መኃልየ መኃልይ 8

8
1ምነው አንተ የእናቴን ጡት እንደ ጠባ
እንደ ወንድሜ በሆንክልኝ፤
በመንገድ ላይ አግኝቼ ብስምህ
ማንም ሰው አይንቀኝም ነበር፤
2ወደ ወላጅ እናቴ ቤት ባስገባሁህ ነበር፤
በዚያም ስለ ፍቅር ባስተማርከኝ ነበር፤
በሮማን ፍሬዬ ጭማቂ የጣፈጠውን
መልካሙን የወይን ጠጅ ባጠጣሁህ ነበር።
3ግራ እጁን ያንተርሰኛል፤
በቀኝ እጁ ያቅፈኛል።
4እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅ ሆይ!
ፍቅር ራሱ ወዶ እስኪነሣ ድረስ
ቀስቅሳችሁ እንዳታስነሡት ዐደራ እላችኋለሁ።
ሰባተኛ መዝሙር
የፍቅር ውዳሴ
የሙሽራይቱ ጓደኞች
5በወዳጅዋ ትከሻ ላይ ደገፍ ብላ
ከበረሓ የምትመጣ ይህች ማን ናት?
ሙሽራይቱ
ዱሮ እናትህ አንተን አምጣ በወለደችበት
በፖም ዛፍ ሥር ቀስቅሼ አስነሣሁህ።
6በዘለዓለማዊ ፍቅር በልብህ ውስጥ እንደ ማኅተም አትመኝ፤
በክንድህም እንደ ማኅተም እኔን ብቻ ያዘኝ፤
ፍቅር እንደ ሞት የበረታች ናት፤
ቅናትም እንደ መቃብር የከፋች ናት፤
የእሳትዋ ወላፈን እንደ እግዚአብሔር ወላፈን ነው።
7የውሃ ብዛት የፍቅርን እሳት ሊያጠፋ አይችልም፤
ጐርፍም ጠራርጎ ሊወስዳት አይችልም፤
ሰው ባለው ሀብት ሁሉ ፍቅርን ለመግዛት ቢሞክር
ፍቅር በገንዘብ ስለማትገኝ ሰዎች ይዘባበቱበታል።
የሙሽራይቱ ወንድሞች
8ገና ጡት ያላወጣች ትንሽ እኅት አለችን፤
ለጋብቻ ብትጠየቅ ለዚህች ለእኅታችን የምናደርግላት
ምንድን ነው?
9እርስዋ ቅጽር ብትሆን ኖሮ
የብር ማማ እንሠራላት ነበር፤
እርስዋ የቅጽር በር ብትሆን ኖሮ
ከሊባኖስ ዛፍ ሳንቃ የታነጸ መዝጊያ እንሠራላት ነበር።
ሙሽራይቱ
10እነሆ፥ እኔ ቅጽር ነኝ፤
ጡቶቼም እንደ ቅጽር ማማዎች ናቸው፤
ከውዴ ጋር ስሆን እርሱ ደስታንና ሰላምን ያገኛል።
የሙሽራይቱ ጓደኞች
11ሰሎሞን በባዓልሃሞን የወይን ተክል ቦታ ነበረው፤
የወይኑንም ተክል ቦታ ለአትክልተኞች አከራየው፤
እያንዳንዳቸውም አንድ ሺህ ብር ያመጡለት ነበር፤
ሙሽራይቱ
12እኔ የግሌ የሆነ የወይን ተክል ቦታ አለኝ፤
ሰሎሞን ሆይ! አንተ አንድ ሺህ ብር፥
አትክልተኞቹ ሁለት መቶ ብር ልትወስዱ ትችላላችሁ።
ሙሽራው
13አንቺ የእኔ ሙሽራ ሆይ! በአትክልት ቦታ ሆነሽ ጓደኞቼ ድምፅሽን ለመስማት ይፈልጋሉ፤
እስቲ ለእኔ ድምፅሽን አሰሚኝ።
ሙሽራይቱ
14ውዴ ሆይ! ፈጥነህ ወደ እኔ ና፤
የቅመም ተክሎች በሚበቅሉባቸው ተራራዎች ላይ
የሚዘል አጋዘን ወይም የዋልያ ግልገል ምሰል።

ማድመቅ

ያጋሩ

ኮፒ

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ