መኃልየ መኃልይ 7
7
ሙሽራው
1ልዕልት ሆይ!
እግሮችሽ በነጠላ ጫማ ውስጥ ሲታዩ እንዴት ያምራሉ!
ዳሌዎችሽ በብልኅ አንጥረኛ እጅ የተሠራ የዕንቊ ጌጥ ይመስላሉ፤
2እንብርትሽ በወይን ጠጅ የተሞላ ብርሌ ይመስላል፤
ወገብሽ ዙሪያውን በውብ
አበባ የታሰረ የስንዴ ነዶ ይመስላል።
3ሁለቱ ጡቶችሽ መንታ የዋልያ ግልገሎችን ይመስላሉ።
4አንገትሽ በዝሆን ጥርስ እንዳጌጠ ግንብ ነው፤
ዐይኖችሽ በታላቅዋ ከተማ በሐሴቦን የቅጽር በር አጠገብ
የሚገኙ የውሃ ኲሬዎችን ይመስላሉ።
አፍንጫሽ ወደ ደማስቆ አቅጣጫ ለመመልከት
የተሠራውን የሊባኖስ ግንብ ይመስላል።
5የራስሽ ቅርጽ እንደ ቀርሜሎስ ተራራ ነው፤
ዞማው ጠጒርሽም የሐር ጒንጒን የመሰለ ነው።
ንጉሡም በሹሩባሽ ውበት ተማርኮአል።
6ውዴ ሆይ! እንዴት ያማርሽ ነሽ?
እንዴትስ ውብ ነሽ?
ፍቅርሽ እንዴት ያስደስታል?
የጋራ ፍቅራችን
7ቁመናሽ የዘንባባ ዛፍ ይመስላል፤
ጡቶችሽም ዘለላውን ይመስላሉ።
8በዘንባባው ዛፍ ላይ ወጥቼ
ፍሬውን መልቀም እወዳለሁ፤
ጡቶችሽ እንደ ወይን ዘለላ ዕቅፍ ይሁኑ፤
የእስትንፋስሽ መዓዛ እንደ ፖም ፍሬ ሽታ ነው።
9የአፍሽም መዓዛ እንደ መልካም ወይን ጠጅ ነው።
ሙሽራይቱ
እንግዲያውስ መልካሙ የወይን ጠጅ
በውዴ ከንፈሮችና ጥርሶች መካከል
እየተንቆረቆረ በዝግታ ይውረድ።
10እኔ የውዴ ነኝ፤
የእርሱም ምኞት ወደ እኔ ነው።
11ውዴ ሆይ! ና፤ ከከተማ ወጥተን ወደ ገጠር እንሂድ፤
ሌሊቱን በዚያ እናሳልፍ።
12ማልደንም ወደ ወይኑ ተክል ቦታ እንሂድ፤
የወይኑ አበባ ፈክቶ እንደ ሆነ፥
ሮማኑም አብቦ እንደ ሆነ እንይ፤
በዚያም ፍቅሬን እገልጥልሃለሁ።
13የእንኰይ ፍሬ መዓዛና እንዲሁም ደስ የሚያሰኙ
ልዩ ልዩ ፍራፍሬዎች ደጃችንን ሞልተውታል።
ውዴ ሆይ! ከነዚህም ፍሬዎች
የበሰሉትንና አዲስ የተቀጠፉትን ለአንተ አኑሬልሃለሁ።
Currently Selected:
መኃልየ መኃልይ 7: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997