ታዲያ፥ ዳዊት የተናገረው ይህ በረከት ለተገረዙት ብቻ ነውን? ወይስ ላልተገረዙትም? ላልተገረዙትም ነው፤ “አብርሃም በእግዚአብሔር ስላመነ እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት” ብለናል። እንግዲህ አብርሃም እምነቱ ጽድቅ ሆኖ የተቈጠረለት መቼ ነው? ከመገረዙ በፊት ነውን ወይስ ከተገረዘ በኋላ? ከመገረዙ በፊት ነው እንጂ ከተገረዘ በኋላ አይደለም። አብርሃም ገና ከመገረዙ በፊት እምነቱ ጽድቅ ሆኖ እንደ ተቈጠረለት ማረጋገጫ ምልክት እንዲሆነው ተገረዘ፤ ስለዚህ አብርሃም፥ ሳይገረዙ ለሚያምኑና እምነታቸው ጽድቅ ሆኖ ለሚቈጠርላቸው ሁሉ አባት ነው። እንዲሁም አብርሃም ለተገረዙትም አባት ነው፤ ለተገረዙት አባት የሆነበትም ምክንያት በመገረዛቸው ብቻ ሳይሆን እርሱ ከመገረዙ በፊት የነበረውን እምነት በመከተላቸውም ጭምር ነው። ለአብርሃምና ለዘሩ ዓለምን እንደሚወርስ እግዚአብሔር ተስፋ የሰጠው በእምነት ስላገኘው ጽድቅ ነው እንጂ ሕግን በመፈጸሙ አይደለም። የተስፋው ወራሾች ሕግን የሚፈጽሙ ሰዎች ከሆኑማ እምነት ዋጋ አይኖረውም፤ ተስፋም ከንቱ መሆኑ ነው። ሕግ የሚያመጣው የእግዚአብሔርን ቊጣ ነው፤ ሕግ ከሌለ ግን ሕግን የመተላለፍ በደል አይኖርም። ስለዚህ ተስፋው የተመሠረተው በእምነት ላይ ነበር፤ ይህም ተስፋ ለአብርሃም ዘሮች ሁሉ ከእግዚአብሔር በጸጋ የተሰጠ መሆኑ በዚህ ተረጋግጦአል። ይህም ሕግን ለሚከተሉት ሰዎች ብቻ ሳይሆን እንደ አብርሃም ላመኑ ሁሉ ነው፤ በዚህም መሠረት አብርሃም የሁላችንም አባት ነውና። ስለ አብርሃም፦ “የብዙ ሕዝብ አባት አድርጌሃለሁ” ተብሎ ተጽፎአል፤ ይህም ተስፋ ለአብርሃም የተሰጠው እርሱ የሞቱትን በሚያስነሣውና የሌለውን እንዲኖር በሚያደርገው አምላክ ስለ አመነ ነበር። አብርሃም ዘርህ እጅግ ይበዛል ተብሎ በተነገረው መሠረት የብዙ ሕዝብ አባት እንደሚሆን ያመነውና ተስፋ ያደረገው ምንም ተስፋ በማይጣልበት ነገር ነው።
ወደ ሮም ሰዎች 4 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ወደ ሮም ሰዎች 4:9-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች