል፤ ሙታን የማይነሡ ከሆነ፥ ክርስቶስንም አላስነሣውም ማለት ነው፤ ምክንያቱም ሙታን ካልተነሡ፥ ክርስቶስም አልተነሣም። ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ነው፤ እናንተም እስከ አሁን ድረስ ከነኀጢአታችሁ አላችሁ ማለት ነው። በክርስቶስም ያንቀላፉት ጠፍተዋል ማለት ነው። ክርስቶስን ተስፋ ያደረግነው ለዚህች ሕይወት ብቻ ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ የምናሳዝን ነን። ነገር ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት ሁሉ በኵራት ሆኖ በእርግጥ ከሙታን ተነሥቶአል። ሞት በአንድ ሰው በኩል እንደመጣ፥ የሙታንም ትንሣኤ በአንድ ሰው በኩል ሆኖአልና። ሰዎች ሁሉ በአዳም እንደሚሞቱ፥ እንደዚሁም ሰዎች ሁሉ በክርስቶስ ሕያዋን ይሆናሉ፤ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፤ መጀመሪያ በኵራት የሆነው ክርስቶስ፥ በኋላም ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ የእርሱ የሆኑት። ከዚያም ግዛትን፥ ሥልጣንና ኃይልን ሁሉ ከደመሰሰ በኋላ መንግሥትን ለእግዚአብሔር አብ ሲያስረክብ፥ ያንጊዜ ፍጻሜ ይሆናል። ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ ሥር እስከሚያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና። የሚደመሰሰው የመጨረሻው ጠላት ሞት ነው፤ “ሁሉን ነገር ከእግሩ ሥር አስገዝቶለታል” ተብሏልና፤ ነገር ግን፥ ሁሉን ነገር አስገዛለት ሲል፥ ሁሉ ነገር በክርስቶስ ሥር እንዲገዛ ያደረገውን እግዚአብሔርን እንደማይጨምር ግልጽ ነው። ሁሉ ከተገዛለት በኋላ እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ እንዲሆን ወልድ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ለእርሱ ይገዛል።
1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15 ያንብቡ
ያዳምጡ 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15:12-28
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos