መኃልየ መኃልይ 6
6
አምስተኛ መዝሙር
ፍቅር ከሁሉ ይመረጣል
የሙሽራይቱ ጓደኞች
1አንቺ ከሴቶች ሁሉ የተዋብሽ!
ወዳጅሽ ወዴት ሄደ?
እኛም አብረንሽ እንድንፈልገው
የሄደበትን አቅጣጫ ንገሪን።
ሙሽራይቱ
2ውዴ የበጎቹን መንጋ ለማሰማራትና
ውብ አበባን ለመቅጠፍ፥
የሽቶ ዕፀዋት ወደሚገኙበት የአትክልት ቦታው ወርዶአል።
3ውዴ የእኔ ነው፤ እኔም የእርሱ ነኝ፤
በሱፍ አበባዎች መካከል መንጋውን ያሰማራል።
ሙሽራው
4ፍቅሬ ሆይ! እንደ ቲርጻ ከተማ የተዋብሽ ነሽ፤
እንደ ኢየሩሳሌምም እጅግ ያማርሽ ነሽ፤
የጦር ዓርማ ይዞ እንደሚጓዝ ሠራዊት
የሚያስፈራ ግርማ አለሽ።
5እባክሽ ዐይኖችሽን ከእኔ ላይ አንሺ፤
እነርሱ እኔን ማርከው እስረኛ አድርገውኛል።
ጠጒርሽ ከገለዓድ ተራራ ላይ እንደሚወርድ
የፍየል መንጋ ነው።
6ጥርሶችሽ በመካከላቸው ምንም መኻን ሳይኖርባቸው
መንታ መንታ እንደሚወልዱና በውሃ እንደ ታጠቡ
ነጫጭ የበጎች መንጋ ደስ ያሰኛሉ።
7ሁለቱ ጒንጮችሽ በፊትሽ ዐይነ ርግብ ውስጥ ሲታዩ
ለሁለት የተከፈሉ የሮማን ፍሬ ፍንካች ይመስላሉ።
8ሥልሳ ንግሥቶች፥ ሰማኒያ ቊባቶችና
ከቊጥር በላይ የሆኑ ቈነጃጅት አሉ፤
9እኔ ግን የምወደው አንዲትዋን ብቻ ነው፤
እርስዋም ምንም እንከን የሌለባት
እንደ ርግብ የተዋበች ናት፤
እርስዋ ለእናትዋ አንድ ናት፤
የወለደቻት እናትዋም ከሁሉ አብልጣ ታፈቅራታለች፤
ቈነጃጅትም እርስዋን እየተመለከቱ ያወድሱአታል፤
ነገሥታትና የንጉሥ ቊባቶች ያሞግሡአታል።
10ይህች እንደ ብርሃን የምትፈልቅ፥
እንደ ጨረቃ የምትደምቅ፥
እንደ ፀሐይ የምታበራ፥
የጦር ዓርማ ይዞ እንደሚጓዝ ሠራዊት
ግርማዋ የሚያስፈራ፥
እርስዋ ማን ናት?
11በሸለቆ የተተከሉትን ተክሎች ልምላሜ አይ ዘንድ
ወይኑ አቈጥቊጦ፥ ሮማኑም አብቦ እንደ ሆነ ልመለከት
ወደ ለውዝ ተክል ቦታ ወረድኩ፤
12ሳላስበው፥ ምኞቴ በሠረገላ ላይ
እንደ ልዑል አስቀመጠኝ።
የሙሽራው ጓደኞች
13አንቺ ሱላማዊት ሆይ! ነዪ ተመለሺ፤
በደንብ አድርገን እንድንመለከትሽ ነዪ ተመለሺ።
ሙሽራይቱ
ሱላማጢስን በሁለት ሠራዊት መካከል እንደሚደረግ ጭፈራ
የምትመለከቱአት ለምንድን ነው?
Currently Selected:
መኃልየ መኃልይ 6: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997