ትንቢተ ሶፎንያስ 1
1
የእግዚአብሔር ፍርድ ቀን
1ሶፎንያስ የኩሺ ልጅ ሲሆን፥ ኩሺ የገዳልያ ልጅ፥ ገዳልያ የአማርያ ልጅ፥ አማርያ ደግሞ የንጉሥ ሕዝቅያስ ልጅ ነው፤ የአሞን ልጅ ኢዮስያስ የይሁዳ ንጉሥ በነበረበት ዘመን እግዚአብሔር ለሰፎንያስ የተናገረው ትንቢት እንደሚከተለው ነው። #2ነገ. 22፥1—23፥30።
2እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሁሉን ነገር ከምድር ላይ ፈጽሜ አጠፋለሁ፤ 3ሰዎችንና እንስሶችን፥ የሰማይ ወፎችንና የባሕር ዓሣዎችን እደመስሳለሁ፤ ክፉዎች እንዲገለባበጡ አደርጋለሁ፤ የሰውን ዘር ከምድር ላይ አጠፋለሁ፤ ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።
4“የኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ሕዝብ ሁሉ እቀጣለሁ፤ ከዚያም ቦታ የበዓል አምልኮ ርዝራዥንና የጣዖት ካህናትን መታሰቢያ አጠፋለሁ። #ኢሳ. 14፥29-31፤ ኤር. 47፥1-7፤ ሕዝ. 25፥15-17፤ ኢዩ. 3፥4-8፤ አሞጽ 1፥6-8፤ ዘካ. 9፥5-7። 5ጣራ ላይ ወጥተው ለፀሐይ፥ ለጨረቃና ለከዋክብት የሚሰግዱትን አጠፋለሁ፤ እኔን እያመለኩና በስሜ እየማሉ፥ ዘወር ብለው ደግሞ ሚልኮም ተብሎ በሚጠራው ጣዖት ስም የሚምሉትን እደመስሳለሁ። 6ከእኔ የራቁትን፥ እኔን መከተል የተዉትንና ወደ እኔም መጥተው እኔ እንድመራቸው ያልጠየቁኝን አጠፋለሁ።”
7የእግዚአብሔር ፍርድ ቀን ስለ ቀረበ በእግዚአብሔር ፊት ዝም በሉ፤ እግዚአብሔር ሕዝቡን ለመሥዋዕት እንደሚታረድ እንስሳ አሳልፎ ለመስጠት እየተዘጋጀ ነው፤ ይሁዳን የሚበዘብዙ ጠላቶችንም ለይቶ አዘጋጅቶአል። 8እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቤን አሳልፌ በምሰጥበት ቀን ልዑላኑንና ባለ ሥልጣኖችን እንዲሁም የባዕድ ባህል የሚከተሉትን ሁሉ እቀጣለሁ። 9በዚያን ቀን በአሕዛብ የአምልኮ ሥርዓት በቤተ መቅደሱ መድረክ ላይ እየዘለሉ የሚያመልኩትንና የጌታቸውን ቤት በዓመፅና በማታለል በተገኙ ዕቃዎች የሚሞሉትን ሰዎች እቀጣለሁ።”
10እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በዚያን ቀን ከኢየሩሳሌም ቅጽር በዓሣ በር በኩል ኡኡታ ይሰማል፤ ከአዲሱም አደባባይ የዋይታ ድምፅ ያስተጋባል፤ በኰረብቶችም አካባቢ ከፍተኛ ሽብር ይሰማል። 11እናንተ ከከተማው በታችኛው ክፍል የምትኖሩ ሁሉ ነጋዴዎቻችሁ ስለሚወገዱና በብር የሚነግዱ ሁሉ ስለሚጠፉ ይህን ድምፅ በምትሰሙበት ጊዜ ‘ዋይ! ዋይ!’ እያላችሁ አልቅሱ።
12“በዚያን ቀን መብራት ይዤ ኢየሩሳሌምን እፈትሻለሁ፤ በመንደላቀቅ ኑሮ በአተላ ውስጥ አቅርሮ እንደ ቀረ የወይን ጠጅ የሆኑትንና ‘እግዚአብሔር በጎም ሆነ ክፉ ነገር አያደርግም’ የሚሉትን እቀጣለሁ። 13ሀብታቸው ይዘረፋል፤ ቤቶቻቸውም ይፈርሳሉ፤ በዚያን ጊዜ ቤት ይሠራሉ፤ ነገር ግን አይኖሩበትም፤ ወይንም ይተክላሉ፤ ነገር ግን የወይኑን ጠጅ አይጠጡም።”
14ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአል፤ አመጣጡም እየፈጠነ ነው፤ ያ ቀን እጅግ አስፈሪ ነው፤ በዚያን ቀን የሚሰማው ድምፅ አስከፊ ነው፤ ተዋጊው በከፍተኛ ድምፅ ይጮኻል። 15ያ ዕለት የቊጣ፥ የመከራና የጭንቀት፥ የጥፋትና የመፍረስ፥ የጨለማና የጭጋግ፥ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን ይሆናል፤ 16በዚያን ቀን በተመሸጉት ከተሞችና በረጃጅም ግንቦች ላይ የጦርነት መለከትና የማስጠንቀቂያ ድምፅ ይሰማል።
17እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ኃጢአት በመሥራት እኔን ስለ በደሉ እንደ ዕውሮች እስኪደናበሩ ድረስ በሰዎች ላይ ታላቅ መከራ አመጣለሁ፤ ደማቸው እንደ ትቢያ ይፈስሳል፤ ሬሳቸውም እንደ ጒድፍ የትም ይጣላል።”
18እግዚአብሔር ቊጣውን በሚገልጥበት በዚያን ቀን ሰዎችን ብራቸውና ወርቃቸው ሊያድናቸው አይችልም፤ እንደ እሳት ባለው ቅናቱ ምድር ሁሉ ትጠፋለች፤ ይህም የሚሆነው በዓለም የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ በድንገት የሚያልቁ ስለ ሆነ ነው።
Currently Selected:
ትንቢተ ሶፎንያስ 1: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997