ሰዎች ሁሉ ለገዢዎችና ለባለሥልጣኖች በትሕትና እንዲታዘዙ፥ መልካም ሥራን ሁሉ ለመሥራት ዝግጁዎች እንዲሆኑ፥ በማንም ላይ ክፉ ነገር እንዳይናገሩ አሳስባቸው፤ ይልቅስ ከሰው ጋር የማይጣሉና ገሮች፥ ፍጹም ትሕትናን ለሰው ሁሉ የሚያሳዩ ይሁኑ፤ እኛም ከዚህ በፊት ሞኞች፥ የማንታዘዝ እምቢተኞች፥ መንገዳችንን የሳትን ተላላዎች፥ ለልዩ ልዩ ፍትወትና ሥጋዊ ደስታ የተገዛን፥ በተንኰልና በምቀኝነት የምንኖር፥ የተጠላንና እርስ በርሳችንም የምንጣላ ነበርን። ነገር ግን የመድኀኒታችን የእግዚአብሔር ደግነትና ፍቅር የተመላ ርኅራኄ በተገለጠ ጊዜ፥ እኛ በሠራነው የጽድቅ ሥራ ሳይሆን ራሱ በምሕረቱ አዳነን፤ ያዳነንም በአዲስ ልደት መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት በተገኘው መታደስ ነው። እግዚአብሔር በለጋሥነቱ በአዳኛችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት መንፈሱን በብዛት አፈሰሰልን። ይህንንም ያደረገው በጸጋው ጸድቀን በተስፋ የምንጠባበቀውን የዘለዓለምን ሕይወት እንድንወርስ ነው። ይህ የታመነ አባባል ነው። በእግዚአብሔር ያመኑ ሰዎች ለመልካም ሥራ እንዲተጉ ይህን ነገር ሁሉ በጥብቅ እንድታስገነዝብ እፈልጋለሁ፤ ይህም ነገር መልካምና ለእያንዳንዱ ሰው ጠቃሚ ነው። ነገር ግን ከሞኞች ክርክር፥ ከትውልዶች ቈጠራ፥ ከጭቅጭቅ፥ በሕግ ምክንያት ከሚነሣው ጠብ ራቅ፤ እነዚህ ነገሮች ጥቅም የሌላቸውና ዋጋቢሶች ናቸው። መለያየትን የሚያመጣውን ሰው አንድ ጊዜ ወይም ሁለት ጊዜ ከመከርከው በኋላ ከእርሱ ራቅ። እንዲህ ያለው ሰው ጠማማና ኃጢአተኛ ነው፤ እርሱ በራሱ ላይ የፈረደ መሆኑን ዕወቅ። አርጤማስን ወይም ቲኪቆስን ወደ አንተ በምልክበት ጊዜ አንተ ወደ ኒቆጵልዮን ወደ እኔ ለመምጣት ፍጠን፤ እኔ ክረምቱን እዚያ ለማሳለፍ ወስኜአለሁ። ሕግ ዐዋቂው ዜናስና አጵሎስ ጒዞአቸውን እንዲጀምሩ አድርጋቸው፤ በሚያስፈልጋቸውም ነገር ሁሉ ርዳቸው። የእኛም ሰዎች ደግሞ ያለ ፍሬ እንዳይቀሩና የኑሮን ችግር ማቃለል እንዲችሉ መልካም ሥራን መሥራት ይማሩ። ከእኔ ጋር ያሉት ሁሉ ሰላምታ ያቀርቡልሃል፤ በእምነት ከእኛ ጋር ተካፋይ ለሆኑ ወዳጆቻችን ሁሉ ሰላምታ አቅርብልን። የእግዚአብሔር ጸጋ ከሁላችሁም ጋር ይሁን።
ወደ ቲቶ 3 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ወደ ቲቶ 3:1-15
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች