መኃልየ መኃልይ 1:1-17

መኃልየ መኃልይ 1:1-17 አማ05

ከሰሎሞን መዝሙሮች መካከል በጣም ውብ የሆነው መዝሙር። ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይልቅ ጣዕም ያለው ስለ ሆነ፥ ከንፈሮችህ ይሳሙኝ። የምትቀባው ሽቱ መልካም መዓዛ አለው፤ ስምህን መጥራት ሽቱን እንደ መርጨት ነው፤ ቈነጃጅትም የሚያፈቅሩህ ስለዚህ ነው። እጄን ይዘህ ሳበኝ፤ አብረን እንሩጥ። ንጉሡ ወደ እልፍኙ አስገባኝ፤ በዚያም አብረን ደስ ይለናል፤ ፍቅርህ ከወይን ጠጅ ይልቅ ያስደስታል፤ ስለዚህ ቈነጃጅት ሁሉ እጅግ ያፈቅሩሃል። እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ! ስሙኝ፤ እኔ ጥቊር ነኝ፤ ይሁን እንጂ ውብ ነኝ፤ የመልኬ ጥቊረት እንደ ቄዳር ድንኳን ነው፤ ውበቴ ግን እንደ ሰሎሞን ቤተ መንግሥት መጋረጃዎች ነው። መልኬን ያጠቈረው የፀሐይ ቃጠሎ ነው፤ ስለዚህ ጥቊር በመሆኔ አትናቁኝ፤ የእናቴ ልጆች የሆኑ ወንድሞቼ ስለ ተጣሉኝ የወይን ተክል ጠባቂ አደረጉኝ፤ ስለዚህ የግሌ የወይን ተክል ለመጠበቅ ጊዜ አልነበረኝም። ውዴ ሆይ! እስቲ ንገረኝ፤ የበጎችህን መንጋ የምታሰማራው የት ነው? በቀትርስ ጊዜ ዕረፍት ያገኙ ዘንድ እንዲመሰጉ የምታደርገው የት ነው? አንተን በመፈለግ የጓደኞችህን መንጋ በመከተል ፊትዋን እንደ ሸፈነች ሴት የምቅበዘበዘው ለምንድን ነው? አንቺ ከሴቶች ሁሉ ያማርሽ ውብ ሆይ! ቦታውን የማታውቂው ከሆነ የበጎቹን ዱካ ተከትለሽ ሂጂ፤ የፍየል ግልገሎችሽንም በእረኞቹ ድንኳኖች አጠገብ አሰማሪ። ውዴ ሆይ! የፈርዖንን ሠረገሎች በሚስቡ ፈረሶች መካከል ያለችውን ውብ ባዝራ ትመስያለሽ፤ የጉንጮችሽ ውበት እንደ ከበረ ሉል ነው፤ አንገትሽም በዕንቊ ጌጥ የተዋበ ነው። እኛ ግን የብር ፈርጥ ያለው የወርቅ ጌጥ እናሠራልሻለን። ንጉሡ በድንክ አልጋው ላይ ዐረፍ ብሎ ሳለ የሽቶዬ መዓዛ ቤቱን ሁሉ ሞላው። ውዴ በጡቶቼ መካከል እንደሚያርፍ፥ መዓዛው እንደ ተቋጠረ ከርቤ ነው። ውዴ፥ ዔንገዲ ተብሎ በሚጠራው የወይን ተክል ቦታ እንደ በቀለ የበረሓ አበባ ነው። ፍቅሬ ሆይ! እንዴት የተዋብሽ ነሽ! እንዴትስ ያማርሽ ነሽ! ዐይኖችሽ እንደ ርግብ ውብ ናቸው። ውዴ ሆይ! አንተም እኮ ውብ ነህ፤ እጅግም ደስ ታሰኛለህ፤ አልጋችንም እንደ ለምለም ሣር ደስ የሚያሰኝ ነው። የቤታችን ምሰሶ የሊባኖስ ዛፍ ነው፤ ጣራውም በጥድ እንጨት የተዋቀረ ነው።