መኃልየ መኃልይ 5
5
ሙሽራው
1እኅቴ ሙሽራዬ ሆይ!
እነሆ ወደ አትክልት ቦታዬ ገባሁ፤
ከርቤዬንና የሽቶ አበባዎቼን ለቀምኩ፤
የማር ሰፈፌን ከወለላው ጋር ተመገብኩ፤
የወይን ጠጄንና ወተቴንም ጠጣሁ።
ሠርገኞች
ወዳጆቼ ሆይ!
በፍቅር እስክትረኩ ድረስ
ብሉ፥ ጠጡ።
ሙሽራይቱ
2እኔ ተኝቼአለሁ፤ ልቤ ግን ነቅቶአል፤
ውዴ እንዲህ እያለ በር ሲያንኳኳ ሰማሁት፤
“ውድ እኅቴ የሆንሽ ሙሽራዬ ሆይ!
እንከን የሌለብሽ ርግቤ ሆይ!
እባክሽ በሩን ክፈችልኝ፤
ራሴ በጠል ርሶአል
ጠጒሬም በሌሊት ካፊያ ረስርሶአል።”
3ልብሴን አውልቄአለሁ፤
ታዲያ፥ እንደገና ልልበስን?
እግሬንም ታጥቤአለሁ፤
ታዲያ፥ እንዴት እንደገና ላሳድፈው?
4ውዴ በመተላለፊያው በኩል
እጁን ወደ ውስጥ ዘረጋ፤
አንጀቴም ስለ እርሱ ተንሰፈሰፈ።
5ስለዚህ ለውዴ በሩን ልከፍትለት ተነሣሁ፤
የበሩን መክፈቻ እጀታ ስይዘው
እጆቼ ከርቤ አንጠባጠቡ፤ ጣቶቼም የከርቤ ፈሳሽ አፈሰሱ።
6ለውዴ በሩን ከፈትኩለት።
ውዴ ደርሶ ተመለሰ፤
ድምፁን ለመስማት እጅግ ጓጉቼ ነበር፤
አጥብቄ ፈለግኹት፤ ነገር ግን ላገኘው አልቻልኩም፤
ጠራሁት፤ እርሱ ግን አልመለሰልኝም።
7እየተዘዋወሩ ከተማውን የሚጠብቁ ሰዎች አገኙኝ፤
ደብድበውም አቈሰሉኝ፤
የከተማውን ቅጽር የሚጠብቁ ዘበኞች
መጐናጸፊያዬን ገፈው ወሰዱብኝ።
8እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት
ውዴን ያገኛችሁት እንደ ሆነ
እኔ ከፍቅሩ የተነሣ መታመሜን እንድትነግሩት
ዐደራ እላችኋለሁ።
የሙሽራይቱ ጓደኞች
9አንቺ ከሴቶች ሁሉ የተዋብሽ ሆይ!
በውኑ የአንቺ ፍቅረኛ ከሌሎች የተለየ ነውን?
ስለ እርሱ ይህን ያኽል ዐደራ የምትዪን?
እርሱ ከሌሎች የሚለይበት ነገር ምንድን ነው?
ሙሽራይቱ
10ውዴ እጅግ የተዋበና ጤነኛ ነው፤
ከዐሥር ሺህ ወንዶች መካከል
እርሱን የሚመስለው የለም።
11የእርሱ ራስ የወርቅ ሉል ይመስላል፤
ጠጒሩም ዞማና እንደ ቊራ የጠቆረ ነው።
12ዐይኖቹ በወንዝ አጠገብ እንደሚታዩና
በወተት የታጠቡ እንደሚመስሉ ርግቦች ያምራሉ።
13የጉንጮቹ ማማር ጣፋጭ ሽታ ያላቸው የቅመማቅመም
ዕፀዋት እንደሚገኙበት የአትክልት ቦታ ነው፤
ከንፈሮቹ መዓዛው የሚጣፍጥ የከርቤ ሽቶ
እንደሚያፈሱ የአሸንድዬ አበባዎች ናቸው።
14ክንዶቹ የዕንቊ ፈርጥ እንዳለበት የወርቅ ዘንግ ያምራሉ፤
አካሉ በሰንፔር ዕንቊ እንዳጌጠ የዝሆን ጥርስ ነው።
15እግሮቹ በወርቅ መሠረት ላይ የተተከሉ
የዕብነበረድ ምሰሶዎችን ይመስላሉ፤
መልኩ በሊባኖስ ዛፍ እንዳጌጠ
እንደ ሊባኖስ ተራራ ነው።
16አፉ እንደ ማር. የጣፈጠ ነው፤
ሁለንተናውም የደስ ደስ አለው፤
እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት
እንግዲህ ውዴና ወዳጄ ይህን የመሰለ ነው።
Currently Selected:
መኃልየ መኃልይ 5: አማ05
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ
© The Bible Society of Ethiopia, 2005
© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997