የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መኃልየ መኃልይ 3

3
1ሌሊቱን ሙሉ በአልጋዬ ላይ ሆኜ፥
ልቤ የምትወደውን ፈለግኹት፤
ፈለግኹት፤ ነገር ግን አላገኘሁትም።
2አሁን ተነሥቼ በከተማው አካባቢ
በመንገዶችና በአደባባዮች መካከል
ልቤ የምትወደውን እፈልገዋለሁ፤
ፈለግኹት፤ ነገር ግን አላገኘሁትም።
3እየተዘዋወሩ ከተማውን የሚጠብቁ ሰዎች አገኙኝ፤
እኔም “ልቤ የምትወደውን አይታችኋልን?” ብዬ ጠየቅኋቸው።
4ከእነርሱም ጥቂት አለፍ እንዳልኩ
ልቤ የምትወደውን አገኘሁት፤
እንዳያመልጠኝም አጥብቄ ያዝኩት፤
ወደ እናቴም ቤት ወሰድኩት፤
እኔ ወደተወለድኩበትም ክፍል አስገባሁት።
5እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ!
ፍቅር ራሱ ፈቅዶ እስኪነሣ ድረስ
ቀስቅሳችሁ እንዳታስነሡት፤
በፈጣን አጋዘንና በምድረ በዳ ዋልያ ስም
ዐደራ እላችኋለሁ።
ሦስተኛ መዝሙር
ጋብቻ
ሠርገኞች፦
6እንደ ነጋዴ ቅመም መልካም መዓዛ ያላት፥
በዕጣንና በከርቤ መዓዛ እየተወገደ እንደ ጢስ ዐምድ ሆና
ያቺ ከበረሓ የምትመጣው ማን ናት? #3፥6 ያ ከበረሓ የሚመጣው ምንድን ነው? ወይም ያቺ ከበረሓ የምትመጣው ማን ናት?
ሙሽራይቱ፦
7እነሆ፥ የሰሎሞን ሠረገላ እየመጣች ነው፤
ከእስራኤል ኀያላን መካከል የተመረጡ
ሥልሳ የክብር ዘበኞች አጅበዋታል፤
8ሁሉም በሰይፍ አያያዝ የሠለጠኑና
በጦርነትም የተፈተኑ ናቸው፤
በሌሊት ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ለመመከት
እያንዳንዱ ሰይፉን እንደ ታጠቀ ያድራል።
9ንጉሥ ሰሎሞን በሠረገላው ውስጥ የሚቀመጥበት ዙፋን
ከሊባኖስ እንጨት የተሠራ ነው፤
10የዙፋኑ ምሰሶዎች በብር የተለበጡ ናቸው፤
የራስ ማስደገፊያው በወርቅ ያጌጠ ነው፤
መቀመጫውም በሐምራዊ ሐር የተሸፈነ ነው፤
ውስጡ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት በፍቅር አስውበው
በጠለፉት ጌጥ የተዋበ ነው።
11እናንተ የጽዮን ቈነጃጅት! ንጉሥ ሰሎሞንን ለማየት ኑ፤
እርሱ እጅግ በተደሰተበት በሠርጉ ቀን እናቱ
በራሱ ላይ የደፋችለትን ዘውድ ጭኖአል።

ማድመቅ

Share

Copy

None

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}