1ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል መግቢያ
መግቢያ
ብሉይ ኪዳን ከዕብራይስጥ ወደ ግሪክ በተተረጐመበት ጊዜ አንድ መጽሐፍ የነበረው ዜና መዋዕል ከርዝመቱ የተነሣ ለሁለት ተከፍሏል። የመጽሐፉ ስያሜ በዕብራይስጥ ቋንቋ “የዕለታቱ ቃላት፥ በቀኖች ወይም በጊዜያት የተመዘገቡ ክንዋኔዎች” ማለት ነው። ይህም ሐረግ በዜና መዋዕል ቀዳማዊ ምዕራፍ ሀያ ሰባት ቊጥር ሀያ አራት ላይ ተጠቅሶአል። የኢትዮጵያ የመጽሐፉ ስያሜ የዕብራይስጡን የሚከተል ነው። መጽሐፈ ዜና መዋዕል ከአዳም እስከ ፋርስ ንጉሥ እስከ ቂሮስ ድረስ ያለውን የቅዱስ መጽሐፍ ታሪክ በአጠቃላይ በውስጡ አካቶ የያዘ ነው። መጽሐፉ የመጽሐፈ ሳሙኤልንና የመጽሐፈ ነገሥትን ታሪክ በተለየ አኳኋን ዳግመኛ የሚተርክ ብቻ ሳይሆን የራሱ የሆነ ይዘትና መልእክት ያለው መጽሐፍ ነው። መጽሐፈ ዜና መዋዕል የተጠቀመባቸው ምንጭ መዛግብት አሉት፤ እነርሱም በእስራኤልና በይሁዳ የነገሥታት ታሪክ መጻሕፍት የተመዘገቡ ሰነዶች፥ ከተለያዩ የትውልድ ሐጎች የስም ዝርዝር የተጻፈባቸው መዝገቦች፥ የተለያዩ ነቢያት የጻፉዋቸው የታሪክ መጻሕፍት የተለያዩ ሌሎች ሰነዶች (2ዜ.መ. 23፥10-15) ናቸው። በአጻጻፍ ስልቱም የትውልድ ሐረግን የባለ ሥልጣኖች ስም ዝርዝርን፥ ንግግርን፥ ስብከትን፥ ጸሎትን እንዲሁም ትንቢታዊ የፍርድ ትንቢትን ተጠቅሞአል። መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ የእስራኤልን የትውልድ ታሪክ በመዘርዘር ይጀምራል፤ ከዚያም በኋላ በንጉሥ ዳዊት ላይ ትኩረቱን ያደርጋል። ይህም ንጉሥ ዳዊት በኬብሮን መንገሡን፥ ኢየሩሳሌምንም መያዙን፥ በልቡ ለጌታ ቤተ መቅደስን ለመሥራት መሻቱን፥ ጌታም ደም በማፍሰሱና የውጊያ ሰው በመሆኑ ለእርሱ ቤት እንደማይሠራለት መናገሩን፥ ስለ ሰሎሞን ንግግር ማድረጉን፥ የእስራኤል ማኅበር የሰሎሞንን ንግሥናን መቀበሉን ይተርካል። በአጠቃላይ መጽሐፉ ሁለት ዋና ዓላማ አለው፤ አንዱ በኢየሩሳሌም ያለው ቤተ መቅደስ ብቸኛ የአምልኮ ስፍራ መሆኑንና በእርሱም የሚደረገው ሥርዓተ አምልኮ ተቀባይነት ያለው እውነተኛ አምልኮ መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው። ሌላው እውነተኛዋ እስራኤል የምትተዳደረው ከይሁዳ በወጣው በዳዊት ቤተሰብ የዘር ሐረግ መሆኑን ማስገንዘብ ነው።
ዜና መዋዕል ቀዳማዊ በሁለት ዐብይት ክፍሎች ይከፈላል። አንደኛው ከምዕራፍ አንድ እስከ ዘጠኝ ያለው ሲሆን ስለ እስራኤል የትውልድ ሐረግ በዝርዝር የሚያስቀምጥ ነው። ሁለተኛው ከምዕራፍ ዐሥር እስከ ሀያ ዘጠኝ ያለው ሲሆን ስለ ንጉሥ ዳዊትና ስለፈጸማቸው የተለያዩ ተግባራት ያወሳል። ሁለተኛው ዐብይ ክፍል በሁለት ንዑስ ክፍሎች ይከፈላል። አንደኛው ከምዕራፍ ዐሥር እስከ ሀያ አንድ ያለው ሲሆን ስለ ንጉሥ ዳዊት ታሪክ ይናገራል። ሁለተኛው ደግሞ ከምዕራፍ ሀያ ሁለት እስከ ምዕራፍ ሀያ ዘጠኝ ያለው ሲሆን ከንጉሥ ዳዊት ወደ ንጉሥ ሰሎሞን ያለውን የሽግግር ጊዜ የሚገልጽ ነው።
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ባጠቃላይ ሲታይ በሰባት ዋና ዋና ሐሳቦች ላይ የተመሠረተ ነው። አንደኛው በኢየሩሳሌም ስለሚሠራው ቤተ መቅደስ የሚናር ነው፤ ቤተ መቅደሱ የእግዚአብሔር ማደርያ፥ የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ታቦት ማረፍያ፥ መሥዋዕት የሚቀርብበት፥ እስራኤል ሁሉ ጌታን በደስታ የሚያገለግሉበትና ጸሎታቸውን የሚያቀርቡበት ስፍራ ነው። ሁለተኛው ጽሑፉ ትኩረት ሰጥቶ ስለ ንጉሥ ዳዊትና ስለ ንጉሥ ሰሎሞን ስብእናና ስላከናወኑት የተለያዩ ተግባራት የሚገልጽ ነው። ሁለቱም ነገሥታት በንግሥናው ዙፋን ላይ በጌታ ተመርጠው መሾማቸው፥ ሁለቱም ለቤተ መቅደሱ ግንባታ ትኩረት መስጠታቸው፥ ሁለቱም አርባ ዓመት ሲገዙ ለጌታ ፍጹም ቀናዒና ታማኝ መሆናቸውን ይገልጻል። ሦስተኛው ዐብይ ሐሳብ ስለ ካህናቱ በተለይም ስለ ሌዋውያን ዘማሪዎች የሚናገረው ነው። ይህም የመዘምራን ቡድን በሦስት ተከፍሏል፤ የአሳፍ ልጆች የዖቤድ ኤዶም ልጆችና የኤማን ልጆች ናቸው። አራተኛው በሁለቱ ንጉሦች ዙርያ የእስራኤል ሕዝብ ምን ዓይነት ንቁና ሙሉ ተሳስትፎ እንደነበረው የሚያወሳ ነው፤ ይህም ሕዝቡ ለሁለቱም ነገሥታት ጠንካራ ድጋፍ መስጠቱን፥ የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም በሚመጣ ጊዜ በቤተ መቅደሱ ግንባታና በአምልኮው ሥርዓት ሙሉ ተሳትፎ ማድረጉን፥ ዳዊት ለሰሎሞን ባደረገው ንግግር የእስራኤል ሹማምንት ሁሉ መገኘታቸውን፥ ሰሎሞን በነገሠ ጊዜ እስራኤል ሁሉ መገኘቱን ይተርካል። አምስተኛው፥ መልካም የሠራ እንደሚሸለም ክፉ የሠራ እንደሚቀጣ የሚገልጽልንን ሐሳብ የሚያንጸባርቅ ነው። “የአባትህን አምላክ እወቅ በፍጹም ልብና በነፍስህ ፈቃድም አምልከው ብትፈልገው ታገኘዋለህ ብትተወው ግን ለዘለዓለም ይጥልሃል” የሚል መልእክት ይገኝበታል። እንዲህ ያለው የጽድቅ ፍርድ ከንጉሥ ሰሎሞን በኋላ በመጡት ነገሥታት ላይ እንደመመዘኛ ደንብ ሆኖ አገልግሎአል። ስድስተኛው፥ ስለ ንስሐ አጥብቆ የሚናገር ነው፤ ይህም በዳዊት ቤት ላያ ያመፁት የሰሜኑ ግዛት ንስሐ ገብተው ቢመለሱ እንኳ ጌታ በጻድቅ ፍርዱ ከሚቀጣቸው ይልቅ በምሕረቱ ይቅር እንደሚላቸው ይናገራል። ሕዝቅያስ ንስሐ ገብቶ ከጥፋት መዳኑ እንደ ምሳሌ ሊቀርብ ይችላል። ሰባተኛው ሐሳብ እስራኤላውያን የእግዚአብሔር መሻትና ወደ እርሱ ልባቸውን ማቅናት እንደሚገባቸው ያስተምራል። ይህም እግዚአብሔር የሚሻው ሕጉን መጠበቅ ብቻ ሳይሆን በፍጹም ልብ ለእርሱ መታዘዝንም ጭምር ነው።
የመጽሐፉ አጠቃላይ ይዘት
የአዳም ዘሮች እስከ ንጉሥ ሳኦል ድረስ (1፥1—9፥44)
የሳኦልና የልጆቹ ሞት (10፥1-14)
የዳዊት መንገሥና ኢየሩሳሌምን መያዙ (11፥1-9)
ዝነኞቹ የዳዊት ወታደሮች (11፥10—12፥40)
የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ኢየሩሳሌም መወሰዱ (13፥1—16፥43)
ቤተ መቅደስን የሚሠራ ሰሎሞን ነው (17፥1-27)
የዳዊት ወታደራዊ ድሎች (18፥1—20፥8)
ዳዊት የሕዝብ ቈጠራ በማድረጉ የእግዚአብሔር ቊጣ (21፥1-30)
ቤተ መቅደሱን ለመሥራት የተደረገ ዝግጅት (22፥1—28፥21)
ለቤተ መቅደሱ ሥራ የሕዝቡ ስጦታ (29፥1-20)
የሰሎሞን መንገሥ (29፥21-25)
የዳዊት ሞት (29፥26-30)
ምዕራፍ
Currently Selected:
1ኛ መጽሐፈ ዜና መዋዕል መግቢያ: መቅካእኤ
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ